ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከማርሶዴቶ ፌዴሬሽን ቡድን አባላት ጋር በቫቲካን ሲገናኙ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከማርሶዴቶ ፌዴሬሽን ቡድን አባላት ጋር በቫቲካን ሲገናኙ   (@VATICAN MEDIA)

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ኢየሱስን በእያንዳንዱ ሰው ውስጥ ማግኘት እንደሚቻል አስገነዘቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በስፔይን የአእምሮ እና የጡንቻ ሕመም ያለባቸውን ሰዎችን የሚደግፍ መንግሥታዊ ካልሆነ የማርሶዴቶ ፌዴሬሽን ቡድን አባላት ጋር በቫቲካን ተገናኝተዋል። ቅዱስነታቸው ለቡድኑ አባላት ባደረጉት ንግግር “ኢየሱስ ክርስቶስን እጅግ ደካማ እና ተጋላጭ በሆኑ ሰዎች ሕይወት ውስጥ ማየት እንደ ሰብዓዊ እና ክርስቲያን ማኅበረሰብ እንድናድግ ያስችለናል” ሲሉ አስታውሰዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በስፔን ቶሌዶ ግዛት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1980 ዓ. ም. ተመሥርቶ የአእምሮ እና የጡንቻ ሕመም ያለባቸውን ሰዎች በመደገፍ ላይ የሚገኝ እና የተቋቋመትን 45ኛ ዓመት ዘንድሮ ለማክበር ወደ ሮም የተጓዙት የማርሶዴቶ ፌዴሬሽን አባላትን ነሐሴ 19/2018 ዓ. ም. ጠዋት በቫቲካን ተቀብለው አነጋግረዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለእንግዶቹ ባደረጉት ንግግር፥ “የፌዴሬሽኑ ሥራ ማንም የማያየው እና እግዚአብሔር ብቻ ሊሸልመው የሚችላቸውን በርካታ ሥራዎች ያካተተ ከባድ ሥራ ነው” ሲሉ አስረድተው፥ ሆኖም ሥራው በእያንዳንዱ ሰው ፊት ኢየሱስ ክርስቶስን በማግኘት በጥልቅ የሚደሰቱበት ተልዕኮ መሆኑን አፅንዖት ሰጥተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለማርሶዴቶ ፌዴሬሽን ተግባር የእመቤታችን ማርያም ዕርዳታን ተማጸኑ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለማርሶዴቶ ፌዴሬሽን ተግባር የእመቤታችን ማርያም ዕርዳታን ተማጸኑ   (@VATICAN MEDIA)

ቅዱስነታቸው በማቴ 25፡40 ላይ “እውነት እላችኋለሁ፤ ከሁሉ ለሚያንሱት ከእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ እንኳ ያደረጋችሁት ለእኔ እንዳደረጋችሁት ነው” የሚለውን በመጥቀስ፥ የማርሶዴቶ ፌዴሬሽን አባላት በሥራቸው አማካኝነት የወንጌል ምስክሮች መሆናቸውን ጠቁመው፥ “ይህም በሕመሙ ​​በተጎዱ ሰዎች ሕይወት ውስጥ እኛን የሚፈታተነን የኢየሱስ ክርስቶስን እይታ በመገንዘብ እንደ ሰብዓዊና ክርስቲያን ማኅበረሰብ እንድናድግ ይረዳናል” ብለዋል።

ድጋፍ የማይደረግለት ማንም የለም

“አንድነት፣ ሰብዓዊ ክብርን መከላከል እና በማኅበረሰብ ውስጥ ሙሉ በሙሉ መካተት” የሚሉት ፌዴሬሽኑ የአእምሮ እና የጡንቻ ሕመም ካለባቸው ሰዎች ጋር ለመሥራት ያለውን አካሄድ የሚያመለክቱ እሴቶች መሆቸው ታውቋል።

አባ ማርቼሊኖ ካሳስ ፑዌንቴ፥ “የአእምሮ ችግር ያለበት ሰው ያለ ድጋፍ መቅረት የለበትም” በማለት ከ40 ዓመታት በፊት የመሠረቱት የማርሶዴቶ ፌዴሬሽን ሕልማቸውን እውን ማድረግ መጀመሩ ይታወሳል።

ፌዴሬሽኑ ባሁኑ ጊዜ ከ2,600 የሚበልጡ ሰዎችን በማገልገል ላይ የሚገኝ ሲሆን፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ዘንድሮ ሰኔ ወር ላይ በስፔን ሐዋርያዊ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት የጠቀሱትን መልዕክት ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ታውቋል።

ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው፥ “የክርስቶስን ፍቅር ለወንድሞቻችን እና ለእህቶቻችን ማሳየት ግድ ይለናል (2ኛ ቆሮ 5፡14)። ለእነርሱ ፍላጎት ምላሽ የምንሰጥበት ልግስና እና እንክብካቤ የእምነታችን ማረጋገጫ ነው” ማለታቸው ይታወሳል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለማርሶዴቶ ፌዴሬሽን አባላት ያስተላለፉትን መልዕክት ሲያጠቃልሉ፥ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ጥበቃን በመለመን፥ በቀጣይ ሥራቸው ከቡድኑ ጋር አብራቸው እንድትጓዝ ተማጽነዋል።

“እመቤታችን ቅድስት ማርያም በችግር ጊዜ ታበረታችሁ፣ ትኩረታችሁን ዘወትር በእግዚአብሔር ላይ ለማድረግ እና ፌዴሬሽናችሁ ለቤተ ክርስቲያንም ሆነ ለኅብረተሰቡ እውነተኛ ምሳሌ ሆኖ ለመቀጥል ትርዳችሁ” በማለት የእግዚአብሔርን ቡራኬ ተመኝተውላቸዋል።

 

25 Aug 2026, 15:32