ፈልግ

ካርዲናል ፓሮሊን እና ካርዲናል ፒሳባላ በኢየሱስ ጥምቀት ቤተ ክርስቲያን ቡራኬ የተሰማቸውን ደስታ ገለጹ

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን እና ፓትርያርክ ፒየርባቲስታ ፒሳባላ በዮርዳኖስ የሚገኘው የኢየሱስ ጥምቀት ቤተ ክርስቲያን ከተባረከበት ሥፍራ ሆነው የተሰማቸውን ታላቅ ደስታ የተጋሩ ሲሆን፥ ታሪካዊ ክስተቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ምዕመናን ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ መሰብሰቡ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“በዙሪያችን ሁሉም ነገር ስለ ግጭቶች፣ ስለ መለያየት፣ ስለ ጥላቻ እንደሚናገር እናውቃለን፤ ነገር ግን በሌላ በኩል ዛሬ ትኩረታችንን ሕይወታቸውን ለኢየሱስ ክርስቶስ እና ለጎረቤቶቻቸው መስጠት በሚፈልጉት በርካታ ሰዎች ላይ ለማድረግ እንፈልጋለን” ብለዋል።

የኢየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ ብፁዕ ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒሳባላ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ ዓርብ ታኅሳስ 2/2017 ዓ. ም. በዮርዳኖስ የሚገኝ የኢየሱስ ጥምቀት ቤተ ክርስቲያን ቡራኬን ተከትሎ የተሰማቸውን ደስታ አጋርተዋል።

በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው መስዋዕተ ቅዳሴን የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብፁዕ ካርዲናል ፒዬትሮ ፓሮሊን የመሩት ሲሆን፥ በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ስድስት ሺህ ምዕመናን እና ነጋዲያን ተገኝተዋል።

በአል-ማግታስ የጥምቀት ሥፍራ በተከናወነው በእምነት የተሞላ አስደሳች በዓል የተሰማቸውን ታላቅ ደስታ ሁለቱ ብጹዓን ካርዲናሎች፥ ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን እና ብጹዕ ካርዲናል ፒዛባላ ለምዕመናኑ በማጋራት “በተለይም በተስፋ ኢዮቤልዩ ወቅት ሊያበረታታን ይገባል” ብለዋል።

ፓትርያርክ ፒዛባላ፥ የቤተ ክርስቲያኑ ቡራኬ ለረዥም ጊዜ ሲጠበቅ የቆየው ሂደት ፍጻሜን እንደሚያመለክት ገልጸው፥ ይህም የቤተ ክርስቲያን መታደስ እና የአዲስ ጅምር ምልክት ነው” ሲሉም አክለዋል።

“የኢየሱስ ክርስቶስን ጥምቀት እና አገልግሎቱንም መጀመሩን የሚያመለክተው ይህ ቦታ ለቤተ ክርስቲያናችን አዲስ ሕይወት ጅምር ነው” ያሉት ፓትርያርክ ፒየርባቲስታ ፒሳባላ፥ በቅድስት አገር ውስጥ በመካሄድ ላይ ያለው ጦርነት ሰብዓዊ ቀውሶችን በማስከተል ነዋሪውን ለከፍተኛ ስቃይ መዳረጉን አስረድተዋል።

ካርዲናል ፒየርባቲስታ ፒሳባላ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ያደረጉት ቃለ ምልልስ፥

የቤተ ክርስቲያኑ ቡራኬ በአካባቢው ባለው ሌላኛው በጎ የሕይወት ክፍል ላይ እንዲያተኩሩ መጋበዙን አበክረው በመናገር፥ ይህም ሕይወታቸውን ለጌታ እና ለጎረቤቶቻቸው ለማቅረብ በሚፈልጉ በርካታ ሰዎች ላይ የሚታይ መሆኑን አስረድተዋል።

ካርዲናል ፓሮሊን ክርስቲያኖች ተስፋ እንዲያደርጉ ጋብዘዋል
ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን የእርሳቸው በሥፍራው መገኘት ለመካከለኛው ምስራቅ ክርስቲያኖች የመቀራረብ ተጨባጭ ተግባር እንደሆነ ከገለጹ በኋላ በደረሰው ከፍተኛ ስቃይ የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸዋል። የቤተ መቅደሱን ቡራኬ ምዕመናኑ በደስታ እንዲቀበሉት አሳስበው፥ የተስፋ ኢዮቤልዩ በሚከበርበት በዚህ ወቅት በመካከለኛው ምስራቅ ከፍተኛ ስቃይ እየደረሰ ቢሆንም በቤተ ክርስቲያኑ ቡራኬ የተሰማቸውን የግል ስሜት አጋርተዋል።

የኢዮቤልዩ ቅዱስ ዓመት በጣም ውስብስብ እና አሳዛኝ በሆነ ሁኔታ ውስጥ መሆኑ እውነት ነው” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ በብዙ የዓለም ክፍሎች እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት ጉዳቶች እየደረሱ መሆኑን ጠቁመው፥ ይሁን እንጂ ክርስትና እና የወንጌል ምስክርነት ሰላምን እና እርቅን ለማስፋፋት መሆኑን ተናግረዋል።

ኢየሱስ የሰው ቤተሰብ አባል የሆነበት
“ይህ ቦታ ኢየሱስ የሰው ቤተሰብ አባል የሆነበት ቦታ በመሆኑ እጅግ እጅግ አስፈላጊ ነው” ያሉት ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ ቤተ ክርስቲያን እና ክርስቲያኖች በዚህ ሁኔታ ውስጥ የሰላም፣ የእርቅ እና የተስፋ ምልክቶች መሆናቸውን በማሳሰብ “የኢዮቤልዩ ጥሪም ይህ ነው” ሲሉ አሳስበዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ፓሮሊን፥ የመካከለኛው ምስራቅ ሀገር ዮርዳኖስ በሰላም እና በስምምነት ለመቆየት የቻለችበትን ተጠይቀው ሲመልሱ፥ “ዮርዳኖስ በቀጣናው እና በዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ዘንድ የምትጫወተውን ሚና እንደምትቀጥል ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል።

ዮርዳኖስ ለሰላም የጋራ ውይይት እና ጥረት የሚደረግባት አገር ናት” ብለው፥ ከዚህም በላይ ሕዝቡ የዚህን ቀን አስፈላጊነት፣ ውበት እና የቤተ ክርስቲያን ቡራኬን በማስታወስ ሰላማዊ አስተሳሰብን ይዞ ሁከትን እንዲያሸንፍ አሳስበዋል።

 

11 January 2025, 16:19