የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን   (ANSA)

ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን ከአዲሱ የሊባኖስ ፕሬዝዳንት ጋር መነጋገራቸው ተገለጸ

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን በመካከለኛው ምሥራቅ የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ እንደራሴ እና ከሊባኖስ አዲሱ ፕሬዝዳንት ጋር ተገናኝተው መነጋገራቸውን የቅድስት መንበር መግለጫ አስታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

መግለጫው እንዳስታወቀው፥ ብፁዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ውስጥ ከሚገኙ ጳጳሳዊ ተወካዮች ጋር በአማን ከተማ ተገናኝተው ለሰላም ባላቸው ፍላጎት በሁሉም የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን በዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ የታነጸውን የኢየሱስ ጥምቀት ቤተ ክርስቲያን ያለውፈው ዓርብ ለመባረክ በተጓዙበት ወቅት፥ በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ከሚገኙት ሐዋርያዊ እንደራሴዎች ጋር በዮርዳኖስ ዋና ከተማ አማን ውስጥ ጥር 5/2017 ዓ. ም. የተካሄደውን ስብሰባ መርተዋል።

የቅድስት መንበር መግለጫ ክፍል ሰኞ ማምሻውን እንዳስታወቀው፥ በስብሰባው ላይ እውቅና የተሰጣቸው የባህሬን፣ የግብጽ ሪፐብሊክ፣ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች፣ የዮርዳኖስ፣ የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ፣ የኢራቅ ሪፐብሊክ፣ የእስራኤል መንግሥት፣ የኩዌት መንግሥት፣ የሊባኖስ ሪፐብሊክ፣ የኦማን ሱልጣን፣ የፍልስጤም መንግሥት፣ የኳታር መንግሥት፣ የሶርያ ሪፐብሊክ እና የየመን ሪፐብሊክ ተወካዮች መገኘታቸው ታውቋል።

ብፁዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን በዮርዳኖስ ከሚገኝ የቫቲካን ዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ በዮርዳኖስ የኢየሱስ ጥምቀት ቤተ ክርስቲያን ከተባረከ በኋላ ሊባኖስ አዲስ ፕሬዝዳንት ከመምረጧ ጋር በሶርያ ውስጥ መልካም ለውጦች እንደሚኖሩ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

መካከለኛው ምስራቅ “የሰላም ምድር” እንደሚሆን ተስፋ አለ
የቅድስት መንበር መግለጫ በማብራሪያው፥ በስብሰባው ወቅት በቀጣናው እየተከሰቱ ያሉ ቀውሶች፣ በየሀገራቱ ያለው የፖለቲካ እና የቤተ ክህነት ሁኔታ፣ በአንዳንድ አካባቢዎች የሚታዩ የተስፋ ምልክቶች እና በግጭቶች ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸውን ሕዝቦች የሚጎዱ ሰብዓዊ ቀውሶች መኖራቸውን አስታውቋል።

መግለጫው በመቀጠልም፥ “የተኩስ አቁም ስምምነት በቅርቡ እንደሚደረግ እና መካከለኛው ምስራቅ የሰላም ምድር እንደሚሆን፣ ክርስቲያኖች በሃይማኖቶች መካከል ወንድማማችነት እንዲኖር እና ለየአገሮቻቸው ዕድገት አስፈላጊ መሣሪያ ሆነው የሚቆዩበት ተስፋ አለ” ሲል አስታውቋል።

አዲስ ከተመረጡት የሊባኖስ ፕሬዝዳንት ጋር የተደረገ የስልክ ጥሪ
ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን ጥር 1/2017 ዓ. ም. ከተመረጡት አዲሱ የሊባኖስ ፕሬዝዳንት ዮሴፍ አውን ጋር ሰኞ ከሰዓት በኋላ በስልክ መነጋገራቸውን የቅድስት መንበር መግለጫ አስታውቋል።

“አስደሳች የስልክ ውይይት ነበር” ያለው መግለጫው፥ ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን ለአዲሱ የሊባኖስ ፕሬዝዳንት መልካም ምኞት መግለጻቸውን እና በጸሎታቸውም እንደሚያስታውሷቸው ማረጋገጣቸውን አስታውቋል።

ሊባኖስ ውስጥ በፍጥነት የተካሄደውን የጠቅላይ ሚኒስትር ናዋፍ ሳላም ሹመት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን በደስታ ማናገራቸውን መግለጫው አክሏል።

 

14 January 2025, 17:12