ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፣ በህዳር ወር ኡራጓይ፣ አርጀንቲና እና ፔሩን እንደሚጎበኙ ተገለጸ!
የዚህ ዜና አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እ.አ.አ ከህዳር 6 እስከ ሕዳር 17/2026 ዓ.ም ወደ ኡራጓይ፣ አርጀንቲና እና ፔሩ ሐዋርያዊ ጉዞ እንደሚያደርጉ የቅድስት መንበር የፕሬስ ጽ/ቤት ዛሬ አስታውቋል።
ቅዱስ አባታችን እ.አ.አ ከህዳር 6 እስከ 8/2026 ዓ.ም ሞንቴቪዲኦ፣ ፔሳንዱ እና ፍሎሪዳ፤ እንዲሁም እ.አ.አ ከህዳር 8 እስከ 11/2026 ዓ.ም ቡዌኖስ አይረስ፣ ኮርዶባ እና ሉጃን እንዲሁም እ.አ.አ ከህዳር 11 እስከ 17/2026 ዓ.ም ሊማ፣ ቺክላዮ፣ ኩስኮ እና ፑካላፓ እንደሚጎበኙ ተገልጿል።
የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን 36% ብቻ የህዝብ ብዛት ያላት ኡራጓይ በመላው በላቲን አሜሪካ ዝቅተኛው የካቶሊኮች ቁጥር ያላት ሀገር ናት። ይህ በእንዲህ እንዳለ አርጀንቲና የቀድሞ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የትውልድ አገር ነበረች፣ ምንም እንኳን ከቡዌኖስ አይረስ የመጡት የቀድሞ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በ12 ዓመታት የጵጵስና ዘመናቸው የገዛ አገራቸውን ለመጎብኘት እንዳልቻሉ ይታወቃል።
ፔሩ፣ በመጨረሻም፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በደንብ የሚያውቁት አገር ናት - ለመጀመሪያ ጊዜ እ.አ.አ በ1980ዎቹ እንደ ሚስዮናዊ ሆነው ወደ እዚያው እንዳቀኑ የሚታወስ ሲሆን በኋላም እዚያ እንደ ጳጳስ ሆነው አገልግለዋል እና የፔሩ ዜግነት አግኝተዋል።
ይህ ወደ ላቲን አሜሪካ የሚደረገው ጉዞ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በአስራ አንድ ቀናት ውስጥ አስር ከተሞችን የሚጎበኙበት፣ ስድስተኛው ዓለም አቀፍ ጉዞቸው ይሆናል። የጉዞው መርሃ ግብር በጊዜው ይፋ ይደረጋል።
