“ይህ ኃላፊነትን የሚወስዱበት ሰዓት ነው”
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
"ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ “አእምሮን፣ ቃላትን እና አገራትን ለግጭት ከሚያነሳሳ የሐሰት እውነታ ይልቅ የዛሬው ካቶሊካዊ ባህል የምሕረትን እውነታ ማቅረብ አለበት። በምሕረት እውነታ ውስጥ ጠላትነት ሊኖሩ አይችልም። ሰዎች በሙሉ ጠላቶችም እንኳን ቢሆኑ በወንድማማችነት እና እህትማማችነት መንፈስ በእውነት መገናኘት አለባቸው” ማለታቸው ይታወሳል።
እነዚህ ቃላት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በጣሊያን ሪሚኒ ከተማ በተካሄደው ስብሰባ ላይ ለተሳታፊዎቹ የተናገሯቸው ናቸው። ከኅብረት እና ከነፃነት ተሞክሮ በመነሳት በተለይም በበጋው የዕረፍት ጊዜ ማጠናቀቂያ ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች በተገኙበት ስብሰባ ላይ የተናገሯቸው ናቸው። እነዚህ ቃላት ስብሰባውን ብቻ በማስመልከት የቀረቡ ሳይሆን ነገር ግን ከሁሉ አስቀድሞ የምንገኝበትን እውነታ ማየት እንድንችል የቀረቡ እውነተኛ ግብዣ ነበሩ።
የቀሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ከ44 ዓመታት በፊት ለስብሰባው ተካፋዮች ባደረጉት ንግግር፥ ‘ግንኙነት’ እና ‘በሕዝቦች መካከል ያለ ወዳጅነት’ ለሚሉት ጭብጦች ውበት አፅንዖት በመስጠት፥ ‘በዓለም ታሪክ ውስጥ አስደናቂ ጊዜያት ናቸው’ ሲሉ ጠርተዋቸው ነበር።
ዛሬ የዓለም አቀፍ ሁኔታ ከዚያን ጊዜ በበለጠ እርግጠኛ ያልሆነ አደገኛ ጊዜ ነው። በቁጥር እየጨመሩ የመጡ ግጭቶች፣ በሲቪሎች እና በልጆች ላይ የሚፈጸሙ ጭፍጨፋዎች ብዙ ናቸው። አንድ ሰው ስለ ጋዛ እና ስለ ዩክሬን ግጭት ብቻ ያስብ ይሆናል። ነገር ግን ብዙ አገራት የራሳቸውን የመሣሪያ ትጥቅ ለማደራጀት ብዙ ገንዘብ እያፈሰሱ ይገኛል። ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በዚህ ሁሉ መሃል የስብሰባውን ጥሪ በማስታወስ፥ ይህም በተወሰነ አካባቢ ብቻ ተከልሎ መቆየት ሳይሆን እርስ በርስ የመገናኛ እና የውይይት መስቀለኛ መንገዶች መሆን እንደሚገባ በማሳሰብ፥ ጊዜውንም “የኃላፊነት ጊዜ” ብለው ጠርተውታል።
ከሃያኛው ክፍለ ዘመን አሳዛኝ ሁኔታዎች በኋላ ዛሬ ኢየሱስ ክርስቶስን መከተል ማለት ክፋት ከክፋት ጋር መዋጋት የማይችል መሆኑን ሙሉ በሙሉ መገንዘብ ማለት ነው። ለእኛ ሲል በተሰቀለው በመሲሑ ኢየሱስ ክርስቶስ የተዋቀረ ብቸኛው የመቤዠት መንገድ እና የክርስቲያን መልስ ፍቅር ነው።
ስለዚህ ዛሬ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ‘ሐሰት’ ብለው ለመጥራት ያላመነቱትን፥ አእምሮን፣ ቃላትን እና አገራትን እንደገና ለጥፋት ለሚቀሰቅሱት በሙሉ የካቶሊክ ባሕል በእውነተኛ እውነታ ምላሽ ይሰጣል። የምሕረት እውነታ፣ ጠላትነት የሌለበት እና ሁሉም ሰው በእውነተኛ የወንድማማችነት እና እህትማማችነት መንፈስ የሚገናኙበት ነው።
ስለዚህ የሰው ልጅ አብሮ መኖርን ከጥርጣሬ ነፃ ለማውጣት፣ ከመጠን ያለፈ ትርፍን ከማምለክ፣ ቴክኖሎጂን እና ፋይናንስን ከሞት ንግድ ለማላቀቅ ተጨባጭ ውሳኔ የሚያደርጉ ደፋር ሰዎች ያስፈልጋሉ።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለድህነት እና ለእኩልነት ማጣት፣ ለጦርነት እና ለአካባቢያዊ አደጋዎች መንስኤ የሆኑት ኢ-ፍትሃዊ የኃይል ግንኙነቶች እንዲጋለጡ ጥሪ አቅርበዋል። ይህ የሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ተተኪ ጠንካራ እና ተጨባጭ ጥሪ ከርዕሠ ሊቃነ ጵጵስና ሥልጣናቸው የመጀመሪያ ቀን ጀምሮ ‘ትጥቅ የሌለበት እና ትጥቅን የሚያስፈታ ሰላም’ በማለት ሲናገሩ የቆዩ ሲሆን፥ ይህም የሁሉን ካቶሊካዊ ምዕመናን ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ተሳትፎን ለማረጋገጥ እንደ መስፈርት መወሰድ አለበት።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የስብሰባው ተካፋዮች ሃላፊነቶችን እንዲወስዱ፣ እራሳቸውን በቀዳሚነት እንዲያስቀምጡ፣ በተለይም ከሁሉም ዓይነት የጠባብነት ስሜቶች በላይ ትስስራቸውን እንዲያሰፉ መጋበዛቸው ጠቃሚ ነው። የኅብረት እና የነፃነት እንቅስቃሴዎች፣ ቡድኖች እና ማኅበረሰቦች የተለያዩ ባህሎች፣ ስሜቶች እና ዳራዎች ካሏቸው ወንድሞች እና እህቶች፣ በተለይም ከድሆች ለማራቅ የሚፈልገውን ሁሉ በመቃወም ወደ እውነታው ሙሉ በሙሉ መግባት የሚቻልባቸው ዋና ምንጭ መሆን አለባቸው።
በመጨረሻም፥ በፍቅር ውስጥ ማስገደድ፣ የሐሰት ትርክት ማቅረ ወይም መመልመል ፈጽሞ እንዳይኖር ለማድረግ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛን ማሳሰቢያ ማጉላት ተገቢ ነው። ምክንያቱም ፍቅር የሚገኘው በነፃነት፣ በዘላቂ ግንኙነት እና በራስ ልግስና ስጦታ ብቻ ነው” በማለት ርዕሠ አንቀጹ ሐተታውን ደምድሟል።
