ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ “በከተሞች ወንጌልን ማሰራጨት” የሚል የጸሎት ሃሳብ ይፋ አደረጉ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “በከተሞች ወንጌልን ማሰራጨት” በሚለው የነሐሴ ወር የጸሎት ሃሳባቸው መላው ካቶሊካውያን እንዲተባበሩ ያቀረቡት ማሳሰቢያ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዓለም አቀፍ የጸሎት አውታረ መረብ የተዘጋጀ እና “ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር አብረን እንጸልይ” በተሰኘ ወርሃዊ የቪዲዮ መልዕክት ይፋ ሆኗል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ “በጎዳናዎቻችን፣ በአደባባዮቻችን እና በሠፈሮቻችን ጭምር አብሮን የሚጓዘው መልካሙ እረኛ ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ረጃጅም ሕንፃዎች እና መንደሮች እንዲገባ፣ በጩኸት እና በጥድፊያ መካከል የሕይወት ትርጉም ከሚፈልጉ በሚሊዮን ከሚቆጠሩ ሰዎች ጋር እንዲሆን” በማለት በጸሎት ጠይቀዋል።
ከተሞች የነጻነት እና የዕድል ቦታዎች ቢሆኑም የጥርጣሬ እና የመገለል ቦታዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ተናግረው፥ ከተሞች ወንጌል ሊታውጅ የሚችልባቸው ምቹ ቦታዎች እንደሚሆኑ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
ቅዱስነታቸው ምእመናን ቀለል ያሉ የፍቅር እና የቸርነት ምልክቶችን እንዲያሳዩ እንዲሁም ወደ ፊት በመጓዝ ግዴለሽነትን እና መገለልን በወንድማማችነት የሚዋጋ ማኅበረሰብ ሆነው አብረው እንዲሠሩ ጸሎት አቅርበዋል።
ዛሬ ከዓለም ሕዝብ መካከል ወደ 45% የሚሆነው በከተሞች እንደሚኖር የሚገመት ሲሆን ይህም የብዙ ሰዎች የአእምሮ ጤናን በተለይም ወጣቶችን የሚጎዳ ብቸኝነትን ጨምሮ ማኅበረሰባዊ ፈተናዎችን በማስከትል የሥነ-ሕዝብ ዕድገት ከፍተኛ ትኩረት ሆኗል።
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዓለም አቀፍ የጸሎት አውታረ መረብ
የጸሎት ሐዋርያነት ሆኖ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1844 ዓ. ም. የተመሠረተው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዓለም አቀፍ የጸሎት ኔትወርክ ለኢየሱሳውያን ማኅበር በአደራ የተሰጠ ጳጳሳዊ አገልግሎት ነው።
ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይህን ጳጳሳዊ አገልግሎት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በታኅሳስ ወር 2020 ዓ. ም. ከቫቲካን ፋውንዴሽኖች አንዱ በማድረግ የመጨረሻ ደንቦቹን በሐምሌ ወር 2024 ዓ. ም. ማጽደቃቸው ይታወሳል።
ባሁኑ ወቅት በ92 አገራት ውስጥ የሚገኘው ይህ የጸሎት ኔትወርክ በየቀኑ ለእግዚአብሔር ተልዕኮ ራሳቸውን አዘጋጅተው ለመኖር የሚፈልጉ ከ22 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ያቀፈ መንፈሳዊ ማኅበር ነው።
የተልዕኮው ዋና ማዕከል የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ወርሃዊ የጸሎት ሃሳብ ሲሆን፥ ማኅበሩ የሰው ልጅን በሚያጋጥሙት አጣዳፊ ችግሮች እና በቤተ ክርስቲያኗ ተልዕኮ ውስጥ እንዲያተኩሩ አባላቱን ይጋብዛል።
