ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ “በእርግጠኝነታችን ሳንመካ ለኢየሱስ ክርስቶስ ክፍት ልንሆን ይገባል” ሲሉ አሳሰቡ
ክቡራት እና ክቡራን፥ ከዚህ ቀጥሎ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለምዕመናን ያሰሙትን ቃለ-ምዕዳን ትርጉም ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን፥
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
“ውድ ወንድሞቼ እህቶቼ፥ መልካም ዕለተ ሰንበት ይሁንላችሁ! ከማቴ 16:13-20 ተወስዶ የተነበበው የዛሬው ቅዱስ ወንጌል ‘በእውነት ለእኔ ኢየሱስ ማነው?’ በሚል በእምነት ጉዞአችን ላይ እያንዳንዳችንን የሚያጋጥመን ጥያቄን ያቀርብልናል።
ይህ የወንጌል ክፍል ጥያቄ ለደቀ መዝሙርነት ተሞክሮ ምን ያህል ወሳኝ መሆኑን እንድንረዳ ያደርገናል። በእርግጥም አሥራ ሁለቱ ሐዋርያት የመምህራቸውን ሕይወትና አገልግሎት በብዙ መንገድ ቢካፈሉም ነገር ግን ኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያቱ የእግዚአብሔርን መንግሥት ምስጢር በእውነት እንደሚያውቁት ወይም እንደተረዱት አድርጎ አላሰበም። ስለዚህ ሰዎች ስለ እርሱ ምን እንደሚሉ ከጠየቃቸው በኋላ በቀጥታ ‘እናንተስ እኔን ማን ትሉኛላችሁ?’ ሲል ጠየቃቸው። (ማቴ 16:15)
ወንድሞች እና እህቶች፥ ይህ ለእያንዳንዱ ዘመን ደቀ መዛሙርት እና ለእያንዳንዳችን ጭምር መሠረታዊ ጥያቄ ነው። እምነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የተሰጠ ነገር አይደለም። ይልቁንም የኢየሱስ ክርስቶስን እና የወንጌሉን መልዕክት እንደገና ማግኘት አለብን። ወደ መልዕክቱ በጥልቀት በመግባት በሕይወታችን ውስጥ የምናደርጋቸውን ምርጫዎች ማደስ አለብን። በዚህም ከምንናገረው ነገር ጋር የሚጣጣሙ ይሆናሉ። በዚህ መንገድ ሁሉንም ነገር እናውቃለን ብለን እንድናስብ እና እምነትን ወደ ተራ ልማድነት እንድናሳንስ የሚያደርገንን ፈተና ማሸነፍ እንችላለን።
በየቀኑ ራሳችንን የምንጠይቀው ጥያቄ፥ ‘ለእኔ ኢየሱስ ማን ነው? በሕይወቴ ውስጥ የእርሱ መገኘት ምን ማለት ነው?’ የሚሉት በተለይ በጸሎት እና በወንጌል አስተንትኖ ወቅት የሚነሱ ጥያቄዎች ናቸው። ሆኖም የወንድሞቻችንን እና የእህቶቻችንን ቁስሎች እና ፍላጎቶች እንዲሁም ሕሊናችንን እጅግ በሚፈታተኑ ግንኙነቶች እና ሁኔታዎች ውስጥ በምንገኝበት ወቅት ጭምር ይነሳሉ። ባጭሩ በዕለት ተዕለት ሕይወታችን፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ጠቃሚ ነገሮችን የተናገረ እና ያደረገ ታላቅ የታሪክ ሰው መሆኑን ወይም እኛን ወደ አብ ፍቅር ለማምጣት እና ሕይወታችንን እና የምንኖርበትን ዓለም ለመለወጥ የተላከ መሆኑን ማወቅ እንችላለን።
ውድ ወንድሞች እና እህቶች! ከእምነታችን እና ሃይማኖታዊ እርግጠኝነት ለመውጣት ሳንሞክር ነገር ግን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ባለን እውነተኛ ግንኙነት ክፍት መሆንን እንቀጥል።
ወደ ክርስትና እምነት ሲመጣ አንዳንድ ጊዜ በሰማነው ነገር፣ በጋራ ግምቶች ወይም በተሰጠን ምስክርነት ምናልባትም በጥሩ ዓላማ ረክተን ልንኖር እንችላለን። ሆኖም ኢየሱስ ክርስቶስ የግል ምላሽ እንድንሰጥ፣ የበለጠ በቅርበት እንድናውቀው እና በአዲስ ገጠመኝ ከእርሱ ጋር በወዳጅነት እንድንኖር ይጠይቀናል። ይህ ደግሞ የማናውቃቸውን መንገዶች እንድንከተል እና ከገመትናቸው የተለዩ ምርጫዎችን እንድናደርግ ሊጠይቀን ይችላል።
ይህ በግል እና በቤተ ክርስቲያን ጉዞ፥ አንዳንድ ጊዜ እንደምናስበው እስከ ዛሬ የምናደርጋቸውን ነገሮች ማድረግ ብቻ በቂ እንደሆነ በምናስናስበው የሐዋርያዊ አገልግሎት ምርጫዎቻችንም ሊከሰት ይችላል። በምትኩ ኢየሱስ ክርስቶስ ማን ነው? በእውነት አውቀዋለሁ? ወንጌሉ ዛሬ ከእኔ ምን ይላል? ምን ዓይነት እርምጃዎችን እና ምርጫዎችን ለማድረግ ተጠርቻለሁ?” ብለን ራሳችንን አዘወትረን መጠየቅ ያስፈልጋል።
በልጇ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የእግዚአብሔርን ፈቃድ በልቧ ውስጥ የፈለገች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘወትር በእምነት መንገድ እንድትመራን እንጠይቃት።” በማለት ቅዱስነታቸው የዕለቱን ቃለ ም ዕዳን አጠቃልለዋል።
