ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ የፖርቱጋል ጦር ሠራዊት አባላትን በቫቲካን ሲቀበሉ ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ የፖርቱጋል ጦር ሠራዊት አባላትን በቫቲካን ሲቀበሉ  (@Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ የፖርቱጋል ጦር ሠራዊት ከጌታ ብርታትን በማግኘት ዜጎችን እንዲጠብቅ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከፖርቱጋል የጦር ሠራዊት አባላት ጋር ነሐሴ 18/2018 ዓ. ም. በቫቲካን ተገናኝተዋል። ቅዱነታቸው የጦር ሠራዊት አባላትን በቫቲካን ተቀብለው ባስተላለፉት መልዕክት፥ ከእግዚአብሔር ዘንድ በሚያገኙት ጥንካሬ በመበርታት ዜጎችን እንዲጠብቁ አሳስበው፥ በቅርቡ ያረፉትን ሁለት የፖርቱጋል ወታደሮችን በማስታወስ፥ ጦር ሠራዊቱ ትውልድ አገሩን፣ የሕግ የበላይነትን እና የዜጎቻቸውን ሕይወት እና ደህንነት እየጠበቁ በእግዚአብሔር ድጋፍ ጠንካሮች እንዲሆኑ አበረታተዋቸዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለፖርቱጋል የጦር ሠራዊት አባላት ባደረጉት ንግግር፣ ሰዎች ራሳቸውን መከላከል የማይችሉ መሆናቸውን በማወቅ ተልዕኳቸውን በትሕትና ለመወጣት ከእግዚአብሔር ዘንድ ጥንካሬን እንዲያገኙ አበረታተዋቸዋል።

“እያንዳንዳችሁ በየቀኑ የትውልድ አገራችሁን ሉዓላዊነት እና የሕግ የበላይነት የማስከበር፣ የዜጎቻችሁን ደህንነት የመጠበቅ እና ከኢፍትሃዊነት የመጠበቅ ክቡር ተልእኮ አላችሁ” ሲሉ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሰኞ ነሐሴ 18/2018 ዓ. ም. በቫቲካን ለተቀበሉት የፖርቱጋል የጦር ሠራዊት አባላት ቡድን ተናግረዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በፖርቱጋል ለሚገኙት የጦር ኃይሎች፣ የአየር ኃይል፣ የባሕር ኃይል፣ የብሔራዊ ሪፐብሊካን ጥበቃ እና የሕዝብ ደህንነት ፖሊስ አባላት፣ ክርስቲያን ሆኑ ክርስቲያን ላልሆኑት በሙሉ ሰላምታቸውን አቅርበዋል እንዲሁም ዓርብ ነሐሴ 15 ያረፉትን ሁለት ወጣት ወታደሮችን አስታውሰዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ወታደሮቹ “እንደ ደጉ ሳምራዊ ዕርዳታን ለመስጠት በመንገድ ላይ ቆመው ሕይወታቸውን አጥተዋል” ሲሉ ተናግረው አክለውም እነሱንም ሆነ ቤተሰቦቻቸውን ለእግዚአብሔር አደራ ሰጥተዋል። ሁለቱ ወታደሮች የሞቱት ጎማ ሲቀይር የነበረ አንድ የጭነት መኪና አሽከርካሪን ሲረዱ በደረሰባቸው የመኪና አደጋ እንደነበር ይታወሳል።

የጦር ሠራዊቱ አባላት በሮም የተገኙት ከ60 ዓመታት በፊት እንደ ጎረጎሮሳውያኑ በ1966 ዓ. ም. ተመሥርቶ በ1981 ዓ. ም. ወደ ወታደራዊ መኮንንነት ያደገበትን እና ከ25 ዓመታት በፊት የመጀመሪያው ጳጳስ የተሾመበትን ጨምሮ ሌሎች ተከታታይ የመታሰቢያ በዓላትን ለማክበር እንደ ነበር ታውቋል።

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ ከፖርቱጋል የጦር ሠራዊት አባላት ጋር
ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ ከፖርቱጋል የጦር ሠራዊት አባላት ጋር   (@VATICAN MEDIA)

ከእግዚአብሔ ዘንድ ብርታትዎን አግኙ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ክርስቲያን ለሆኑት የሠራዊቱ አባላት ባስተላለፉት መልዕክት፥ ወደ ሮም ያደረጉትን ጉዞ ለግል ሕይወት እድሳት እና እምነታቸውን የሚያጥናክሩበት አጋጣሚ አድርገው እንዲጠቀሙበት ጥሪ አቅርበዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች በጻፈው መልዕክት ላይ “በጌታና በኃይሉ ችሎት የበረታችሁ ሁኑ፤ ወገባችሁን በእውነት ታጥቃችሁ፣ የጽድቅንም ጥሩር ለብሳችሁ እግሮቻችሁም ለሰላም ወንጌል ዝግጁ ሆናችሁ ጸንታችሁ ቁሙ” ያለውን እንዲከተሉ አበረታተዋቸዋል።

