ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ልክ ወደ ምንጩ እንደሚመራ ጅረት፣ መዝሙር ወደ እግዚአብሔር ይመራናል አሉ!
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
ሙዚቃ ከምሥጢር ወሰን በላይ ሊመራን ይችላል። ልክ አንድ ጅረትን የሚከተል ሰው በመጨረሻ ምንጩ ላይ እንደሚደርስ ሁሉ፣ የመዝሙር ውበት ወደ እግዚአብሔር ሊመራን ይችላል፣ ዓለም ራሱ ሊጠግነው የማይችለውን የትርጉም እና የደስታ ጥማትን ያረካል ሲሉ ቅዱስነታቸው ተናግረዋል።
ይህ ምስል ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሐምሌ 22/2018 ዓ.ም በካስቴል ጋንዶልፎ ጳጳሳዊ የአትክልት ስፍራዎች ውስጥ በቦርጎ ላውዳቶ ሲ በተካሄደው የሰላም ድምጽ ዘማሪዎች ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር የሰጡት ጭብጥ ሐሳብ ነበር።
በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ የተገለጸውን "መላእክት እና ቅዱሳን መዘምራንን" በማስታወስ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ "ቃል በቃል ሁልጊዜ አይዘምሩም ነበር" ብለዋል። ይልቁንም ፍጹም የሆነ የመዝሙር ለዛ የሚመነጨው ከእግዚአብሔር ጋር ካላቸው የጋራ ማሰላሰል ነው - ምድራዊ ሙዚቃም እኛን ለመቅረብ የሚረዳን ለዛ አለው ሲሉ ተናግረዋል።
ከቅድስት ምድር፣ ከኡጋንዳ እና ከጣሊያን፣ በአንድነት
በላውዳቶ ሲ የከፍተኛ ትምህርት ማዕከል ከአቶ አንድሪያ ቦቼሊ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር የተደራጀው እና በታዋቂው በሙዚቃ ውስጥ ከቀጭን መለስ ከወፍራም ቀጠን ያለ የወንድ ድምጽ ራሱ የተወከለው፣ ዝግጅቱ የአዚዚ የቅዱስ ፍራንችስኮስ ሞት 800ኛ ዓመት ክብረ በዓልን የሚያከብር የቅዱስ ፍራንችስኮስ ጽሑፎችን ያካትታል።
ንባቦቹ እንደ የፍጡራን መዝሙር፣ ከቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ እና ከቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እስከ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ያሉ፣ የቅዱስ ፍራንችስኮስ ጽሑፎችን እና ከብዙ ሊቃነ ጳጳሳት የተወሰዱ ቃላትን ያካትታሉ - ከቅዱስ ጳውሎስ 6ኛ እና ከቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እስከ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ድረስ ማለት ነው።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ስብሰባውን “የደስታ አጋጣሚ” ሲሉ አቶ አንድሪያ ቦቼሊ እና የABF ድምጽ መዘምራንን በማጀባቸው አመስግነዋል፣ ከቅድስት ምድር፣ ከኡጋንዳ እና ከጣሊያን የተውጣጡ 164 ልጆች እና ወጣቶችን ያቀፈ ነው። በሙዚቃ ፍቅራቸው አንድ ላይ በመሆን ብዙዎቹ በጦርነት፣ በድህነት እና በመከራ የተሞላ ሕይወት ይጋራሉ።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በስብሰባው መጨረሻ ላይ ከሚቀርበው ባለብዙ ቋንቋ ጸሎት ጋር፣ ሙዚቃ የተለያዩ ድምጾችን ወደ አንድ የስምምነት ለዛ እንዴት እንደሚያስተሳስር እና እያንዳንዱ ሰው ለጠቅላላው ልዩ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ እንዳሳየ ገልጸዋል። በዚህ መንገድ፣ የመዘምራን ቡድኑ የስምምነት ለዛ እና የትብብር ምልክት ይሆናል።
