ካርዲናል ፓሮሊን፥ በመካከለኛው ምስራቅ የክርስቲያኖች መገኘት አስፈላጊ መሆኑን ገለጹ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ባለፈው ሳምንት ዮርዳኖስን የጎበኙት ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን በዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ የታነጸውን አዲሱ የኢየሱስ ጥምቀት ቤተ ክርስቲያን ዓርብ ጥር 2/2017 ዓ. ም. የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓትን በመምራት መባረካቸው ሲታወስ፥ በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ተስፋን ምልክት ያደረጉ ከስድስት ሺህ የሚበልጡ ምእመናን መካፈላቸው ታውቋል።
ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን ከበዓሉ መልስ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቆይታ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለዲፕሎማሲ አካላት ጥር 1/2017 ዓ. ም. የተናገሩትን ጨምሮ ወቅታዊ የዓለም ሁኔታዎች በማስመልከት ቃለ ምልልስ አድርገዋል።
በዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ የታነጸውን አዲሱ የኢየሱስ ጥምቀት ቤተ ክርስቲያን ቡራኬን አስመልክተው እንደተናገሩት፥ በዓሉ ደማቅ እና በሚገባ የተዘጋጀ እና ከሁሉም በላይ ትልቅ ተስፋ ያለው እንደ ነበር ገልጸዋል። በዚህ የተስፋ ኢዮቤልዩ ዓመት በብዙ ግጭቶች፣ ውጥረቶች እና ፈንጂዎች የተከፋፈለው ክልል ዛሬ ለም የእርሻ መሬት መሆኑ በራሱ የተስፋ ምልክት ነው” ያሉት ብጹዕነታቸው፥
ነብዩ ኢሳይያስ እንዳለው፥ ሰዎች ሰይፋቸውን ማረሻ ጦራቸውንም ማጭድ ማድረግ እንደሚችሉ ተናግረው፥ የጦር መሣሪያም የሰላም መሣሪያ ሊሆን እንደሚችል አስረድተዋል። የሰዎች ትልቅ እና ሕያው ተሳትፎ የተስፋ ምክንያት እንደሆነ፣ ክርስትና እና የእግዚአብሔር ጸጋ ወቅታዊ ግጭቶችን ለመፍታት የሚያግዙ መንገዶችን ለማግኘት ወሳኝ ኃይሎች መሆናቸውን አስረድተዋል።
ምንም እንኳን ያለፉት እና የቅርብ ጊዜ ክስተቶች ስደትን የሚያበረታቱ ቢሆንም ክርስቲያኖች ከጥንት ጀምሮ በመካከለኛው ምሥራቅ እንደሚገኙ የገለጹት ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ በእነዚህ አገራት የሚኖሩ ክርስቲያኖች በቁጥር እየቀነሱ መምጣታቸውን ገልጸው፥ በመካከለኛ ምሥራቅ አገራት ውስጥ የክርስቲያን ማኅበረሰብ ከጥንት ጀምሮ የኖረ በመሆኑ አረብ ማለት ክርስቲያን ማለት እንደሆነ አስረድተዋል።
በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ ክርስቲያኖች በሁሉም መስክ አስተዋጽዖ ማድረግ እንደሚችሉ ብጹዕነታቸው ተናግረው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ደጋግመው “መካከለኛው ምሥራቅ ያለ ክርስቲያኖች አስፈላጊ የሆነውን የክልሉን ማንነት የሚገልጽ ታሪክ ካጣ ድሃ ይሆናል” ማለታቸውን አስታውሰዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለዲፕሎማሲ አካላት