በቅፍርናሆም እንደ ነበረው የመቶ አለቃ፥ ኢየሱስ መከራን የሚቀበል አገልጋዩን እንዲፈውስ እንደጠየቀው ሁሉ በጌታም እንዲጸኑ አሳስበዋል። ሰዎች አቅመ ደካሞች ቢሆኑም ነገር ግን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ሲቀርቡ ከራሳቸው የሚበልጥ ነገር የሚመኙ መሆኑን እንዲያቁ አደራ ብለዋል።

“ኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወታችሁ የምትቀርጽባቸውን እሴቶች በሚገባ ያውቃል” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ እነሱም ታዛዥነት፣ ተግሣጽ፣ ራስን መካድ፣ ታማኝነት፣ ጓደኝነት፣ ቁርጠኝነት፣ ኃላፊነት እና ድፍረት ናቸው” ሲሉ አብራርተው፥ የመቶ አለቃውም እግዚአብሔር እንደሚፈልገው ተሰምቶታል ሲሉ አፅንዖት ሰጥተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በማከልም የመቶ አለቃው በአመለካከቱ “የሥልጣን ተዋረድን እንዴት እንደገመገሙው እና ይህም የዕለት ተዕለት ሕይወቱ ገጽታ ጌታ እና አምላኩ እንደሆነ ከሚገልጸው ከናዝሬቱ ኢየሱስ ጋር ያለውን ግንኙነት እንዲረዳ ማገዙን ያሳያል” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከፖርቱጋል የጦር ሠራዊት አባላት የቀረበላቸውን ስጦታ ሲቀበሉ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከፖርቱጋል የጦር ሠራዊት አባላት የቀረበላቸውን ስጦታ ሲቀበሉ   (@VATICAN MEDIA)

ትሕትና ያለበት ድፍረት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ “ይህ ወታደር በአንድ በኩል ሥልጣኑን ያውቃል፤ በሌላ በኩል ደግሞ በእግዚአብሔር ልጅ ፊት የእምነት ጥንካሬን እና የትሕትና ድፍረትን አሳይቷል” ሲሉ ተናግረው፥ “አንድ ሰው ምንም ያህል ኃላፊነት እና ኃይል ቢኖረውም፣ ምንም ያህል የማይነቀፍ ቢሆንም ዘወትር ማለቂያ ለሌለው ዘላለማዊነት ይጠማል” ሲሉ አፅንዖት ሰጥተዋል።

ከፖርቱጋል የጦር ሠራዊት አባላት መካከል
ከፖርቱጋል የጦር ሠራዊት አባላት መካከል   (@Vatican Media)

“መሪ ካኅናት ተልዕኮአችሁን ቀጥሉ”

በመጨረሻም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለካኅናት ባስተላለፉት መልዕክት፥ ቤተ ክርስቲያን የወታደር አባላት እና የፖሊስ መኮንኖችን መንፈሳዊ ዕድገት ሃላፊነት ለካኅናት እንደምትሰጥ ተናግረው፥ ሁሉንም ሰው በደስታ እንዲቀበሉ፣ እንዲያዳምጡ፣ የእግዚአብሔርን ቃል እንዲያመጡላቸው እና ቅዱሳት ምስጢራትን በማክበር፣ ከእያንዳንዱ ሰው እና ቤተሰቦቹ ጋር በመሆን በክርስቶስ ስም እንዲያገለግሉ አበረታተዋቸዋል።

“ከዚህ ልዩ አገልግሎት የሚመጣው በክርስትና ሕይወት ልምምድ ውስጥ የግል ዕድገት እና የምታገለግሏቸው የወታደራዊ እና የደህንነት ኃይሎች እስትንፋስ ጥንካሬ ውጤቶች ናቸው" ሲሉ ለአገልግሎታቸው አመስግነዋል።

“ለቤተ ክርስቲያኒቱ እና ለአገሪቱ ያላችሁ ፍቅር ምስክርነት መጽናናትን የሚያመጣ እና ተስፋን የሚሰጥ ነው” ብለው በመጨረሻም የፋጢማ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በተልዕኮአቸው ውስጥ ከሚገኙት ሁሉ ጋር እንድሆን በመጸለይ ንግግራቸውን ደምድመዋል።

 

25 Aug 2026, 15:20