ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በስፔይን ሴውታ ከተማ ያለው አስደንጋጭ ሁኔታ እንዳሳስባቸው ገለጹ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
በስፔኗ ራስ ገዝ ከተማ ሴውታ ውስጥ ያለው አስደንጋጭ የስደተኞች ሁኔታ ያሳስበኛል” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በአፍሪካ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት ከእግዚአብሔር ዘንድ የሰላም፣ የመረጋጋት እና የፍትህ መፍትሄዎች እንዲገኙ ጸሎታቸውን አቅርበዋል።
ቅዱስነታቸው በስፓኒሽ ቋንቋ ተማጽኖአቸውን ያቀረቡት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር የብስራተ ገብርኤል ጸሎት ካደረሱ በኋላ ሲሆን፥ በሰሜን አፍሪካ የባሕር ዳርቻ ከሞሮኮ ጋር የምትዋሰነው የስፔን ራስ ገዝ ሴውታ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች የሚገኙባት ከተማ እንደሆነች ይታወቃል።
በቅርብ ቀናት ውስጥ ብቻ ከሞሮኮ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ወደ ግዛቲቱ ለመግባት የሞከሩ ሲሆን፥ ይህም እጅግ ብዙ የስደተኞች መቀበያ ጣቢያዎች እንዲገነቡ እና ስፔንም ተጨማሪ የጸጥታ ሃይሎችን እንድታሰማራ ማድረጉ ታውቋል።
ባሕርን ለመሻገር በተደረጉ አስቸጋሪ እና አደገኛ ሙከራዎች በትንሹ የ67 ሰዎች ሕይወት ጠፍቷል። ሮይተርስ የዜና ምንጭ በዘገባው አብዛኞቹ ተጎጂዎች በባሕር ውስጥ ሰጥመው እንደቀሩ ወይም ሲያቋርጡ በድብቅ እንደተገደሉ አስታውቋል።
ጦርነቶች እንዲቆሙ የተደረገ ጸሎት
በጦርነት ምክንያት ስቃይ የሚደርስባቸውን ሰዎች ያስታወሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “በዓለም ዙሪያ የሚካሄዱ ጦርነቶች ቆመው ሰላም እንዲገኝ እና ለግጭቶችም ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄዎች እንዲገኙ የምናቀርበውን ጸሎት እንቀጥል” ሲሉ አሳስበዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በጦርነት የተጎዱትን በተለይም አቅመ ደካሞችን እና ራሳቸውን ከአደጋ መከላከል የማይችሉ ሕፃናትን፣ አረጋውያን እና ሕሙማንን በጸሎታቸው አስታውሰው፥ የሚሰቃዩትን እግዚአብሔር እንዲያጽናናቸው፣ ዕርዳታን የሚያቀርቡ ሰዎች ሥራን እንዲባርክ ጸልየዋል።
የአሲሲ ይቅርታ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በመጨረሻም በሳምንቱ መጨረሻ የሚከበረውን የአሲሲ የይቅርታ በዓል በማስታወስ ምእመናን ለዚህ ታላቅ መንፈሳዊ ስጦታ እግዚአብሔርን እንዲያመሰግኑ እና ስጦታውንም እንዲንከባከቡት አደራ ብለዋል።
“የአሲሲ ይቅርታ” ከአሲሲው ቅዱስ ፍራንችስኮስ ጋር የተቆራኘ ሙሉ የይቅርታ አገልግሎት ሲሆን ይህም በእርቅ እና በቅዱስ ቁርባን ምስጢራት እንዲሁም ቁምስናዎችን እና በፍራንችስካውያን የሚመሩ ቤተ ክርስቲያናትን በመጎብኘት፣ የሐዋርያት ጸሎተ ሃይማኖትን እና “አባታችን ሆይ!” ጸሎትን በመድገም፣ ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት እና ዓላማቸው በመጸለይ ሊገኝ የሚችል እንደሆነ ታውቋል።
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1216 ዓ. ም. የተጀመረው “የአሲሲ ይቅርታ” ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ቅድስት ድንግል ማርያም እና መላእክት ቅዱስ ፍራንችስኮስ በአሲሲ በገነባት ትንሿ የጸሎት ቤት ፊት በተገኙበት ወቅት እንደ ነበር ይታወሳል።
ቅዱስ ፍራንችስኮስ ለነፍሳት ድነት ምን እንደሚፈልግ ኢየሱስ በጠየቀው ጊዜ፥ ወደ ጸሎት ቤቷ ለሚገቡት ሙሉ ይቅርታ እንዲሰጣቸው ጠይቆት እንደ ነበር ሲታወስ በኋላም ነሐሴ 25 ወይም 26 ፍራንችስካዊ ቁምስናን የሚጎበኝ ማንኛውም ሰው የይቅርታ ስጦታን እንደሚያገኝ ታውቋል።
