ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ የእግዚአብሔርን ጥሪ በማዳመጥ በቁርጠኝነት ሊከተሉት እንደሚገባ አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
“ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር መገናኘት ልብን በደስታ በመሙላት የፍቅሩ እና የምሕረቱ ምስክሮች እንድንሆን ጥንካሬ ይሰጠናል” ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “አይዟችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ” (ዮሐንስ 16:33) በሚል መሪ ቃል ቅዳሜ እና እሁድ ኤኳዶር ውስጥ በኢባራ ከተማ ለተካሄደው 7ኛ ብሔራዊ የወጣቶች ቀን ተሳታፊዎች የቪዲዮ መልዕክት በመላክ የሚያጽናና ማሳሰቢያ አቅርበዋል።
ለጥሪው ምላሽ መስጠት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለወጣቶች በላኩት መልዕክት ኢየሱስ ክርስቶስ ለሕይወታቸው ትርጉም እንደሚሰጥ አስረድተው፥ “የእግዚአብሔርን ጥሪ እንድትሰሙ እና በቆራጥነት እንድትከተሉ አበረታታችኋለሁ” ብለው፥ ወጣቶች የቤተ ክርስቲያን ውድ ልጆች እንደሆኑ አስታውሰዋል።
በደስታ ሌሎችን ወደ ክርስቶስ መጥራት
ሌሎች በርካቶች ክርስቶስን እንዲያውቁ ለማድረግ ቤተ ክርስቲያን የወጣቶችን ደስታ፣ ድፍረት እና ምስክርነት ትፈልጋለች” ብለው፥ በፍቅሩ እንድትለወጡ ራሳችሁን ፍቀዱ” ሲሉ አክለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በመጨረሻም ወጣቶች የይቅርታ፣ የእርቅ እና የሰላም አራማጆች እንዲሆኑ ጥሪ በማቅረብ፥ የኢኳዶርን ወጣቶች ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አደራ ሰጥተዋል።
“እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወንጌልን በተግባር እንድትኖሩ እና እግዚአብሔር ለሕይወታችሁ ላለው እቅድ ራሳችሁን ለማስገዛት የምታነሳሳ ምሳሌ ትሁን” ሲሉ ጸሎታቸውን አቅርበዋል።
