ፈልግ

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጆቫኒ ፒየትሮ ዳል ቶሶ፤ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጆቫኒ ፒየትሮ ዳል ቶሶ፤ 

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጆቫኒ፥ የመካከለኛው ምስራቅ ክርስቲያኖች ብቻቸው አለመሆናቸውን ተናገሩ

በዮርዳኖስ መዲና አማን የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ እንደራሴ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጆቫኒ ፒየትሮ ዳል ቶሶ በመካከለኛው ምሥራቅ ያሉ ክርስቲያን ማኅበረሰቦችን በማበረታታት ላይ የሚገኘውን የዮርዳኖስ ክርስቲያኖች ታሪክ በማስመልከት ከቫቲካን ዜና ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጆቫኒ በቃለ ምልልሳቸው፥ “መካከለኛውን ምስራቅ ያለ ክርስቲያኖች ተሳትፎ መካከለኛው ምስራቅ ማለት አይቻልም” ሲሉ ገልጸው፥ በዮርዳኖስ ውስጥ ለሚገኙት ማኅበረሰቦች ክርስቲያኖች ያበረከቱትን ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማስታወስ እንደሚገባ እና ይህ አስተዋጿቸው እንደሚቀጥልም አስረድተዋል።

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጆቫኒ ይህን ያስረዱት፥ በዮርዳኖስ ያለውን ታሪካዊ እና የረጅም ጊዜ የክርስቲያኖች መገኘት በማስታወስ በአማን ከሚገኘው የቫቲካን ዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ነው። “በዮርዳኖስ የኢየሱስ ክርስቶስ መገኘት የተረጋገጠባቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቦታዎች ብቻ ሳይሆኑ የመጀመሪያዎቹ የክርስቲያን ማኅበረሰቦች እንደ ነበሩበት የምናይባቸው ቦታዎችም አሉን” ሲሉ አስረድተዋል። ከዜና አገልግሎቱ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉት፥ “ዮርዳኖስ የክርስትና እምነት ጎህ” በሚል ርዕሥ የተዘጋጀውን ዐውደ ርዕዩ ከከፈቱ በኋላ እንደ ነበር ታውቋል።

“ዮርዳኖስ የክርስትና እምነት ጎህ” የሚለው የዐውደ ርዕዩ ርዕሥ ስለ ዮርዳኖስ ክርስቲያኖች የሚያስረዳ መሆኑን የተናገሩት አቡነ ጆቫኒ፥ በዮርዳኖስ የኢየሱስ ክርስቶስ መገኘት የተረጋገጠባቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቦታዎች ብቻ ሳይሆኑ የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያን ማኅበረሰቦች እንደኖሩበት የምናይባቸው ሥፍራዎችም መኖራቸውን ገልጸው፥ ካለፉት ክፍለ ዘመናት ጀምሮ ዮርዳኖስ ውስጥ ክርስቲያን ማኅበረሰቦች በቀጣይነት እንደሚኖሩ አስረድተዋል።

“ዐውደ ርዕዩም ይህን ሃቅ በትክክል ማጉላት ይፈልጋል” ያሉት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጆቫኒ፥ በተለይ ዮርዳኖስ ይህን ያህል ሃብት እንዳላት ማወቁ፣ በዮርዳኖስ የሚገኙ ክርስቲያን ማኅበረሰቦች እንደ ሌሎች ሃይማኖቶች ሁሉ የመካከለኛው ምስራቅ እና የአረቡ ዓለም ባህል አካል መሆናቸውን ማወቁ በተለይም ለምዕራቡ ዓለም አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረው፥ “ይህ ዐውደ ርዕይ ምዕራባውያኑ የመካከለኛው ምስራቅ ተፈጥሮ እና ታሪክ ምን እንደሚመስል በሚገባ እንዲገነዘቡ ይረዳል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ” ብለዋል።

“በእርግጥ ጦርነቱ ያስከተሏቸው አንዳንድ መዘዞች አሉን” ያሉት አቡነ ጆቫኒ፥ በተለይም በርካታ ፍልስጤማውያን በዮርዳኖስ እንደሚኖሩ ገልጸው፥ የብዙዎቹ ዘመዶች በዮርዳኖስ ማዶ እንደሚገኙ አስረድተዋል። ፍልስጤማውያኑ ጦርነቱ እጅግ እንዳሳዘናቸው ገልጸው፥ “እያንዳንዱ ጦርነት አሳዛኝ ቢሆንም ነገር ግን እርስ በርስ መቀራረቡ ይህን አሳዛኝ ሁኔታ እንድንለማመድ ያስችለናል” ብለዋል።

