ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፓትሪክ፥ በሱዳን ሐዋርያዊ ጉብኝት በማድረግ ላይ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፓትሪክ፥ በሱዳን ሐዋርያዊ ጉብኝት በማድረግ ላይ  

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፓትሪክ፥ በጦርነት ለተጎዳች ሱዳን የጸሎት እና የቁሳቁስ ዕርዳታ እንዲደረግላት ጠየቁ

በጦርነት በተጎዳች ሱዳን ውስጥ ከሚኖሩ ካቶሊካዊ ማኅበረሰብ እና እንዲሁም ከፖለቲካ ባለሥልጣናት ጋር ለመገናኘት ወደ ሱዳን በሚሄዱበት ወቅት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት እና ቤተ ክርስቲያን ለአገሪቱ ሕዝብ ያላቸው ቅርበት መግለጽ የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ እንደራሴ ተልዕኮ ዋና ማዕከል መሆኑ ተገልጿል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በደቡብ ሱዳን የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ እንደራሴ ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፓትሪክ ሆርጋን በሱዳን ያደረጉትን የአሥር ቀናት ሐዋርያዊ ጉብኝት አጠናቅቀው ተመልሰዋል። ሱዳን በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ በምትገኝበት ወቅት ሐዋርያዊ ጉብኝት ያደረጉት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፓትሪክ ለአገሪቱ ካቶሊካዊ ማኅበረሰብ ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ የቀረበ የመቀራረብ እና የአብሮነት መልዕክት  አድርሰዋል።

በሱዳን ጦር ሃይሎች እና በፓራሚትሪ ፈጥኖ ደራሽ ሃይሎች መካከል የተፈጠው የስልጣን ሽኩቻ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በሚያዝያ ወር 2023 ዓ. ም. ለተጀመረው ጦርነት ምክንያት በመሆን፥ በርካታ የሰው ሕይወት እንዲጠፋ፣ ንብረት እንዲወድም እና ነዋሪውን በማፈናቀል በዓለም ላይ እጅግ የከፋ ሰብዓዊ ቀውስ ማስከተሉን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ገልጿል።

በዚህ የእርስ በርስ ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሲቪሎች መገደላቸው፣ መንደሮች እና የእርሻ መሬቶች መውደማቸው፣ ወደ 12 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸው፣ ከአራት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ወደ ጎረቤት ሀገራት መሰደዳቸው ታውቋል።

በደቡብ ሱዳን የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ እንደራሴ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፓትሪክ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ በሱዳን በምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ያደረጉትን የአሥር ቀናት ሐዋርያዊ ጉብኝት ፈጽመው መመለሳቸውን ገልጸው፥ በደቡብ ሱዳን የቅድስት መንበር እንደራሴ ቢሆኑም በዚህ ወቅት ለሱዳንም ኃላፊነት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ዋና ዓላማ፥ “በመከራ ብዙ ለተፈተነች በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት በአስከፊ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ለምትገኝ የሱዳን ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ያቀረቡትን የመቀራረብ እና የማበረታቻ መልዕክት ለማቅረብ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።

ጸሎት ለሱዳን ካቶሊካዊ ምዕመናን ሰላም

በሱዳን የሚገኝ ካቶሊክ ማኅበረሰብ በሁሉም አቅጣጫ እጅግ ተቸግሯል” ያሉት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፓትሪክ፥ ከምዕምናኑ ዘንድ መልካም አቀባበል እንደተደረገላቸው ተናግረው፥ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው እና ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ የተላከላቸው የአብሮነት እና የመቀራረብ መልዕክት በምዕመናኑ ዘንድ ደስታን በመፍጠሩ እግዚአብሔርን አመሰግነዋል።

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፓትሪክ፥ በሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ወቅት በካርቱም፣ በአትባራ፣ በኦምዱርማን እና በፖርት ሱዳን ተገኝተው ከምዕመናን ጋር መስዋዕተ ቅዳሴን አቅርበዋል። “በሁሉም ቦታዎች ምዕመናኑ መስዋዕተ ቅዳሴውን በበርካታ ቁጥር፣ በደስታ እና በጋለ ስሜት ተሳትፈዋል” ያሉት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፓትሪክ፥ በዚህ መንፈስ መካከል የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛን መልዕክት ለምዕመናኑ ማድረስ በመቻላቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

