አባ ታዴውስ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ጥሩ የዕረፍት ጊዜ እንደሚኖራቸው ያላቸውን ተስፋ ገለጹ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ መልካም የዕረፍት ጊዜን እንደሚያሳልፉ፥ ጊዜያቸውን በጸሎት፣ መጽሐፍት በማንበብ እና በስፖርት ለማሳለፍ ያላቸውን ምኞት እንደሚያሳኩ በካስቴል ጋንዶልፎ የቪላኖቫው ቅዱስ ቶማስ ቁምስና መሪ ካኅን እና የሳሌዢያን ዶን ቦስኮ ማኅበር አባል አባ ታዴውስ ሮዝመስ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት ተናግረዋል።
ቅዱስነታቸው ባለፈው ዓመት የዕረፍት ጊዜያቸውን በካስቴል ጋንዶልፎ ለማሳለፍ የመጡበትን ወቅት ያስታወሱ አባ ታዴውስ፥ በካስቴል ጋንዶልፎ ወደሚገኝ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ማረፊያ ሲደርሱ የአካባቢው ነዋሪዎች ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል።
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ሰላምታ አስገራሚነት
አባ ታዴውስ ከሁሉም አስቀድመው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለቁምስናው መሪ ካኅን እና ለምዕመናኑ ላቀረቡት ሰላምታ ምስጋናቸውን አቅርበው፥ ክስተቱን አስገራሚ ሆኖ እንዳገኙት አስረድተዋል።
ለጳጳሳዊ ቁምስና አስፈላጊነት እውቅናን የሰጡበት እንደሆነ ገልጸው፥ “በሥፍራው የሚገኙት የቫቲካን ተቋማት በተናጥል ቢሠሩም በሕገ ቀኖና መሠረት ቁምስናው እና የቁምስናው መሪ ካኅን ጠቃሚ ሚና አላቸው” ብለው፥ ይህም ቅዱስነታቸው ለቁምስናው ምዕመናን ያሳዩት አስደናቂ ምልክት ነበር” ብለዋል።
የቅዱስነታቸው የዕረፍት ጊዜ
አባ ታዴውስ በገለጻቸው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ዘንድሮ በካስቴል ጋንዶልፎ የሚያሳልፉት ጊዜ ካለፈው ዓመት የተለየ እንደሆነ ጠቁመው፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ይህን ጊዜ በካስቴል ጋንዶልፎ እውነተኛ የዕረፍት ጊዜን ለማሳለፍ እንደሚፈልጉ አስቀድመው መናገራቸውን አስረድተዋል።
አባ ታዴውስ በማከልም፥ ቅዱስነታቸው ወደ ካስቴል ጋንዶልፎ የሚመጡት ለጸሎት፣ ለዕረፍት፣ ለማንበብ እና ለሰውነት እንቅስቃሴ መሆኑን በግልጽ መናገራቸውን ጠቅሰው፥ “እንደተመኙትም ሁሉ ቦታው እንደ ቤታቸው እንዲሰማቸው እና መልካም የዕረፍት ጊዜን እንዲያሳልፉ እንፈልጋለን” ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ እንደተናገሩት ሁሉ፥ ዕለቱን በደስታ የሚጠባበቁ ምዕመናንን እሑድ ዕለት በኅብረት በሚያቀርቡት የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ወቅት እንደሚያገኟቸው እና ሌሎች ተመሳሳይ ገጠመኞች ሊኖሩ እንደሚችሉ መጠቆማቸውን አባ ታዴውስ አስታውሰዋል።
ትስስርን የሚያጠናክሩ ስብሰባዎች
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ባለፈው ዓመት ካስቴል ጋንዶልፎን በጎበኙበት ወቅት ሊያገኟቸው የቻሉባቸው ተደጋጋሚ አጋጣሚዎች እንደ ነበሩ አባ ታዴውስ ተናግረዋል። በየሳምንቱ ማለት በሚቻል ሁኔታ ሰኞ ከሰዓት በኋላ ወደ ቪላ ባርቤሪኒ እንደሚጓዙ እና እስከ ማክሰኞ ምሽት ድረስ እዚያው እንደሚቆዩ ተናግረዋል።
ከማረፊያቸው ሲወጡ ሊመቀበሏቸው ውጭ ከተሰበሰቡት ነጋዲያን ወይም ከጋዜጠኞች ጋር ይነጋገሩ እንደ ነበር፣ የቁምስናው መሪ ካኅን እንደመሆናቸው ጥቂት ቃላትን ለመለዋወጥ፣ መረጃዎችን ለማስተላለፍ ወይም ሰላምታ ለመስጠት ዕድል ማግኘታቸውን አባ ታዴዎስ አስታውሰዋል።