ሰላም ቶሎ እንደሚመጣ ተስፋ እንደሚያደርጉ ገልጸው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የሰላምን አስፈላጊነት በማስመልከት ባደረጉት ንግግር፥ “በቀጣናው ሰላምን ለማስፈን መወያየት አስፈላጊ ነው” ማለታቸውን አስታውሰዋል። እነዚህ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ቃላት እጅግ የተደነቁ እና በእርግጠኝነትም በመካከለኛው ምስራቅ በተለይም በዮርዳኖስ መንግሥት ተጽእኖ እንዳለው ተናግረው፥ የቅዱስነታቸው መልዕክት በብዙዎች ዘንድ ተደማጭነትን አግኝቶ ሰላምን በቅርቡ እንደሚያስገኝ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

የቅድስት መንበር ዋና ጸሐፊ ብጹዕ ካርዲናል ፒየትሮ ፓሮሊን በሐዋርያዊ ጉብኝታቸው በዮርዳኖስ ወንዝ ምሥራቃዊ ዳርቻ የታነጸውን አዲሱን የኢየሱስ ጥምቀት ቤተ ክርስቲያን ለመባረክ ተሰይመው መምጣታቸው የቦታውን አስፈላጊነት የሚያጎላ፣ እያንዳንዳችን ጥምቀታችንን እንድናስታውስ ከማድረጉ በተጨማሪ ቤተ ክርስቲያን ለምዕመናኖቿ ያላትን ጥልቅ ፍቅር የሚገልጽ፣ በዮርዳኖስ የምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን እና በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ ክርስቲያኖች በሙሉ ብቻቸውን አለመሆናቸውን የሚገልጽ የወዳጅነት ምልክት በመሆኑ እጅግ አስፈላጊ እንደ ሆነ አስባለሁ” ብለዋል።

“በመካከለኛው ምሥራቅ አገራት የሚገኙ ክርስቲያኖች ብቻቸውን አይደሉም” ያሉት አቡነ ጆቫኒ፥ቅድስት መንበር በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ ክርስቲያን ማኅበረሰቦችን እንደምታስባቸው ተናግረው፥ መካከለኛው ምስራቅ ያለ ክርስቲያኖች ተሳትፎ መካከለኛው ምስራቅ ሊባል እንደማይችል በማስረዳት፥ ክርስቲያኖች በዮርዳኖስ ላሉ ማኅበረሰቦች ያበረከቱት አስተዋጽዖ ትልቅ መሆኑን ማስታወስ እንደሚገባ እና ይህ አስተዋጽኦቸው የሚቀጥል መሆኑን አስረድተዋል።

ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጆቫኒ፥ “ለምሳሌ ክርስቲያን ያልሆኑ ተማሪዎች ወደ ክርስቲያን ትምህርት ቤቶች በተለይም ወደ ካቶሊክ ትምህርት ቤቶች እንደሚሄዱ ካሰብን ይህም ቤተ ክርስቲያን ለኅብረተሰቡ የምታበረክተው አስተዋፅኦ ቀጣይነትን የሚያሳይ እና ዓለም አቀፋዊት ቤተ ክርስቲያን በመካከለኛው ምስራቅ ያላትን ሚና መገንዘብ አስፈላጊ የሆነበትም ለዚህ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

“ዮርዳኖስ እንግዳ ተቀባይ አገር ናት” ያሉት አቡነ ጆቫኒ፥ በርካታ ምዕመናን በኢዮቤልዩ ቅዱስ ዓመት ውስጥ የሚጎበኟት አገር እንደምትሆን እና ቅዱሳን ቦታዎችን መጎብኘት እምነትን ሊያድስ እንደሚችል፣ ይህም ደግሞ የቅዱስ ዓመት ዓላማ እንደሆነ እና እምነታችንን ለማደስ ጥሩ ከሆኑት መንገዶች መካከል አንዱ እምነት ከተወለደባቸው ቦታዎች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ማድረግ እንደሆነ በዮርዳኖስ የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ እንደራሴ የሆኑት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ጆቫኒ ፒየትሮ ዳል ቶሶ አስረድተዋል።

 

09 January 2025, 13:32