ፈልግ

የጤና ባለሙያዎች የቫይሬስ ስርጭት መከላከያ መሣሪያዎችን ለብሰው የጤና ባለሙያዎች የቫይሬስ ስርጭት መከላከያ መሣሪያዎችን ለብሰው  (AFP or licensors)

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለኮንጎ የኢቦላ ሰለባዎች ዕርዳታ እንዲደረግላቸው ጥሪ አቀረቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በኮንጎ ዲሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ በኢቦላ ወረርሽኝ ለተጎዱ ሰዎች እና በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ በማዕድን ቁፋሮ አደጋ ለተጎዱ ሰዎች ዓለም አቀፍ ዕርዳታ እንዲደረግላቸው ጥሪ አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እሑድ ነሐሴ 17/2018 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር የብስራተ ገብርኤል ጸሎት ባደረሱበት ወቅት፥ በኮንጎ ዲሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ውስጥ በተከታታይ የኢቦላ ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰቱን አስታውሰዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ “በኮንጎ ዴሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ ውስጥ በኢቦላ ወረርሽኝ መስፋፋት ምክንያት ሕይወታቸውን ያጡትን ብዙ ጊዜ በጸሎቴ አስታውሳቸዋለሁ” ብለው፥ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለወረርሽኙ ምላሽ እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል።

“በርካታ የሰውን ሕይወት ለማዳን የአካባቢውን ማኅበረሰብ ጥረቶችን በማካተት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ምላሽ እንዲሰጥ አበረታታለሁ” ብለዋል።

በአሁኑ ጊዜ ምንም ዓይነት የተረጋገጠ ሕክምና ወይም ክትባት በሌለው የኢቦላ ቫይረስ መጠቃታቸው ከተረጋገጠባቸው 5,300 ሰዎች መካከል እስካሁን ከ2,500 በላይ ሰዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸው ታውቋል።

የዓለም ጤና ድርጅት (WHO) እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በግንቦት 2026 ዓ. ም. ባሰራጨው ዘገባ ወረርሽኙ በኮንጎ ዲሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ እና በኡጋንዳ መከሰቱን አስታውቋል።

የኮንጎ ዲሞክራሲያዊት ሪፐብሊክ የጤና ሚኒስትር፥ በአገሪቱ ውስጥ ለ16,000 ሰዎች የተሰጣቸው የኢርቬቦ ክትባት ሌሎች የኢቦላ ዝርያዎችን በማጥቃት ውጤታማ መሆኑን ተናግረዋል።

የቫይረሱን ስርጭት ለማስቆም የሚደረገው ጥረት በመንግሥት ኃይሎች እና ወረርሽኙ በተጠናከረባቸው ዋና ዋና ከተሞችን በሚቆጣጠሩት የታጠቁ ቡድኖች መካከል በተፈጠረ ግጭት ምክንያት መስተጓጎሉ ታውቋል።

በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ በማዕድን ቁፋሮ አደጋ ለተጎዱት የቀረበ ጸሎት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በሌላ በኩል በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ዛምቦዬ ውስጥ በወርቅ ማዕድን ቁፋሮ አደጋ የተጎዱትንም በጸሎታቸው አስታውሰዋል።

ቅዱስነታቸው በአደጋው ለተጎዱት ሰዎች በሙሉ ያላቸውን ቅርበት ገልጸው እግዚአብሔር ነፍሳቸውን  በምሕረቱ እንዲቀበል እና የማዕድን ማውጫ ቦታው ደህንነት እና ሕጋዊነት ለማረጋገጥ የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዝ” ጸሎታቸውን አቅርበዋል።

በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ዛምቦዬ የወርቅ ማዕድን ማውጫ ሥፍራ ነሐሴ 12/2018 ዓ. ም. በተከሰተው የመሬት መደርመስ ከ100 ሰዎች በላይ መሞታቸው ሲነገር ከክስተቱ አስቀድሞ ቦታው ተዘግቶ እንደ ነበር መንግሥት አስታውቋል።

 

 

 

 

24 Aug 2026, 15:48