እጅግ የሚያስደስቱ ጊዜያት እንደ ነበሩ፣ አንድ ሰው አባታዊ ቅርበታቸውን በትክክል የሚገነዘብበት ወቅት እንደ ነበር አስረድተው፥ “ይህ ባሕል የበጋው ወቅት ካለፈ በኋላም እንደሚቀጥል ተስፋ አደርጋለሁ” ሲሉ ተናግረዋል።
የማይረሳ መስዋዕተ ቅዳሴ እና የቅዱስነታቸው ስጦታ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ባለፈው ዓመት ሐምሌ 6/2017 ዓ. ም. በቪላኖቫው ቅዱስ ቶማስ ቁምስና ያሳረጉትን የመጀመሪያ መስዋዕተ ቅዳሴ ጥልቅ ስሜት ያስታወሱት አባ ታዴዎስ፥ ቤተ ክርስቲያኑ ትንሹ ከመሆኑ የተነሳ በሥነ-ሥርዓቱ ላይ ለመሳተፍ የሚፈልጉትን ምእመናን በሙሉ ማስተናገድ አለመቻሉን አስረድተዋል።
ምን ጊዜም ቢሆን የማይረሱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በቀጥታ ለምዕመናን ንግግር ማድረጋቸው እና ልዩ ስጦታ ማቅረባቸው መሆኑን አባ ታዴውስ ጠቁመው፥ ስጦታቸውም የሚያምር የቅዳሴ ጽዋ እንደ ነበር አስታውሰው፥ ይህን ስጦታ በመላው ምዕመናን ስም ከእጃቸው መቀበል ክብር እንደ ነበረ እና ለዚህም ማመስገናቸውን ተናግረው፥ በክኅነት ሕይወታቸውም እጅግ ዋጋ ያለው ጊዜ ሆኖ እንደሚቀር አስረድተዋል።
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ትውስታዎች
አስተያየታቸውን መስጠት የቀጠሉት አባ ታዴውስ ሮዝመስ፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ በካስቴል ጋንዶልፎ ምዕመናን ልብ ውስጥ ልዩ ሥፍራ እንዳላቸው ገልጸው፥ የቅዱሱ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ስም በምዕመናን ታሪክ ውስጥ በየጊዜው እንደሚነሳ አስረድተዋል።
ያለፈው እሑድ ዓይኖቻቸው በእንባ የተሞሉ ምዕመናንን ማየታቸውን የተናገሩት አባ ታዴውስ፥ ብዙዎቹ የልጅነት ጊዜያቸውን እያስታወሱ እንደ ነበር፣ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት አዘውትረው ወደ ካስቴል ጋንዶልፎ ሲመጡ ምዕመናኑ ስለ ቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እንደሚናገሩ በማስረዳት፥ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ወደ ካስቴል ጋንዶልፎ መመለስ እነዚያ ትዝታዎች ወደ ሕይወት እንዲመለሱ በማድረግ በሰዎች ልብ ውስጥ ደስታን እንደሚፈጥር ተናግረዋል።
ር. ሊ. ጳ. ወደ ካስቴል ጋንዶልፎ የመጡባቸው አራት ክፍለ ዘመናት
የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የዘንድሮው የበጋ ወቅት ዕረፍት ከአንድ ከፍተኛ የመታሰቢያ በዓል ጋር የሚገጣጠም ሲሆን፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ዘንድሮ 2026 ዓ. ም. ቤተ ክርስቲያን ካስቴል ጋንዶልፎን የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የበጋ ወቅት ማረፊያ ያደረገችበት 400ኛ ዓመት መታሰቢያ የሚከበርበት ሲሆን፥ ባሕሉን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 1626 ዓ. ም. የጀመሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ኡርባኖስ ስምንተኛ እንደ ነበሩ ይታወሳል።
“ሀገረ ስብከቱ ከአካባቢው ባለሥልጣናት እና ከቁምስናው ጋር መታሰቢያ በዓሉን ለማክበር እየተዘጋጀን እንገኛለን” ብለው፥ የሐዋርያው ጴጥሮስ ተተኪዎች በካስቴል ጋንዶልፎ ለአራት መቶ ዓመታት መገኘታቸውን ማስታወስ ቦታው በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ ያለውን ጠቀሜታ ለማጉላት ልዩ አጋጣሚ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።
