ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ ምዕመናን በቅዱስ ወንጌል በመመራት ለግጭቶች ምላሽ እንዲሰጡ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ቅዳሜ ነሐሴ 16/2018 ዓ. ም. በሳን ማሪኖ ሪፐብሊክ የግማሽ ቀን ሐዋርያዊ ጉብኝት አድርገዋል። ቅዱስነታቸው በሳን ማሪኖ ከካቶሊካዊ ማኅበረሰብ ጋር ተገናኝተው ባስተላለፉት መልዕክት፥ ሁሉም ሰው የሪፐብሊኩ መሥራቾች የሆኑትን የቅዱስ ማሪነስ እና እና የቅዱስ ሊዮን ፈለግ በመከተል በቅዱስ ወንጌል ላይ የበለጠ እምነት እንዲኖረው አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በጣሊያን ውስጥ የምትገኝ ትንሿን አገር ሳን ማሪኖን በጎበኙበት ወቅት ባደረጉት ንግግር የሪፐብሊኩ መሥራቾች የሆኑት የቅዱስ ማሪነስ እና የቅዱስ ሊዮ የሕይወት ገድሎችን አስታውሰዋል።

“ድንጋይ ጠራቢ እና ተራ ምዕመናን የነበሩት ነገር ግን በኋላ ለሐዋርያዊ አገልግሎት የተሾሙት ቅዱስ ማሪነስ እና ቅዱስ ሊዮ በክርስቲያናዊ ነፃነት፣ በጋራ መከባበር እና በኅብረት የወንጌልን መልዕክት ወደ አዲስ ማኅበራዊ እና የፖለቲካን ሞዴልነት መተርጎም ይችሉ ነበር” ሲሉ ተናግረዋል።

 ወጣቶች፥ ልባችሁን ወሰን ለሌለው እግዚአብሔር ክፈቱ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለሳን ማሪኖ ምዕመናን ባደረጉት ንግግር፥ “በከፊል እና ወዲያው በሚሰጡ መልሶች ከመርካት ይልቅ ልባችሁን ወሰን ለሌለው እግዚአብሔር ክፈቱ” በማለት ወጣቶችን አሳስበው፥ ይህም በታሪክ ላይ አሻራቸውን እንዲተዉ ከሚረዳቸው ከእግዚአብሔር ጋር እንዲገናኙ ሊያደርጋቸው እንደሚችል ተናግረዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በመቀጠልም በቦታው የተገኙት በሙሉ እግዚአብሔር የሰጣቸውን የጋብቻ ወይም የምንኩስናን ሕይወት ተልዕኮን በጋለ ስሜት እንዲቀበሉ እና እንደ ፖለቲካ እና ማኅበራዊ ተሳትፎ ያሉ አስቸጋሪ የሥራ መስክ ምርጫዎችን ለማድረግ ድፍረት እንዲኖራቸው ጥሪ አቅርበው፥ “ለዓለም የሚናገር ሰላም” የሚለውን የሐዋርያዊ ጉብኝታቸው መሪ ቃል ለመመስከር በተቻለ መጠን እንዲዘጋጁ አሳስበዋል።

ልጆችን በክርስቲያናዊ እሴቶች ማነጽ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ካኅናት፣ የትምህርተ ክርስቶስ አስተማሪዎች እና ሌሎች መምህራን ወላጆችን በመደገፍ ላበረከቱት ሥራ ካመሰገኗቸው በኋላ፥ ወላጆች የልጆቻቸው ዋና አስተማሪዎች በመሆናቸው ጥበብ በተሞላበት ሐዋርያዊ አቀራረብ የራሳቸውን እምነት እንዲያድሱ እና ክርስቲያናዊ እሴቶቻቸውን ለልጆቻቸው በማስተላለፍ ደስታን እንዲያገኙ ያደርጋቸዋል ብለዋል።

በተለይም የጥምቀት እና የቅዱሳት ምስጢራት ሕይወትን እንዲያዳብሩ እና የአንድነት ተሞክሮ የሆነውን የጋራ አምልኮ ሥርዓትን በጥንቃቄ እንዲያዳብሩት ጥሪ አቅርበዋል።

ወንጌልን በበቂ እምነት በመከተል ለግጭት ምላሽ መስጠት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የሕይወትን ትርጉም ለሚመለከቱ ጥያቄዎች ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም መልስ እንደሆነ እና ቅዱስ ወንጌል ለሁሉም ሰው የነፃነት መንገድ መሆኑን ተናግረው፥ ለምናገኛቸው ሁሉ ልንሰጣቸው የምንችለው ስጦታ እንደሆነም አስረድተዋል። በተለያዩ መንገዶች ክርስቲያኖች ቸርነታቸውን የሚገልጹት እና ድጋፋችንም በምናቀርብላቸው ሰዎች ጥቅም ላይ ያነጣጠረው ለዚህ ነው ሲሉ አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በንግግራቸው ማጠቃለያ፥ “ምላሻችን በግጭት በተሞላ ዓለም ውስጥ በወንጌል በመታመን የምናደርገው ጉዞ ብቻ ነው” ሲሉ ተናግረው፥ ግለኝነትን፣ አለመተማመንን እና ከፋፋይነትን በማሸነፍ ለወንድማማችነት እና ለሰላም ባለን ተስፋ አዲስ ሕይወት ለመተንፈስ የሚያግዝ የኅብረት አስፈላጊነት በማስታወስ “ይህ ውርስ ቅዱስ ማሪነስ እና ቅዱስ ሊዮ የጀመሩትን በጽናት እና በቁርጠኝነት መገንባት የመቀጠል ተልዕኳችን አካል ነው” ሲሉ አስገንዝበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በሳን ማሪኖ ሪፐብሊክ ሐዋርያዊ ጉብኝት ሲያደርጉ

 

22 Aug 2026, 15:33