በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት 

ቅድስት መንበር የጦር መሣሪያ ውድድር በኒውክሌር መሣሪያ አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑን ገለጸች

በቫቲካን የመንግሥታት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ግንኙነት ክፍል ዋና ጸሐፊ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉባኤ ላይ ንግግር አድርገዋል። ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ሪቻርድ ለጉባኤው ተሳታፊዎች ባደረጉት ንግግር ኒውክሌር የጦር መሣሪያ ሙከራዎችን የሚከለክል ስምምነት እንዲፀድቅ አሳስበው በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የጦር መሣሪያ ውድድር ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር ጠቅላላ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ እገዳ ስምምነትን በመጥቀስ ሲናገሩ፥ “የኑክሌር አደጋን ለማስወገድ አስቸኳይ እና ተገቢ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል” ሲሉ አሳስበዋል።

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር ዓርብ መስከረም 16/2018 ዓ. ም. ባደረጉት ንግግር ከ29 ዓመታት በፊት በተደረገው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 14ኛው ጉባኤ ላይ ቅድስት መንበር የፈረመችውን ስምምነት አስታውሰዋል።

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር፥ “ስምምነቱ በሥራ ላይ መዋሉን ማረጋገጥ አለመቻል በኒውክሌር የጦር መሣሪያ ሙከራ ላይ የሚደረገውን ዓለም አቀፍ ጥረት እንደሚያዳክም እና ሥነ ምግባራዊ ኃላፊነትን በሚመለከት ጥያቄዎችን ያስነሳል” ብለዋል።

አደገኛ የውሸት ሕልሞች

“በጋራ ፍራቻ ሰላምን ማስፈን አይቻልም” በማለት የተናገሩት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር፥ “የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ሙከራ አስከፊ ሰብዓዊ እና አካባቢያዊ መዘዝን አስከትሏል ብለው፥ “ቀጣይነት ያለው የኒውክሌር ጦር መሣሪያዎች መስፋፋት እና ዘመናዊነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ከሚሄድ የጦርነት ንግግሮች እና ዛቻዎች ጋር የመጥፋት አደጋን ይደቅናል” ሲሉ ተናግረዋል።

የኑክሌር መሣሪያዎች እንደ ዓለም አቀፍ ስጋት

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጋላገር ዓለም አቀፉን የኒውክሌር ጦር ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት በተዘጋጀው ከፍተኛ ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ ከ80 ዓመታት በፊት በኒው ሜክሲኮ የተደረገው የመጀመሪያው የኒውክሌር ሙከራ ያስከተለውን ከባድ ስቃይ እና ከዚያም በኋላ በሄሮሺማ እና ናጋሳኪ ላይ የደረሰውን አሳዛኝ የቦምብ ፍንዳታ አስታውሰዋል።

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጋላገር የኑክሌር ጦር መሣሪያዎች በዓለም አቀፍ ሰላም፣ በወደፊት ትውልዶች እና በፍጥረት ላይ እያደረሱ ያለውን ተከታታይ ስጋት አጽንዖት ሰጥተው፥ በመቀጠልም በማደግ ላይ ያለው የኒውክሌር ጦር መሣሪያን መልሶ ማቋቋም አዝማሚያ የቅድስት መንበር ከፍተኛ ስጋት መሆኑን ገልጸዋል።

የሰውን ልጅ ሁለንተናዊ ልማት እና ዘላቂ ሰላምን ከማበረታታት ይልቅ ግዙፍ ሃብትን በቀጣይነት ወደ ጦር መሣሪያ ማሸጋገር ተቀባይነት የሌለው እና አዲስ ዓለም አቀፍ ሃላፊነትን የሚጠይቅ መሆኑን ገልጸዋል።

በሰው ሠራሽ አስተውሎት “AI” የታገዘ የጦር መሣሪያ ውድድር

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጋላገር ስለ ሌላው የጭንቀት ምንጭ ሲናገሩ፥ “ሰው ሠራሽ የማሰብ ችሎታን ወደ ወታደራዊ ሥርዓቶች፣ የጠፈር መሣሪታዎችን እና የሚሳኤል መከላከያ ሥርዓቶችን የሚያካትት አዲስ የጦር መሣሪያ ውድድር መፈጠር ነው” ብለዋል።

ከኒውክሌር ጦር መሣሪያ ነፃ የሆነ ዓለም

በቫቲካን የመንግሥታት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ግንኙነት ክፍል ዋና ጸሐፊ ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር፥ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ትጥቅ ለማስፈታት የጀመረውን ጥረት እና ለዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ያለውን ክብር እንዲያድስ በማለት ጠይቀዋል።

የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ሙከራ እገዳ ስምምነትን ማፅደቅ እና ማክበር፥ ከኒውክሌር ጦር መሣሪያ ነፃ የሆነች ዓለምን ለመገንባት እና አስከፊ ሰብዓዊ መዘዞችን ለመከላከል የሚያስችል ተጨባጭ እርምጃ እንደሆነ አስረድተዋል።

ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ፖል ሪቻርድ ጋላገር በመጨረሻም፥ የሁለትዮሽ የጦር መሣሪያ ቁጥጥር ሂደቶችን ማደስ፣ አጠቃላይ የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ሙከራ እገዳ ስምምነትን ሥራ ላይ ማዋልን ጨምሮ ሰፊ ትጥቅ የማስፈታት እርምጃዎች ላይ አዲስ ጥረቶች እንዲደረጉ ጥሪ አቅርበዋል።

 

29 Sep 2025, 16:33