ለሰላም የቀረቡት ጸሎቶች የእያንዳንዱ ሥነ-ሥርዓት ዋና ማዕከል እንደ ነበሩ የገለጹት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፓትሪክ፥ በእነዚህ አጋጣሚዎች በሙሉ ካቶሊካዊ ምዕመናንን ጨምሮ በአስከፊ ጦርነት ምክንያት በከባድ ፈተና ውስጥ ለሚገኙት የአገሪቱ ሕዝቦች በሙሉ መጸለያቸውን ገልጸዋል።

ከፖለቲካ መሪዎች ጋር የተደረገ ውይይት
ከፖለቲካ መሪዎች ጋር የተደረገ ውይይት

ከፖለቲካ መሪዎች ጋር የተደረገ ውይይት

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፓትሪክ ከሱዳን የሽግግር መንግሥት አባላት ጋር በፖርት ሱዳን ተገናኝተው የሃይማኖት እና የባሕል ነፃነት አስፈላጊነትን በመግለጽ ወደፊት የሚመሠረት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትን በተመለከተ የቅድስት መንበር መርሆችን አስረድተዋል።

“ባለሥልጣናቱ ሐዋርያዊ ጉብኝታቸውን በበጎነት በመቀበል መደሰታቸውን እና ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ አሥራ አራተኛ ለሱዳን ያላቸውን ተቆርቋሪነት እና ለሰላም ያላቸውን ፍላጎት አድንቀዋል” ብለዋል።

ጦርነት ሁሉንም የሚጎዳ፥ በጦርነት ምክንያት ክርስቲያኖችን እና ሙስሊሞችን አንድ ዓይነት ዕጣ እንደሚገጥማቸው እና ሁሉም ሰው እንደሚሰቃይ አስረድተው፥ “ጦርነት ተወግዶ ሱዳንን እንደገና ለመገንባት ተባብረን መሥራት አለብን” ብለዋል።

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፓትሪክ፥  በስዳን ሐዋርያዊ ጉብኝት በማድረግ ላይ
ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፓትሪክ፥ በስዳን ሐዋርያዊ ጉብኝት በማድረግ ላይ

ለቤተ ክርስቲያን መሪዎች እና ሚስዮናውያን የቀረበ ምስጋና

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፓትሪክ ሱዳን ውስጥ በልዩ ልዩ አካባቢዎች ያደረጓቸውን ሐዋርያዊ ጉብኝቶች ከካርቱም ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሚካኤል ዲዲ ጋር መፈጸማቸውን ገልጸው፥ በጉብኝታቸው ወቅት ከሀገረ ስብከት ካህናት፣ ከቅዱስ ኮምቦኒ ማኅበር ሚስዮናውያን እና በፖርት ሱዳን ከሚያገለግሉ ሌሎች ሚስዮናውያን ጋር መገናኘታቸው ተናግረው፥ እጅግ አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ ስላሳዩት ታማኝነት ምስጋናቸውን ገልጸል።

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፓትሪክ በሱዳን ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት በማስመልከት እንደተናገሩት፥ ጉብኝታቸውን ማካሄድ በመቻላቸው እና በሰላም በመፈጸሙ እግዚአብሔርን አመስግነው፥ የሚፈለገው ሊሳካ በመቻሉ እና በተለይም ከክርስቲያን ማኅበረሰቦች ጋር ተገናኝተው የቤተ ክርስቲያኗን ቅርበት ያረጋገጡላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

ለሱዳን የተደረጉ ጸሎቶች

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፓትሪክ በቃለ ምልልሳቸው ማጠቃለያ፥ የመላዋ ቤተ ክርስቲያን የጸሎት ድጋፍን ጠይቀው፥ በመጨረሻም በሱዳን ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት በማስመልከት ለቫቲካን መገናኛ ብዙሃን ደንበኞች ገለጻ ለማድረግ ዕድሉን በማግኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው የዜና አገልግሎቱንም አመስግነዋል።

ለሊቀ ጳጳስ አቡነ ፓትሪክ የተደረገ አቀባበል
ለሊቀ ጳጳስ አቡነ ፓትሪክ የተደረገ አቀባበል

 

24 Sep 2025, 14:38