“ሁለት ሕዝቦች እና ሁለት መንግሥታት” የሚለው የርዕሣነ ሊቃነ ጳጳሳት እና የቅድስት መንበር አቋም እንደማያጥፍ ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
“ሁለት መንግሥታት” የሚለው የመፍትሔ ሃሳብ በእስራኤል እና በፍልስጤም መካከል ሰላምን ለማውረድ ብቸኛው መንገድ ሆኖ ቆይቷል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቢተካኩም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከጥቅምት 7/2023 ጀምሮ ዓ. ም. በመካከለኛው ምሥራቅ ዓመፅ እና መለያየት በከፍተኛ ሁኔታ እየተባባሰ መጥቷል። ሆኖም ለሰማንያ ዓመታት ያህል የቅድስት መንበር ዲፕሎማሲያዊ አቋም የማይናወጥ ሆኖ ቆይቷል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በካስቴል ጋንዶልፎ ከምዕመናን ጋር ሆነው የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ባቀረቡበት ወቅት ባደረጉት ንግግር፥ “ሁለት መንግሥታት” የሚለው ፍትህን እና ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ የሚችል ብቸኛ የመፍትሄ ሃሳብ ነው። ይህን ሃሳብ የእስራኤል መንግሥት ውድቅ ቢያደርገውም፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ላለፉት አሥርት ዓመታት ጸንቶ የቆየውን ይህንን የቅድስት መንበር ታሪካዊ አቋም በድጋሚ የሚያረጋግጡ የቅርብ ጊዜ ሐዋርያዊ መሪ ናቸው።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በካስቴል ጋንዶልፎ ባደረጉት ንግግር፥ በዌስት ባንክ በፍልስጤማውያን ላይ የደረሰውን በደል እና ጥቃት ካወገዙ በኋላ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1947 ዓ. ም. በተካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የቀረበው ‘ሁለት መንግሥታት’ የሚለውን የመፍትሄ ሃሳብ እውን በማድረግ ፍትሃዊ እና ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት እንዲነሳሳ እጠይቃለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።
በጽኑ የተመሠረተ የዲፕሎማሲ አቋም
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1947 ዓ. ም. የኢየሩሳሌምን ቅዱስ ሥፍራዎች ዓለም አቀፍ ለማድረግ ጥሪ ከቀረበበት ጊዜ ጀምሮ ‘ሁለት መንግሥታት’ የሚለው የመፍትሄ ሃሳብ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ1980ዎቹ ጀምሮ ቅድስት መንበር በእስራኤል እና በፍልስጤም ግጭት ላይ ለነበራት ዲፕሎማሲያዊ አቋም ጽኑ መሠረት ሆኖ ቆይቷል። ይህ አቋም በተደጋጋሚ ለሚከሰቱ ግጭቶች በሚሰጡ ስሜታዊ ምላሾች ላይ የተቀረፀ ሳይሆን በታሪክ ውስጥ በጥብቅ የተመሠረተ እና በተከታታይ ርዕሣነ ሊቃነ ጳጳሳት የተጠናከረ እንደሆነ ታውቋል።
ር. ሊ. ጳ ፒዮስ 12ኛ ቅዱሳን ሥፍራዎችን እንዲጠበቁ የቀረቡት ጥሪ
የቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1948 ዓ. ም. “በርካታ እንክብካቤዎች” በሚለው ሐዋርያዊ መልዕክታቸው “እያንዳንዱ ወገን ግጭትን በተመለከተ የሕልውናን ደህንነት የሚያረጋግጥ እና እንደዚሁም ለመንፈሳዊ እና ቁሳዊ ደህንነት ምቹ የሆኑ የሕይወት ሥነ-ምግባራዊ እና አካላዊ ሁኔታዎች ምላሽ እንዲሰጥ” ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1949 ዓ. ም. ባወጡት “የቤዛችን መከራ” የተሰኘ ቀጣይ ሐዋርያዊ መልዕክታቸው፥ ከአዳኛችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወት ጋር የተያያዙት ቅዱስ ቦታዎች የጦርነት ውድመት ሊደርስባቸው እንደሚችል በማሰብ፥ ምእመናን ሕጋዊ መንገዶችን በሙሉ በመጠቀም የዓለም መሪዎች ለኢየሩሳሌም እና አካባቢዋ “ሕጋዊ ስልጣን” እንዲሰጡ ማሳመን እንደሚገባ አሳስበው፥ ይህም ሰላም ወዳድ አገራት በተባበረ ጥረት በቂ ዋስትናን ሊሰጧቸው እንደሚችሉ ተናግረዋል።
ር. ሊ. ጳ ጳውሎስ 6ኛ እና የፍልስጤማውያን ሕጋዊ መብቶች
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1964 ዓ. ም. ወደ ቅድስት ምድር የተጓዙት የመጀመሪያው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ፣ በ1967 ዓ. ም. በተካሄደው የስድስት ቀናት ጦርነት ዋዜማ የፍልስጤም ህዝብን ሕጋዊ መብቶች በግልጽ ተናግረው፥ ጉዳዩን ከሰብዓዊ አደጋነት ወደ መሠረታዊ የፖለቲካ ጥያቄነት መቀየራቸው ይታወሳል።
በወቅቱ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ ለነበሩት ዩ ታንት በላኩት መልዕክት፥ “ኢየሩሳሌም በተለይም በቅድስናዋ ምክንያት ለሁሉም ክፍት እና የማትደፈር ከተማ” እንድትባል፣ ከወታደራዊ ሥራዎች ነፃ እንድትሆን እና ከጦርነት መዘዞች መታደጓን ለማረጋገጥ ጥረት እንዲደረግ በመላው የክርስትና ዓለም ስም ጥሪ አቅርበዋል።
የር. ሊ. ጳ. ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ወሳኝ ተነሳሽነት
ይሁን እንጂ ፍልስጤማውያን ነፃ አገር የመሆን መብታቸውን እንዲጠይቁ የመጀመሪያው ወሳኝ ተነሳሽነት የመጣው ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ሲሆን፥ እንደዚሁም የእስራኤልን በደህንነት የመኖር መብቷን አረጋግጠዋል። ይህ ሁለትዮሽ ጥሪ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1984 ዓ. ም. ይፋ ባደረጉት “የቤዛነት ዓመት” በተሰኘ ሐዋርያዊ መልዕክት ላይ ተገልጿል።
ር. ሊ. ጳ. ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በመልዕክታቸው፥ “በእስራኤል ግዛት ውስጥ ለሚኖሩ እና በዚያች ምድር ታሪካቸውን እና እምነታቸው በእንደዚህ ዓይነት ውድ ምስክርነቶች ለሚጠብቁ የአይሁድ ሕዝቦች የሚፈለገውን ደህንነት እና ለእያንዳንዱ ሀገር እና ለእያንዳንዱ ማኅበረሰብ የሕይወት ሁኔታ እና የዕድገት መብት የሆነውን ተገቢውን ሰላም መጠየቅ አለብን” ብለዋል።
“በዚያች ምድር ታሪካዊ መሠረታቸውን የሚያገኙት እና ለብዙ አሥርት ዓመታት ተበታትኖ የቆየው የፍልስጤም ህዝብ እንደገና የትውልድ አገሩን የማግኘት እና ከሌሎች አካባቢ ሕዝቦች ጋር በሰላም እና በመረጋጋት የመኖር ተፈጥሯዊ መብት አላቸው” ሲሉ አክለዋል።
ር. ሊ. ጳ. ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በ2000 (እአአ) በቅድስት ምድር ሐዋርያዊ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት የመጀመሪያው ሳይሆኑ በአስፈላጊነቱ የተነሳ “ታሪካዊ” ተብሎ የተመሰከረለትን ተመሳሳይ መልዕክት ደግመዋል።
