ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በአሲሲ የሚያስተላልፉት መልዕክት ወጣቶችን እንደሚያበረታታ ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በአሲሲ ከተማ ሐምሌ 30/2018 ዓ. ም. በሚያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ለአራት ቀናት ሲካሄዱ የቆዩት ውይይቶች እና አውደ ጥናቶች የሚጠቃለሉ ሲሆን፥ በዚሁ ዕለት ቅዱስነታቸው ከወጣቶች ለሚቀርቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ በመስጠት የመዝጊያ መስዋዕተ ቅዳሴን እንደሚመሩ የጉብኝታቸው መርሃ ግብሩ አመልክቷል።
ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 33 ዓመት የሆናቸው በሺዎች የሚቆጠሩ የአውሮፓ ወጣቶች ከሐምሌ 25 – 30/2018 ዓ. ም. ድረስ በአሲሲ በሚያደርጉት “GO! Franciscan Youth Conference” የተሰኘ ስብሰባ አዘጋጆች መካከል አንዱ እና በወጣቶች ሐዋርያዊ እንክብካቤ ላይ ልምድ ያለው ወንድም ሉካ ዴ ፓስኳሌ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረገው ቆይታ፥ ከወጣቶቹ መካከል ብዙዎቹ ጠንካራ ፍላጎት እንደሌላቸው እና ስለወደፊት ሕይወታቸው ማለም ያቆሙ መሆናቸውን አስረድቷል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛን የመሳሰሉ ሰዎችን መስማት አስፈላጊ መሆኑን ለዜና አገልግሎቱ የተናገረው ወንድም ሉካ፥ ቅዱስነታቸው ለወጣቶች ስለ ሕይወት ሙላት ሊነግሯቸው እንደሚችሉ ገልጾ፥ እንዲሁም ቅዱስ ፍራንችስኮስን የመሳሰሉ ምሳሌ መሆን የሚችሉ ሰዎችን መፈለግ ጠቀሜታ እንዳለው እና ቅዱስ ፍራንችስኮስ የዛሬዎቹን ወጣቶች ሊያነጋግራቸው እንደሚችል አስረድቷል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሐምሌ 30/2018 ዓ. ም. ጠዋት በማለዳ ወደ አሲሲ እንደሚደርሱ የገለጸው ወንድም ሉካ፥ ሥነ-ሥርዓቱ በሙሉ በመላእክት ንግሥት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በባሲሊካ ውስጥ በምትገኝ፣ ቅዱስ ፍራንችስኮስ መልሶ በጠገናት እና በኖረባት ትንሿ ጸሎት ቤት ውስጥ እንደሚከናወን አስረድቷል። ጸሎት ቤቷ ለፍራንችስካዊ ማኅበራት በሙሉ እንዲሁም ዘንድሮ ለሚከበረ የቅዱስ ፍራንችስኮስ ዕረፍት 800ኛ ዓመት መታሰቢያ በዓል ቁልፍ ቦታ መሆኗን አስታውቋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በጸሎት ቤቷ ውስጥ በሚያደርጉት ቆይታ የግል ጸሎት እንደሚያደርጉ የገለጸው ወንድም ሉካ፥ ቀጥለውም ወደ አደባባዩ ከደረሱ በኋላ ወደ ባዚሊካው መግባት ያልቻሉት አቅም ደካሞች ፊት ሆነው ከተለያዩ የአውሮፓ አገራት የተውጣጡ ሦስት ወጣቶች ለሚያቀርቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ በመስጠት፥ ከልዩ ልዩ ፍራንችስካዊ ማኅበራት ተወካዮች ጋር በግል ከተገናኙ በኋላ ከረፋዱ ወደ አራት ሰዓት ተኩል ገደማ የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓትን እንደሚመሩ አስረድቷል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በመስዋዕተ ቅዳሴው ላይ በሚያሰሙት ቃለ-ምዕዳን ወጣቶቹ ባለፉት ቀናት ውስጥ የሰሟቸውን ነገሮች ሁሉ የሚገልጽ ቃል ሊያቀርቡ እንደሚችሉ የተናገረው ወንድም ሉካ፥ ቅዱስነታቸው ወደ መንበራቸው ከተመለሱ በኋላ ለወጣቶች የሚስዮናዊነት መልዕክት የያዘ ጽሑፍ እንደሚያቀርቡላቸው አስረድቷል።
ወጣቶች ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ጋር ከመገናኘታቸው በፊት በተለያዩ ርዕሠ ጉዳዮች ላይ የሚደረጉ አውደ ጥናቶችን እንደሚሳተፉ የገለጸው ወንድም ሉካ፥ በአንድ በኩል በአድማጭነት እየተሳተፉ በሌላ በኩል ደግሞ ራሳቸው ማዕከላዊውን መድረክ በመውሰድ አስተያየታቸውን የሚገልጹበት ዕድል እንደሚያገኙ ገልጿል።
አውደ ጥናቶቹ የዝግጅቱ ዋና ማዕከል እንደሚሆኑ የገለጸው ወንድም ሉካ፥ በመጀመሪያው ምሽት ወጣቶቹ በቀጣዮቹ ቀናት ውስጥ ምን እንደሚደረግ የሚገልጹ የአሲሲ ከተማ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፌሊቼ አክሮካ እና ፕሮፌሰር ማርኮ ኤርባ የመግቢያ ንግግሮችን እንደሚያዳምጡ ታውቋል።
ስለ ሰላም፣ ስለ ይቅርታ እና ስለ ጥሪ የሚናገሩ ውይይቶች እንደሚካሄዱ ያስታወቀው ወንድም ሉካ፥ ይህም ወጣቶች በሕይወታቸው ውስጥ የእግዚአብሔርን ጥሪ እንደገና ለማዳመጥ ዕድል እንደሚሰጣቸው ገልጾ፥ ሐምሌ 28 የሚካሄደውን አውደ ጥናት ከተከታተሉ በኋላ ሐምሌ 29 ቀን በሚካሄዱ የበለጠ ንቁ በሆኑ አውደ ጥናቶች ከተሳተፉ በኋላ በቀጥታ መናገር እና ራሳቸውን መግለጽ እንደሚችሉ አስረድቷል።
ቅዱስ ፍራንችስኮስ ከእምነት ልዩነት ባሻገር ሰዎችን መሳብ መቀጠሉን መመልከታችን ድፍረት እንዲኖረን እና ከጭፍን ጥላቻ ወጥተን አንድ እርምጃ ወደ ፊት ለመራመድ፣ በሕይወት መካከል ከሚያጋጥሙ አስፈላጊ ነገሮች ጋር እንደገና ለመገናኘት እና ምናልባትም ከእግዚአብሔር ጋር መገናኘት የሚፈልጉ ሰዎች ራሳቸውን እንዲያቀርቡ ሊያነሳሳቸው እንደሚችል አስረድቷል።
የቅዱስ ፍራንችስኮስ ምስል ከወጣቶች ልብ ጋር የተያያዙ ብዙ ጉዳዮችን እንደሚያጠቃልል የተናገረው ወንድም ሉካ፥ የአካባቢ እንክብካቤ፣ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ሥር ነቀል ግንኙነት፣ እጅግ ለተቸገሩት ሰዎች የሚደረግ ልግስናን እና ለሴቶች ሊሰጥ የሚገባውን አክብሮትን እንደሚያካትት አስረድቷል።
“ፍራንችስኮስ የሚደነቅ ሰው ነበር” ያለው ወንድም ሉካ፥ ሰዎችን ወደ እርሱ የሚስብ ትህትና እንዳለው፣ ከእኩዮቹ መካከል አንዱ በመሆን ስለ ወጣቶች ሕይወት የመናገር ችሎታው እና ከሁሉም በላይ ዘወትር ታላቅ ህልም አላሚ እንደ ነበር ተናግሮ፥ ቅዱስ ፍራንችስኮስ ሕይወት የሚሰጠውን ነገር ብቻ የሚቀበል ወጣት እንዳልነበረ እና ይህም ብዙ ወጣቶችን እንደሚያስደምም አስረድቷል።