ባደረጉት ንግግር ጋር የተገናኙ አወንታዊ መግለጫዎችን ማንበባቸውን የተናገሩት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ ሶርያ ውስጥ ሁሉም ዜጎች እኩል መብት እና ጥቅም የሚያገኙበት አዲስ ዘመን እንደሚጀምር ተስፋ እንደሚያደርጉ ገልጸው፥ ይህም ቅድስት መንበር ለሁሉም ሀገራት ያቀረበችው የዜግነት ጽንሰ ሃሳብ እንደሆነ በማስረዳት፥ ሁሉም ዜጎች በሕግ ፊት እኩል መብት እና ግዴታ እንዳላቸው ተናግረው፥ ይህ ማለት የአናሳ ብሔረሰቦች እና ክርስቲያኖች መብቶች መከበርን እንደሚያረጋግጥ በእውነት ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል።
ሊባኖስ ከሁለት ዓመታት በኋላ ፕሬዝዳንቷን መምረጧ አዎንታዊ ምልክት እንደሆነ አምናለሁ” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ ይህም ለአገሪቱ ቀጣይነት እና ሕልውና ወሳኝ እንደሆነ ላለፉት ሁለት ዓመታት ስንገልጽ ቆይተናል ብለው፥ የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ፥ “መልዕክት የሆነች አገር” ያሉትን በመጥቀስ፥ ሊባኖስ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ሃይማኖታዊ ልዩነቶች አብረው የሚኖሩባት ሀገር መሆኗን ተናግረዋል።
“በሊባኖስ የፕሬዚዳንትነት ቦታን ማስጠበቅ እና ተቋማትን ማጠናከር ቅድሚያ የሚሰጥባቸው ጉዳዮች እንደሆኑ ሁሌም አበክረን ስንገልጽ ቆይተናል” ያሉት ካርዲናል ፓሮሊን፥ የተስፋ ምልክት የሆነው ይህ ምርጫ ለሊባኖስ አዲስ ምዕራፍ እንዲከፍት ከልብ በመመኘት ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች አንድ ላይ ሆነው የጋራ መግባባት ለመፍጠር እና ለአገሪቱ ጥቅም የሚሠሩበት፣ በተለይም አገሪቱ በአስቸኳይ የምትፈልገውን ማሻሻያ ለማድረግ እንደሚረዳ አስረድተዋል።
በቤይሩት ወደብ በደረሰው ፍንዳታ ለተጎዱት ቤተሰቦች ፍትህ መስጠት፣ በሀገሪቱ ድህነት እና ስቃይ ያስከተለውን የኢኮኖሚ ውድቀት ወደ ነበረበት መመለስ፥ እንዲሁም ፕሬዚዳንት መምረጥ ከአዎንታዊ ማሻሻያዎች መካከል ጥቂቶቹ እንደሆኑ ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን ተናግረው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅርቡ ወደ ሉክሰምበርግ እና ቤልጂየም ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ወቅት የጦርነት ሁኔታዎችን በመጥቀስ “ታማኝነት ያለው ድርድር የሚደነቅ ስምምነት” ማድርግ እንደሚገባ መናገራቸውን አስታውሰዋል።
የመደራደር አቅም ማነስ እና የሕግ የበላይነት ማጣት የሚያሳዝን እንደሆነ ገልጸው፥ ቅዱስነታቸው በቅርቡ ለዲፕሎማቶች ባደረጉት ንግግር፥ ለዚህ ሁኔታ በርካታ ምክንያቶችን በማንሳት፥ ያለመተማመን እና የእርስ በርስ ፍራቻ መኖሩን በማብራራት በክልሎች እና በማኅበረሰቦች መካከል እየጨመረ የመጣው መለያየት የጋራ መፍትሄዎችን ለመፈለግ እንቅፋት እንደሆነ አስረድተዋል።