የር. ሊ. ጳ ቤኔዲክቶስ 16ኛ ድጋፍ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክቶስ 16ኛ ከዘጠኝ ዓመታት በኋላ ማለትም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በግንቦት ወር 2009 ዓ. ም. ወደ ቅድስት ምድር በመጓዝ በጦርነት የተጎዳችውን የኢየሱስ ክርስቶስ የትውልድ ምድር ጎብኝተዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክቶስ 16ኛ የቀደመውን ፈለግ በመከተል፥ “ሁለት መንግሥታት” የሚለው የመፍትሄ ሃሳብ የምኞት ራዕይ ሳይሆን የዓመፅን ሽክርክሪት ለማስቆም እና የክልሉን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ለማረጋገጥ አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታ መሆኑን አፅንዖት ሰጥተዋል።
“ቅድስት መንበር ሕዝባችሁ በአባቶቻችሁ ምድር ከጎረቤቶቿ ጋር ደህንነቱ የተጠበቀ እና በሰላም አብሮ የሚኖር፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚታወቁ ድንበሮች ውስጥ ሉዓላዊ የፍልስጤም አገር የመሆን መብታቸውን ትደግፋለች” ሲሉ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክቶስ 16ኛ ተናግረዋል።
ፍልስጤማውያን “የተስፋ ነበልባል ሕያው ሆኖ እንዲቀጥል፣ የእስራኤላውያንን ሆነ የፍልስጤማውያንን የሰላም እና የመረጋጋት ትክክለኛ ምኞቶች ለማሳካት መንገድ እንንደሚገኝ ተስፋ እንዲያደርጉ” በማለት አሳስበዋል።
የር. ሊ. ጳ ሊዮ 14ኛ አቤቱታዎች
ይህ ታሪካዊ ቅርስ አሁን በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እጅ ውስጥ የሚገኝ እና ከመጀመሪያውም ጀምሮ “ሁለት መንግሥታት” የሚለውን ዓለም አቀፍ የክርክር ማዕቀፍ ማዕከል አድርገውታል።
በተለይ ከኢስታንቡል ወደ ቤሩት ባደረጉት ሐዋርያዊ ጉዞ ወቅት ባደረጉት ንግግር፥ “ቅድስት መንበር ለብዙ ዓመታት “ሁለት መንግሥታት” የሚለውን የመፍትሔ ሃሳብ በይፋ ደግፋለች” ብለው፥ “በአሁኑ ጊዜ እስራኤል ይህንን መፍትሔ እንደማትቀበል ሁላችንም ብናውቅም ነገር ግን ሊያቀራርብ የሚችል ብቸኛው መፍትሔ እንደሆነ እና ለማያቋርጥ ግጭት መፍትሄ እንደሆነ እንረዳለን” ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በጥር 9/2026 ዓ. ም. ለዲፕሎማሲያዊ አባላት ባደረጉት ንግግር፥ “በተለይ ‘ሁለት መንግሥታት’ የሚለው የመፍትሔ ሃሳብ የሁለቱም ሕዝቦች ሕጋዊ ምኞቶችን ለማሟላት ተቋማዊ አመለካከት ሆኖ ይቀጥላል” በማለት ይህን አቋም በድጋሚ ገልጸውታል።
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እና የቀድሞዎቹ ርዕሣነ ሊቃነ ጳጳሳት አቤቱታዎች አሁንም ምላሽ እየጠበቁ ናቸው። ጦርነቱም ሕዝቦችን ማውደም ቀጥሏል። ወደ ሰላም የሚወስደው መንገድ እየጨመረ የመጣ ደመና ይመስላል። ሆኖም ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እና ለቅድስት መንበር የፖለቲካ አለመግባባት እና የሰብዓዊነት አሳዛኝ ሁኔታ መፍትሄውን የሚያፈርሱት አይደሉም። በተቃራኒው ምን ያህን አጣዳፊ እንደሆነ ያሳያሉ። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ኃላፊነቱን እንዲወስድ ጥሪ በማቅረብ አጣዳፊነቱንም አጉልተው ገልጸውታል።
