ፈልግ

በዮርዳኖስ ውስጥ የሚገኝ የንግደት ሥፍራ በዮርዳኖስ ውስጥ የሚገኝ የንግደት ሥፍራ  (ANSA)

ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን በዮርዳኖስ ያለውን የኢየሱስ ጥምቀት ቤተ ክርስቲያን እንደሚባርኩት ተገለጸ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የኢየሱስ ጥምቀት በተፈጸመበት በዮርዳኖስ ወንዝ ምሥራቃዊ ዳርቻ የታነጸውን አዲሱን ቤተ ክርስቲያን እንዲባርኩት የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊንን ጳጳሳዊ መልዕክተኛ አድርገዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይህን ያስታወቁት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን በበዓሉ ሥነ-ሥርዓት ላይ ለመገኘት ዝግጅት ላይ ባሉበት ወቅት በጻፉት መልዕክት እንደ ሆነ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “የሕዝብ ብርሃን” የሚለውን የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ ሐዋርያዊ መልዕክት ጠቅሰው በጻፉት መልዕክታቸው፥ “እግዚአብሔር ሰዎችን ሊቀድሳቸውና ሊያድናቸው የፈለገው በግል እና በመካከላቸው ምንም ዓይነት ትስስር ሳይኖር፥ ነገር ግን እርሱን በእውነት የሚያምኑትን እና በቅድስና የሚያገለግሉትን ሕዝቦች ሊያቋቁም ፈልጎ ነበር” ሲሉ አስረድተዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን አዲሱን ቤተ ክርስቲያን ባርከው የሚከፍቱት ካቶሊካዊ ምዕመናን ወደ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት ቤተ ክርስቲያን ዓመታዊ ንግደት ማድረግ የጀመሩበት 25ኛ ዓመት መታሰቢያ በሚከበርበ ዓርብ ጥር 2/2017 ዓ. ም. እንደሚሆን ታውቋል።

ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን በዮርዳኖስ ወንዝ (አል-ማግታስ) የጥምቀት ቦታ ላይ የታነጸውን አዲሱን ቤተ ክርስቲያን የሚባርኩት የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት በመምራት እንደሚሆን ታውቋል። በሥነ-ሥርዓቱ መካከል የኢየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒዛባላ እንደሚገኙበት ሲጠበቅ፥ በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት ላይ በቅድስት ሀገር የሚገኙ ካቶሊካዊ ማኅበራትን ጨምሮ ሁሉም የላቲን እና የምሥራቅ ካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት ተካፋይ እንደሚሆኑ ታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በመልዕክታቸው ላይ እንደገለጹት፥ በዮርዳኖስ ያሉ ክርስቲያኖች ግንባታው 15 ዓመታት ያህል የፈጀውን የኢየሱስ ጥምቀት ቤተ ክርስቲያን ቡራኬን በጉጉት እንደሚጠብቁት እና ይህም ቤተ ክርስቲያን ለምዕመናኖቿ ያላትን ፍቅር የሚያሳይ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቀጥለውም፥ የዮርዳኖስ ክርስቲያኖች ክርስቶስን እንዲመስሉ፣ ከእምነት ለሚመነጨው ሕያው ተስፋ እና ጎረቤቶቻቸውን በመውደድ በአዲስ ኃይል ይመሰክሩ ዘንድ ምዕምናኑን እንዲያታቱ ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን ጋብዘዋል።

ቅዱስነታቸው በመጨረሻም፥ ብፁዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ለሚገኙት ካቶሊካዊ ምዕመናን ብቻ ሳይሆን ለሲቪል ባለሥልጣናት፣ ለሌላ እምነት ተከታዮች እና የቤተ ክርስቲያንን ተልዕኮን ለሚፈጽሙት፣ የሃይማኖት ነፃነትን፣ የዓለም ሰላም እና ስብዓዊ ክብርን ለሚደግፉ ሁሉ ሰላምታቸውን እንዲያደርሱላቸው ጠይቀዋል።

የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤነዲክቶስ 16ኛ ግንቦት 2/2011 ዓ. ም. የቤተ ክርስቲያኑን የመሠረት ድንጋይ ማስቀመጣቸው ይታውሳል። የዮርዳኖስ የኢንቨስትመንት ቢሮ የቦርድ ሰብሳቢ አባል የሆኑት ናዲም ሙአሸር አዲሱ ቤተ ክርስቲያን እንዲታነጽ ልገሳን በማድረግ ተከታትለው ያሠሩት፥ ኢየሱስ ክርስቶስ በተጠመቀበት በዮርዳኖስ ወንዝ አቅራቢያ በደረሰ የመኪና አደጋ በሞት ለተለየው ልጃቸው መታሰቢያነት እንዲሆን በማለት እንደ ነበር ይታወሳል።


 

08 January 2025, 15:06