ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለቤተክርስቲያኗ ላደረጉት ድጋፍ የጣሊያን ፕሬዝዳንትን አመስግነዋል
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለጣሊያን “ለቤተክርስቲያን እና ለማህበራዊ ህይወት” ላሳዩት “ዘላቂ ትኩረት” ምስጋናቸውን ገልጸዋል፣ እንዲሁም ፕሬዝዳንት ሰርጂዮ ማታሬላን ለአገሪቱ ደጋፊ ቅዱሳን ፍራንችስኮስ እና ለሲዬና ካትሪን ጥበቃ አደራ ሰጥተዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሐሙስ፣ ሐምሌ 15/2018 ዓ.ም 85ኛ የልደት በዓላቸውን ምክንያት በማድረግ ለጣሊያን ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት በላኩት የቴሌግራም መልእክት ይህንን ምኞታቸውን ገልጸዋል። መልእክቱ የሊቀ ጳጳሱን መልካም ምኞት እንዲሁም ለፕሬዚዳንት ማታሬላ ቤተሰብ፣ ለባልደረቦቻቸው እና “ለተወደደችው ጣሊያን” ሐዋርያዊ ቡራኬያቸውን አስተላልፈዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ የጣልያኑ ፕሬዝዳንት ኦፊሴላዊ መኖሪያ የሆነውን የኩዊሪናሌ ቤተ መንግሥትን እ.አ.አ በጥቅምት 14 ቀን 2025 ዓ.ም ጎብኝተው ነበር፣ እዚያም በአውሮፓ ውስጥ ባሉ ቤተሰቦች ላይ በብዝሃ-ወገንነት እና ድጋፍ ላይ ያተኮረ ንግግር አድርገዋል፤ በአውሮፓ አህጉር የውልደት መጠን “በከፍተኛ ሁኔታ እየቀነሰ” መሆኑን ተናግረው እንደ ነበረም ይታወሳል።
በተጨማሪም በአሁኑ ጊዜ ዓለምን እያስጨነቁ ያሉትን ጦርነቶች በማጤን “ፕላኔታችንን እያወደሙ ባሉ በርካታ ግጭቶች” ውስጥ “ያለ ርህራሄ ሞትንና ጥፋትን የሚያቅዱ ሰዎች ምክንያታዊ ባልሆነ ጭካኔ” የተበደሉትን ሰዎች ፊት እንዲመለከቱ እና ጩኸታቸውን እንዲያዳምጡ አሳስበዋል።
ፕሬዝዳንት ማታሬላ በበኩላቸው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ “የሰው ልጅ ማዕከላዊነት” እና ውይይት ለማድረግ ያላቸውን ቁርጠኝነት አጉልተው ገልጸዋል። ፕሬዝዳንቱ ይህንን ቁርጠኝነት ለሊቀ ጳጳሱ በተላኩት መልዕክቶች ላይ በተደጋጋሚ ደግመው አወድሰዋል፤ ከእነዚህም መካከል የቅዱስ ጴጥሮስ መንበር ተተኪ ሆነው ተመርጠው አገልግሎታቸውን የጀመሩበትን የመጀመሪያ ዓመት እና የፋሲካ በዓልን የሚያከብሩበትን ሌላ በዓልን ጨምሮ እነዚህን መልካም ምኞታቸውን ለቅዱስነታቸው መግለጻቸው ይታወሳል።