“ወጣቶችን አሲሲ ውስጥ ባገኘሁ ቁጥር ጥያቄ መጠየቅ ያስደስተኛል” የሚለው ወንድም ሉካ፥ ዕድሜያቸው ምንም ያህል ይሁን ሁልጊዜ “ሕልምህ ምንድን ነው? በልብህ ውስጥ ያለው ትልቁ ፍላጎት ምንድን ነው?” ብሎ እንደሚጥይቅ ገልጾ፥ ነገር ግን ብዙዎቹ መልስ እንደሌላቸው እና ተስፋ እንደቆረጡ ሲያውቅ እንደሚያዝን ነገር ግን የቅዱስ ፍራንችስኮስን የሕይወት ታሪክ ሲያዳምጡ፥ ተስፋን ሳይቆርጥ ዘወትር ከዚያ በላይ ለመሄድ የሚደፍር መሆኑን ማየት እንደቻሉ አስረድቷል።
ቅዱስ ፍራንችስኮስ እጅግ ዘመናዊ እና ተዛማጅነት ያላቸውን ጉዳዮች ይዳስሳል” ያለው ወንድም ሉካ፥ ስለ ፍጥረት እንክብካቤ እና በእርስ በርስ ግንኙነቶች ውስጥ ስለ መከባበር አስፈላግነት፣ በግለኝነት በሚታወቅ ዓለም ውስጥ ስለ ወንድማማችነት እና እህትማማችነት መሰማት እንደሚፈልግ፥ እነዚህ በሙሉ ዛሬ ለሰዎች በጥልቀት የሚናገሩ ጭብጦች መሆናቸው ወንድም ሉካ አስረድቷል።
የዘንድሮ ዝግጅት አካል እንደመሆኑ መጠን ባለፈው ዓመት በሪሚኒ ስብሰባ ላይ የቀረበው ኤግዚቢሽን መካተቱን የገለጸው ወንድም ሉካ፥ ኤግዚቢሽኑ ከዝግጅቱ መጀመሪያ ቀን ጀምሮ እስከ ቅዱስ ፍራንችስኮስ በዓል ድረስ በመላእክት ንግሥት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ባዚሊካ ባለበት ለእይታ እንደቀረበ አስረድቷል።
“ወንድም ፀሐይ” በሚል ርዕሥ ቅዱስ ፍራንችስኮስ ያቀረበው የውዳሴ መዝሙር ብዙውን ጊዜ የሥነ-ምህዳር መዝሙር ተብሎ መተርጎሙን የገለጸው ወንድም ሉካ፥ ቅዱስ ፍራንችስኮስ የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋች እና ፍጥረታት በሕይወቱ ውስጥ ካሉት ሌሎች ነገሮች ሁሉ ቅድሚያ የሚሰጣቸው እንደ ነበሩ አስታውሷል።
የውዳሴ መዝሙሩ በዚህ መንገድ ሲነበብ በተሳሳተ መንገድ እንደሚተረጎም የተናገረው ወንድም ሉካ፥ ቅዱስ ፍራንችስኮስ ይህን የውዳሴ መዝሙር ሲጽፍ በላ ቨርና ላይ ቅንዋትን እንደተቀበለ፣ ማኅበርተኞቹም ወደ ጎን በማለት የማኅበሩ ጠቅላይ አለቃ አድርገውት ለመሾም ባለመፈለጋቸው የተነሳ በመንፈሳዊነት መንገድ ራሱን በብቸኝነት ሁኔታ ውስጥ ማግኘቱን አስረድቷል።
ቅዱስ ፍራንችስኮስ ሥነ-ምህዳርን በማስመልከት የጻፈው የውዳሴ መዝሙር በእውነቱ ለእግዚአብሔር ያቀረበው መዝሙር እንደ ነበር ያስታወሰው ወንድም ሉካ፥ “ቅዱስ ፍራንችስኮስ በፍጥረታት የተሳበው የእግዚአብሔርን አሻራ ስለያዙ እና በእነርሱ አማካይነት እግዚአብሔርን ማየት በመቻሉ ነው” ካለ በኋላ፥ ይህም ቅዱስ ፍራንችስኮስን ከትግሉ እና ከሕማማቱ ወደ ኋላ እንዳይመለስ ረድቶታል” ሲል አስረድቷል።
“ተስፋችን ወጣቶች በራሳቸው ውስጥ ለሚይዙት ጥልቅ ጉጉት ምላሽ መስጠት እንዲችሉ ማድረግ ነው” ያለው ወንድም ሉካ፥ ቅዱስ ፍራንችስኮስ ወጣቶች አስቀድመው የያዙትን ጥያቄዎች በመከተል ወደ ግብ ማድረስ እንዲችሉ ሊያግዝ እንደሚችል፥ ነገር ግን አሁን ባለው ሐዋርያዊ አባት ወይም ወዳጅ ሰው አማካይነት ፍለጋቸውን እንዲቀጥሉ ሊረዳቸው ይችላል” ሲል ወንድም ሉካ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር የነበረውን ቆይታ አጠቃልሏል።