ለመደራደር እና ለመነጋገር በሌላኛው ወገን ቢያንስ በትንሹ መተማመን ሊኖር እንደሚገባ ብጹዕነታቸው ገልጸው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያስረዱት ሌላው ገጽታ ጠላት የሚባለውን የሌላኛው ወገን አቋም የማየት ችሎታ እንደሆነ ተናግረው፥ የሌላውን ወገን ምክንያቶች ለመረዳት ወይም ቢያንስ በቁም ነገር ለማሰብ ፍላጎት ሊኖር እንደሚገባ ተናግረዋል።
ዛሬ ድርድር አስቸጋሪ የሆነው በዚህ ምክንያት እንደሆነ አስረድተው፥ በተጨማሪ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ እንደ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ያሉ ውይይቶችን ለማበረታታት የተቋቋሙ ተቋማት ቀውስ ውስጥ እንደሚገኙ መናገራቸውን በማስታወስ፥ ዛሬ እነዚህ ተቋማት ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የተጫወቱትን ሚና በተሳካ ሁኔታ ለመወጣት እንደሚታገሉ እና ሌሎች ብዙ ምክንያቶች ቢኖሩም የችግሮች ሁሉ መነሻዎች እነዚህ መሆናቸውን አስረድተዋል።
“የሄልሲንኪ መንፈስ በትክክል የቡድን አስተሳሰብን እንደሚያወግዝ የገለጹት ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ ዓላማቸው የቡድን አስተሳሰብን ማሸነፍ እንደሆነ ተናግረው፥ የምንኖረው ለሁለት በተከፈለ እና በሚቃረን ዓለም ውስጥ እንደሆነ በማስረዳት፥ “ምናልባት ዛሬ እነዚህ ቡድኖች ተከፋፍለው በቁጥር እንደጨመሩ ገምተው፥ በተወሰነ መልኩ ሁለት ብሎኮች በነበሩበት ወቅት ልዩነትን ማስወግድ ቀላል ሊሆን ይችላል” ሲሉ ተናግረዋል።
የሄልሲንኪ መንፈስ ከጠላት ሃሳብ ለመራቅ የሚደረገውን ጥረት እንደሚወክል እና ተመሳሳይ አመለካከት ከሌላቸው ጋር የጋራ ስምምነት ማድረግን እንደሚያበረታታ የገለጹት ብጹዕነታቸው፥ የሄልሲንኪ መንፈስ ከግል አመለካከት ባሻገር ወይም ከብቸኛ አመለካከት ይልቅ ሌሎች ሕጋዊ አመለካከቶች መኖራቸውን በመቀበል ከራስ ጋር መታረቅ እንደሚቻል እና ይህም ግጭትን ለማሸነፍ የሚያስችል ስምምነትን ለማግኘት ፈቃደኛ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል።
በግል እይታቸው መሠረት ፍትሐዊ ሰላም ማለት በዓለም አቀፍ ሕግ እና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መግለጫ ላይ የተመሠረተ ሰላም ማለት ነው” ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ በአገሮች እና በክልላዊ ማኅበረሰቦች መካከል ያለውን ግንኙነት ለመቆጣጠር የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ መሳሪያዎች በእጁ እንዳሉ ገልጸው፥ በክርስቲያናዊ እይታ ፍትህን በተለያዩ ገፅታዎች ብንረዳም ነገር ግን በመሠረቱ ፍትሃዊ ሰላም ከዓለም አቀፍ ሕግ እና ደንብ ጋር የተጣጣመ ሰላም መሆኑን እንደሚያመለክት አስረድተዋል።
በክርስቲያናዊ አስተሳሰብ ፍትሕ ማለት ለእያንዳንዱ ሰው የሚገባውን መስጠት ብቻ ሳይሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ ያመጣው ፍትሕ ሲሆን፥ ይህም ለሌሎች ፍቅር እና ይቅርታ የሚሆን ከፍ ያለ የፍትህ ዓይነት መሆኑን ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን አስረድተዋል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ለዲፕሎማሲ አካላት ባደረጉት ንግግር፥ ስለ ይቅርታ ዲፕሎማሲ ተናግረው፥ ይህም በተለይ ከፍትህ ጥያቄዎች በላይ የመሄድ ችሎታን የሚያጎላ እንደሆነ አስረድተዋል።
