ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ለኮሎምቦስ ፈረሰኞች፣ በመለያየት ዘመን የስምምነት ነቢያት ሁኑ ማለታቸው ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ክፍፍል እየጨመረ በመጣበት ዓለም ውስጥ ድልድዮችን በመገንባት እና እርቅን በማስፋፋት “የስምምነት ነቢያት” እንዲሆኑ አበረታተዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በዴንቨር፣ ኮሎራዶ ሐምሌ 28/2018 ዓ.ም በተካሄደው የ144ኛው የጠቅላይ ጉባኤ ላይ ለተሳታፊዎች በቪዲዮ ባስተላለፉት መልእክት ጥሪ አቅርበዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በአካል እና ምናባዊ በሆነ መልኩ በዌብናር መንገድ ለተገኙት ሰዎች ሰላምታ ሲያቀርቡ፣ በስብሰባው ላይ “በእርሱ በአንዱ፣ አንድ ነን” በሚል ጭብጥ እና ስለ አንድነት እና ስለ በጎ አድራጎት ተግባራት፣ ስለ ኮሎምበስ ፈረሰኞች ማሕበር ሁለት መሠረታዊ መርሆዎች ተናግረዋል።
አንድነት ማዳበር አለበት
በመጨረሻው እራት ላይ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ “ሁሉም አንድ ይሆኑ ዘንድ” የሚለውን የኢየሱስን ጸሎት በማስታወስ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ አንድነት ለእያንዳንዱ ትውልድ አማኞች የተሰጠ ስጦታ መሆኑን አፅንዖት ሰጥተው ገልጸዋል።
“አንድነትን መጠበቅ ብዙውን ጊዜ ቀላል አይደለም፣ እና እንደ ቀላል ነገር ሊወሰድ አይችልም” ብለዋል። “በሐቀኛ እና በትህትና ውይይት በንቃት መዳበር አለበት” ሲሉ አክለው የተናገሩት ሲሆን ስለዚህ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ የኮሎንቦስ ፈረሰኞች ማሕበር ክርስቶስ የሚፈልገውን ስምምነት እንዲመሰክሩ አበረታተዋል፣ ከቤተሰቦቻቸውና ከደብራቸው ጀምሮ እስከ ሰፋፊ ማህበረሰቦች ድረስ ሲሉ አክልው ገልጸዋል።
“መከፋፈል በግልጽ በሚነገርበት በዚህ ዘመን፣ ድልድይ ለመገንባት እና በተቻለ መጠን ተቃራኒ አቋሞችን ለማስታረቅ የሚጥሩ የስምምነት ነቢያት በጣም ያስፈልጋሉ” ብለዋል።
የበጎ አድራጎት ኅብረትን ያጠናክራል
ቅዱስ አባታችን ወደ በጎ አድራጎትነት ሐሳብ ሲመለሱ፣ ለተቸገሩ ሰዎች የሚደረጉ ሥራዎች እራሳቸው ወደ አንድነት መንገድ ሊወስዱ እንደሚችሉ ተናግረዋል።
“የተቸገሩትን ለመርዳት ስንመጣ፣ በሚሰጡ እና በሚቀበሉት መካከል እንዲሁም ወንድሞቻቸውን እና እህቶቻቸውን ለመርዳት አብረው በሚሠሩት መካከል የተወሰነ ስምምነት በተደጋጋሚ ይፈጠራል” ብለዋል።
“ስለዚህ፣ በጎነት ለሰው ልጅ ስቃይ ምላሽ ብቻ ሳይሆን ወንድማማችነትን ማጎልበት እና የክርስቲያን ሕይወት እምብርት የሆነውን ኅብረት ለማጠናከር ኃይለኛ መንገድም ይሆናል” ብለዋል።
ዳር ላይ ያሉ ሰዎችን ማገልገል
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በመስራቻቸው ብፁዕ ሚካኤል ማክጊቭኒ የተጀመረውን ተልእኮ ስለቀጠሉ የኮሎምቦስ ፈረሰኞች ማሕበርን አመስግነዋል።
ከአንድ ምዕተ ዓመት በላይ ሆኖታል፣ ማሕበሩ የክርስቶስን ፍቅር “በማሕጸን ውስጥ ላሉ፣ ለነፍሰ ጡር እናቶች፣ ለስደት ለተጋለጡ ክርስቲያኖች፣ ለጦርነትና ለሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ሰለባዎች፣ ለድሆችና ለአደጋ የተጋለጡ እና በኅብረተሰቡ ዳርቻ ላይ ለሚኖሩ” ለማሳየት ሲሠራ ቆይቷል ብለዋል።
በአካባቢ ምክር ቤቶች፣ በአገር አቀፍ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ በተደረጉ ተነሳሽነቶች፣ “ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሰዎች ከማሕበሩ ልግስና ተጠቃሚ ሆነዋል” ሲሉ አክለው ተናግረዋል።
“በእኔ በኩል፣ ማሕበሩ ዕድለ ቢስ ለሆኑት ቀጣይነት ላለው ልግስና ጥልቅ ምስጋናዬን እገልጻለሁ፣ እና ጥረቶችዎ ለብዙ ዓመታት ፍሬ ማፍራታቸውን እንደሚቀጥሉ እተማመናለሁ” ብለዋል ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ።
መልእክታቸውን ሲያጠናቅቁ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ የቤተክርስቲያኗ እናት ማርያም እና የብፁዕ ሚካኤል ማክጊቭኒ አማላጅነት እንዲያጅባቸው አደራ ሰጥተዋል፣ ለሁሉም የኮሎምቦስ ፈረሰኞች ማሕበር አባላት እና ቤተሰቦቻቸው ሐዋርያዊ ቡራኬያቸውን ከሰጡ በኋላ ቅዱስነታቸው መልእክታቸውን አጠናቀዋል።
