ጎጂ የሆኑ መረጃዎችን በማስቀረት ተስፋን መጋራት እንደሚገባ ማሳሰቢያ ቀረበ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ልብ እና ተስፋ የሚሉ ሁለት አስፈላጊ እሴቶችን ለጋዜጠኞች አጉልቶ የሚያሳየው የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የመገናኛ ቀን በሁለት ሥነ-ሥርዓቶች የተከፈተ ሲሆን፥ የመጀመሪያው በሮም ሀገረ ስብከት የማኅበራዊ መገናኛ ጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር በሆኑት አባ ጁሊዮ አልባኔዜ በመሩት የንስሐ ሥነ-ሥርዓት የተከበረ እና ሁለተኛው ብፁዕ ካርዲናል ሬይና የመሩት ዓለም አቀፍ የመገናኛ ባለሞያዎች የተካፈሉት የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት እንደሆነ ታውቋል። ለመክፈቻ በዓሉ ሥነ-ሥርዓቱ ምልክት ይሆን ዘንድ የቅዱስ ፍራንሲስ ደ ላሳል ቅዱስ አጽም ከ1905 ዓ. ም. ጀምሮ በሰሜን ጣሊያን ትሬቪሶ ከተማ ከነበረበት ወደ ሮም መምጣቱ ታውቋል።
ብፁዕ ካርዲናል ሬይና በበዓሉ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ባሰሙት ቃለ-ምዕዳን፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ 59ኛው የዓለም የመገናኛ ቀን፥ ተስፋን በየዋህነት መስጠትን አስመልክተው ያቀረቡትን መልዕክት በመጥቀስ የኢዩቤልዩ ዓመት ማዕከል የሆነውን ተስፋ ከሌሎች ጋር ለመካፈል መጠራታችንን አስታውሰዋል።
የክርስቶስን ምሳሌ በመከተል ጎጂ መረጃን ማስወገድ
ብፁዕ ካርዲናል ሬይና በመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት ላይ ባሰሙት ቃለ-ምዕዳን፥ የኢዮቤልዩ ዓመት የምህረት ጊዜ መሆኑን በመግለጽ፥ ኃጢያት ወደ እግዚአብሔር ይቅርታ የሚለወጥበ ወቅት መሆኑን በማስታወስ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የመገናኛ ባለሞያዎች ጎጂ መረጃዎን በማስወገድ ስለ ተስፋ እንዲናገሩ ያቀረቡትን መልዕክት አጠናክረዋል።
ብፁዕ ካርዲናል ሬይና፥ ዝሙት ስትሰራ ስለተያዘች ሴት በሚናገር የወንጌል ክፍል ላይ በማስተንተን ባሰሙት ቃለ-ምዕዳናቸው፥ በዚህ አሳፋሪ ገጠመኝ ውስጥ ኢየሱስ ክርስቶስ ጠብን አስወግዶ ከእውነት ጋር የሚተባበርበትን የመገናኛ መንገድን መምረጡን አስታውሰው፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ፈሪሳውያንን፥ ከእናንተ መክካከል ኃጢአት የሌለበት አስቀድሞ በድንጋይ ይውገራት” በማለት ትዕቢትን እንዲያወግዱ ማሳሰቡን አስታውሰዋል።
“ጎጂ የሆኑ መረጃዎን ለማስቀረት አስቀድሞ ትዕቢትን ማስወግድ አለብን” ያሉት ብፁዕ ካርዲናል ሬይና፥ ፈራጅ እግዚአብሔር ብቻ መሆኑን ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚያስታውሱን ገልጸው፥ ኢየሱስ ክርስቶስ አመንዝራይቱን እንደ ጥፋተኛ ሳይቆጥራት ነገር ግን የተፈጥሮ ክብሯን በመገንዘብ የመታደስ ተስፋን እንደሰጣት ተናግረዋል።
የተስፋ አድማስ
ኢየሱስ ክርስቶስ አመንዝራይቱን ሴት፥ “ሂጂ፥ ደግመሽ ኃጢአት አትሥሪ” ባለው ላይ በማሰላሰል ቃለ- ምዕዳናቸውን ያሰሙት ብጹዕ ካርዲናል ሬይና፥ እነዚህ ቃላት ተስፋን በመስጠት የመለወጥ ሂደትን የሚያመለክቱ፣ የሴቲቱ የምሕረት ተግባር መሆናቸውን ገልጸዋል። “የኢዮቤልዩ በዓላችንን እንደ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ቀን ለማክበር ከፈለግን፥ የእያንዳንዱን ሰው ክብር የሚያውቅ እና ለጋራ መኖሪያችን እንክብካቤ የሚያደርግ የመገናኛ ዘይቤን መከተል አለብን” ሲሉ አሳስበዋል።
የመለወጥ ጥሪ
ከመስዋዕተ ቅዳሴው ሥነ-ሥርዓት ቀደም ብሎ የቀረበው የንስሐ ጸሎት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የ2025 ዓ. ም. የኢዮቤልዩ ዓመትን በማስመልከት የሰጡትን መመሪያ በማበብ እንደሆነ ታውቋል።የጸሎት ሥነ-ሥርዓቱ እያንዳንዱ ተሳታፊ በልቡ ያለውን ተስፋ እንዲያስብ እና ኢየሱስ ክርስቶስን በሚወክል ቅዱስ በር በኩል በማለፍ የመለወጥ መንገድ እንዲከተል የሚጋብዝ እንደሆነ ታውቋል።
በሮም ሀገረ ስብከት የማኅበራዊ መገናኛ ጽሕፈት ቤት ዳይሬክተር የሆኑት አባ ጁሊዮ አልባኔዜ በበኩላቸው፥ የመገናኛ ባለሞያዎች ሙያቸውን እንደ ተልዕኮ መስክ እንዲመለከቱት በማሳሰብ፥ መለወጥ ከሙያዊ ሕይወት ሊለይ እንደማይል አስረድተዋል። የመገናኛ ባለሞያዎች ለሰዎች ቃል ቅጥረኞች ሳይሆኑ ነገር ግን ግንኙነታቸው ዘወተር የእግዚአብሔርን ፍቅር እና ልግስና የሚያንጸባርቅ መሆኑን እንዲያረጋግጡ አሳስበዋል።
ስለ በጎነት መናገር
አባ አልባኒዜ የመገናኛ ባለሞያዎች ሥራቸው የእግዚአብሔርን በጎነት የሚገልጽ ወይም ዓለማዊ ዓላማዎችን የሚያራምድ መሆኑን ለይተው እንዲያውቁ አደራ ብለው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ማኅበራዊ መገናኛ ተስፋን በማጎልበት ወንድማማችነትን የበለጠ ለመገንባት አስተዋፅዖ የሚያደርግ ይሁን” በማለት ያቀረቡትን ጥሪ በማስተጋባት መልዕክታቸውን ደምድመዋል።