በቻይና ውስጥ እንደሚታየው ውስብስብ ሁኔታዎች ማጋጠማቸው እና የተለያዩ አስተያየቶች መነሳታቸው ምክንያታዊ ነው” ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ አስተያየቶች ሊለያዩ ቢችሉም በእነዚህ አመለካከቶች አለመደንገጣቸውን በመግለጽ፥ ቅድስት መንበር በጠረጴዛው ላይ ካሉት ቁልፍ ጉዳዮች መካከል አንዱ የሆነውን ውይይት መጀመር ውጤታማ መፍትሄ አድርጋ እንደምትወስደው አስረድተዋል።
ከወሳኝ እና ፈታኝ ጉዳዮች መካከል አንዱ የጳጳሳት ሹመት እንደሆነ የተናገሩት ብጹዕነታቸው፥ በጳጳሳት ሹመት ላይ የተደረገው ስምምነት ሁለት መሠረታዊ ነገሮችን ለማሳካት እንደሚፈልግ እና ቀስ በቀስ እንደሚሻሻል እና አንዳንዴም አንድ እርምጃ ወደ ኋላ ቢጓዝም ነገር ግን ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ እንደሚጓዝ አስረድተዋል።
የመጀመሪያው ነገር ቻይና ውስጥ የሚገኙ ሁሉም ካቶሊካዊ ጳጳሳት ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳት ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ማረጋገጥ እንደሆነ የተናገሩት ብጹዕነታቸው፥ ይህ ለካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን መሠረታዊ ነገር እንደ ሆነ ተናግረዋል። ሁለተኛው ሙከራ፥ ሁልጊዜ የተሳካ ባይሆንም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አንድነትን በማጎልበት መከፋፈልን ማሸነፍ እንደሆነ አስረድተዋል።
“አስማታዊ መፍትሄ የለም” ያሉት ብጹዕነታቸው፥ ነገር ግን ስምምነቱ የኅብረት ጉዞ መኖሩን እንደሚያመለክት እና ትንሽ ፍሬ ማፍራት በጀመረው ዘገምተኛ እና ፈታኝ ጉዞ ውስጥ ውጤቶች ገና ላይታዩ እንደሚችሉ፣ በሁለቱ ወገኖች መካከል መተማመን ሲኖር እና የውይይት ችሎታ እያደገ ሲሄድ ውጤቱ የበለጠ ግልጽ ይሆናል” ብለዋል።
ከቻይና መንግሥት ጋር የተደረገው ውይይት ውጤት ጥሩ በመሆኑ ተስፋ የሚያደርጉበት ምክንያት መኖሩን የገለጹት ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ስለ ትዕግስት ዲፕሎማሲን ለዲፕሎማሲ አካላት ያደረጉትን ንግግር በማስታወስ፥ ይህ ጉዳይ ከሌሎቹ በበለጠ ምናልባትም በአጠቃላይ ሐዋርያው ያዕቆብ እንደሚያበረታታን የትዕግስትን አቅም ማዳበር እንዳለብን፣ ዘሩን የዘራው ገበሬ ዝናብን ሆነ በረዶ በትዕግሥት መጠበቁን ማሰብ እንደሚገባ በማሳሰብ የተዘራው ዘርም ፍሬን እንደሚሰጥ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ብዙዎቹ የተጠቀሱት ስሜቶች በአሁን ጊዜ ላይ ብቻ በማትኮር ያለፈውን ችግር በማገናዘብ በረጅም ጊዜ ዕይታ ወደፊት የማየት አቅም ማጣት እንደሆነ አስረድተው፥ ስለዚህ የውሸት ቅዠቶችን ከማዳበር ይልቅ በእግዚአብሔር ቸርነት በመተማመን በተስፋ እና በቁርጠኝነት ወደፊት መራመድ እንችላለን” ሲሉ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ያደረጉትን ሰፊ ቃለ ምልልስ ደምድመዋል።