ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ረሃብ በእውነት ያረካል” ሲሉ ገለጹ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እሑድ ሐምሌ 26/2018 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር የብስራተ ገብርኤል ጸሎት አድርሰዋል። በማቴ. 14: 13-21 ላይ በተጻፈው የእንጀራ እና የዓሣ ተዓምር ላይ በማስተንተን ባሰሙት ቃለ ምዕዳን፥ ኢየሱስ ክርስቶስን ማግኘት ገንቢ ተሞክሮ መሆኑን ለምእመናኑ አስረድተዋል።

ክቡራት እና ክቡራን፥ ከዚህ ቀጥሎ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለምዕመናን ያሰሙትን ቃለ-ምዕዳን ትርጉም ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን፥

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞቼ እህቶቼ፥ መልካም እሑድ ይሁንላችሁ! ቅዱስ ወንጌል የሚነግረንን ስንሰማ ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ያለውን ልዩ ፍቅር እና ለዓለም በሙሉ የሚያመጣውን ድነት የሚያሳዩ ምልክቶችን እንዳደረገ ብዙ ጊዜ እንሰማለን። በዚህም ኢየሱስ ክርስቶስ ለሕይወታችን ትርጉም የሚሰጥ፣ ከክፋት እና ከኃጢአት የሚያድነን አምላክ ሆኖ መቅረቡን እንገነዘባለን።

ኢየሱስ ክርስቶስ የዕውራንን ዐይን ሲያበራ እና መስማት ለማይችሉት የመስማት ችሎታን ሲሰጥ፥ ተዓምራዊ ተግባራትን ከማድረግ የበለጠ ሲያደርግ እና የእግዚአብሔር መንግሥት ቅርብ መሆኑን ለሁሉም ሰው ማወጁን እናያለን። በዚህ መንገድ ከማቴ 14፡13-21 ተወስዶ የተነበበው የዛሬው ቅዱስ ወንጌል ኢየሱስ ክርስቶስ ሰዎችን የጎደሉ የስሜት ሕዋሳትን የሚመልስ ብቻ ሳይሆን ስሜቶቻችንንም በመልካም ነገሮች የሚሞላ መሆኑን ይመሰክራል።

ኢየሱስ ክርስቶስ መስማት የተሳነው ሰው ተፈውሶ የምሥራቹን ቃል እንዲሰማ አድርጓል። ማየት ለተሳነው ሰው የተደረገለትን አስደናቂ የቤዛነት ሥራ ያሳያል። እንደዚሁም ኢየሱስ ክርስቶስ ለተራቡት ሰዎች ምግብን ይሰጣል። የዳቦው መባዛት ታሪክ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር መገናኘት ገንቢ ተሞክሮ መሆኑን ያሳየናል። ምግብ በሌለበት ምድረ በዳ ላይ ኢየሱስ ክርስቶስ የሕይወት እንጀራ ነው። ከእርሱ ጋር ስንሆን ፍላጎቶቻችን በሚገባ ይሟላሉ። ‘ሁሉም በልተው ጠገቡ፤ የተረፈውንም ቁርስራሽ  አሥራ ሁለት መሶብ ሙሉ አነሱ’ (የማቴ. 14:20)። ይህ ቁጥር የጌታ ስጦታ ሁሉ አቀፍ መሆኑን እና ለእኛ ያለው የዕርዳታ እንክብካቤ ፈጽሞ የማያቋርጥ መሆኑን ያሳያል።

የተወደዳችሁ ምዕመናን ሆይ! ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ረሃብ፣ የእኛን የእውነት እና የሕይወት ረሃብ በእውነት ያረካል። የእርሱ ምሳሌ ከሌሎች ጋር ስንጋራ ምንም ነገር እንደማይጣል ያስተምረናል። ለግል ብቻ ማከማቸት ወይም ስግብግብነት እና ብክነት በተቃራኒው የአንድ ክፉ ሥራ ሁለት ገጽታዎች ናቸው። ይህ መንፈሳዊ ሕመም በሃብት ብዛት የሚሰክሩ ሰዎች ስሜት በማዳከም በረሃብ የሚያለቅሱትን እና በጥማት የሚጮኹ ሰዎችን እንዲረሱ ያደርጋል። ስለዚህ በከንቱ በሚጠፋ ሃብት ፊት ምግብን ለመለመን የተዘረጉ እጆችን፣ ሰላም በመጥፋቱ ምክንያት ቤቶቻቸው የተቃጠሉባቸውን ሰዎች  እናገኛለን።

ጦርነት እና ትዕቢት በበዛበት ዓለም ውስጥ ስንኖር ‘ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ሰማይ አሻቅቦ አየና እንጀራውንም ባርኮ ቈረሰው፤ ለሕዝቡ እንዲያከፋፍሉ ለደቀ መዛሙርቱ ሰጣቸው’ የሚለውን የደግነት ምሳሌን እናስብ (ማቴ. 14: 19)። በዚህ የበጎ አድራጎት ተዓምር፣ በመጨረሻው እራት ላይ ደረጃቸውን የሚያገኙ የኢየሱስ ክርስቶስን ባህሪያት እናያለን። ምክንያቱም የእግዚአብሔር ልጅ ወንድማችን ሆኖ ሕይወቱን የሰጠን በዚያን ጊዜ ነበር።

በቅዱስ ቁርባን ጸጋ እየተደሰትን ከቤተሰብ እና ከጓደኛ ጋር የቀረበልንን ማዕድ ጸልየን በመብላት በዕለት ተዕለት ተግባራችን ውስጥ ስለ ቅዱስ ቁርባን ውበት እንመስክር። ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር በመሆን ለተቸገሩ ጎረቤቶቻችን ዕርዳታ የምንስጥ ከሆነ የዕረፍት ጊዜያችን እንኳን የተረጋጋ የወንድማማችነት ጊዜ ሊሆን ይችላል።

ስለዚህ አፍቃሪ እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ማንም ሰው የዕለት እንጀራውን እንዳያጣ፤ እኛም በበጎ ሥራችን ለማደግ እንድትረዳን በጸሎት እንጠይቃት።”

03 Aug 2026, 16:42