ነባር ተወላጅ ሴቶች ነባር ተወላጅ ሴቶች   (AFP or licensors)

የአሜሪካ አገራት ነባር ተወላጅ ሴቶች ለተሻለ የወደፊት ሕይወት ዋና ተዋናይ እንዲሆኑ ጥሪ ቀረበ

በአሜሪካ አገራት መንግሥታት ኅብረት የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ሞንሲኞር ሁዋን አንቶኒዮ ክሩዝ ሴራኖ፥ ዓለም አቀፍ የነባር ተወላጆች ቀን እና ስምንተኛው የአሜሪካ አገራት ሳምንት በማስመልከት በምክር ቤቱ ልዩ ስብሰባ ላይ ንግግር አድርገዋል። የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢው ረቡዕ ነሐሴ 7/2017 ዓ. ም. በተካሄደው ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ የአሜሪካ አገራት ነባር ተወላጅ ሴቶች ለተሻለ የወደፊት ሕይወት ዋና ተዋናይ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ቅድስት መንበር መሠረታዊ መብቶቻቸውን ለማስተዋወቅ እና ለማስጠበቅ እንዲሁም ለሁሉም የአሜሪካ አገራት ነባር ተወላጆች በተለይም ለሴት ነባር ተወላጆ ያላትን ቅርበት አረጋግጠዋል። የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ሞንሲኞር ሁዋን አንቶኒዮ ክሩዝ ሴራኖ ኅብረቱ “የአገሬው ተወላጅ ሴቶች ድምፅ፣ ውክልና፣ አመራር፣ መብቶች እና በኢኮኖሚ ራስን መቻል” በሚል መሪ ሃሳብ ዙሪያ በተዘጋጀ ልዩ ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ ሴቶች በኅብረተሰብ ውስጥ ያላቸውን ሚና እና የሚያበረክቱት አስፈላጊ አስተዋፅዖን በማስመልከት መመሪያን ሰጥተዋል።

ቅድስት መንበር ነባር ተወላጅ ሴቶች ከውጭ የሚጣሉ ፖሊሲዎች ተጠቃሚዎች ብቻ ከመሆን ይልቅ የወደፊት የጋራ ሕይወትን በመገንባት ረገድ ንቁ ተዋናዮች ተደርገው እንዲታዩ መጠየቋን ሞንሲኞር  ክሩዝ ሴራኖ ተናግረው፥ ቅድስት መንበር በእነዚህ ቅስቀሳዎቿ አገር በቀል ባሕሎችን በማስተዋወቅ፣ በመንፈሳዊ ጉዞ መካከል ለሕዝቦች ልማዶች እና ቋንቋዎች ትኩረት እንዲሰጥ መጣሯን አስረድተዋል።

ቋሚ ታዛቢው በመቀጠልም፥ ቤተ ክርስቲያን በተለያዩ ተቋሞቿ እና በምታከናውናቸው ተግባራት በኩል በየአካባቢው የሚገኙ በርካታ ነባር ተወላጆችን በመንከባከብ፣ ለትምህርት ለጤና አገልግሎት ተደራሽነት ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በመመደብ እና በማኅበረሰቡ መካከል ግንዛቤን በማስጨበጥ የእነዚህ ማኅበረሰቦች አባላት የራሳቸው ታሪክ ዋና ተዋናይ እና መሪ እንዲሆኑ ማድረግ መቀጠሏን አስረድተዋል። በተለይም የብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤዎች፣ ሀገረ ስብከቶች፣ ቁምስናዎች እና ተልእኮዎች፣ እንዲሁም የፓን አማዞንያን የቤተ ክርስቲያን አውታረ መረብ (REPAM) እና ሌሎች የተጠናከሩ ሥራዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

የቅድስት መንበር ቋሚ ታዛቢ ሞንሲኞር ሁዋን አንቶኒዮ ክሩዝ ሴራኖ በክልሉ ውስጥ ለሚኖሩ ነባር ተወላጆች እና ተጋላጭ ሕዝቦች በተለይም ሴቶችን እና ልጃገረዶችን ለመድረስ የአሜሪካ አገራት መንግሥታት ኅብረት ለሚያበረክታቸው ተግባራት ያላቸውን አድናቆት በመግለጽ፥ ቅድስት መንበር የነባር ተወላጆችን ድምጽ ከፍ ለማድረግ፣ መብቶቻቸውን ለማስጠበቅ እና በማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ ያላቸውን ሙሉ ተሳትፎ ለማረጋገጥ የሚፈልጉ ተነሳሽነቶችን ለመደግፍ የገባችውን ቃል ማደሷን ገልጸዋል።

 

15 Aug 2025, 16:34