ከግለሰቡ የሚበልጥ ነገር
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሱ በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ በተገለጹት ሰማያዊ "መዘምራን" ላይ በማሰላሰል፣ አንድነታቸው የሚመጣው በእግዚአብሔር ውስጥ "የደስታ ሙላት" ከማግኘት እንደሆነ ተናግረዋል።
ቀጥለውም ሲዘምሩ፣ ሙዚቃ ሁላችንንም ወደ አዲስ ተሞክሮ እንዴት እንደሳበን ገልጸዋል፣ ከእኛ መካከል ማንኛችንም ብቻችንን ልንፈጥረው ከምንችለው ነገር በላይ፣ የውበት ተሞክሮ ይህ ነው። አዲስ አድማስ ይከፍታል እና በውስጣችን ወደ እሱ የመሄድ ፍላጎትን ያነቃቃል ሲሉ ቅዱስነታቸው ተናግረዋል።
ወደ ምንጩ እንደሚሄድ ጅረት
ወደዚያ አድማስ መሄድ ማለት "አንድ ነገር" ብቻ ሳይሆን "አንድ ሰው" ማግኘት ማለት ነው። "ጅረትን ወደ ምንጩ መመለስ እንደምንችል ሁሉ፣ የሙዚቃ ውበትም ውበት የሆነውን ሰው እንድንገናኝ ይጋብዘናል። እግዚአብሔር የሰጣችሁን ስጦታዎች ማዳበራችሁን ቀጥሉ፣ እናም ወደ እርሱ እንዲመሩአችሁ ፍቀዱ" ሲሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ተናግረዋል።
ዓለም የትርጉም ጥማታችንን ማርካት አይችልም
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የወጣቶችን "እረፍት የሌላቸው ልቦች እንዳሉ" አምነው ተቀብለዋል፣ "በሕይወት የምንፈልገውን ሁሉ" በእውነት ሊያሳርፍ የሚችለው ጌታ ብቻ እንደሆነ ተናግረዋል። "ለታላላቅ ነገሮች እንደተፈጠራችሁ እና መላው ዓለም የትርጉም እና የደስታ ጥማችሁን ለማርካት በቂ እንዳልሆነ አስታውሱ" ሲሉ ተናግረዋል።
"ቅዱስ አባታችሁ ይወዳችኋል እና ይጸልያችኋል"
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ከዚያም ለወጣቶቹ የግል ማረጋገጫ ሰጥተዋል፡- "ቅዱስ አባታችሁ ይወዳችኋል እና ለእናንተ፣ ለቤተሰቦቻችሁ እና ለአገሮቻችሁ ይጸልያሉ" ሲሉ የተናገሩት ቅዱስነታቸው ቃላቶቻቸው የሰላም ጸሎት ሆነዋል፣ "በዓመፅ ምክንያት እየተሰቃዩ ባሉ የዓለም ክፍሎች ሁሉ" እንዲነግስ መጸለያችንን እና መዘመራችንን ልንቀጥል ይገባል ብለዋል።
ለወጣት ተሳታፊዎች፣ ከሊቀ ጳጳሱ ጋር አብረው መጸለይ የአስር ቀናት ጉዞ ውጤት ሲሆን በዚህ ወቅት መዘምራንና አስተማሪዎች በመዘመር ጥበብ የመመስረት፣ የወዳጅነት እና የወንድማማችነት ልምድን አካፍለዋል።
የአቶ አንድሪያ ቦቼሊ ፋውንዴሽን ቁርጠኝነት
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የትምህርት እና የማህበራዊ ችግር ያለባቸውን ወጣቶችን በመደገፍ ላደረጉት ስራ የአቶ አንድሪያ ቦቼሊ ፋውንዴሽንን በማመስገን ደምድመዋል።
"በሙዚቃ ኃይል፣ ለቤተክርስቲያኒቱ የጋራ ጥቅምን ለማገልገል የእያንዳንዱን ሰው ሁለንተናዊ እድገት ለማስተዋወቅ ተልዕኮ አስተዋጽኦ እያደረጉ ነው። እግዚአብሔር ጥረታችሁን ይባርክ" ሲሉ ቅዱስነታቸው ተናግረዋል።
"በማቱሳላ" ጥላ ስር
የጸሎት ስብሰባው የተጀመረው በቅርቡ እ.አ.አ በመስከረም 1/2026 ዓ.ም ጀምሮ በቫቲካን የተቀናጀ የሰው ልጅ ሐብት ልማት ለማስተዋወቅ የሚሰራው የቅድስት መንበር ጽ/ቤት ዋና ፕሬዝደንት ሆነው በተሾሙት ካርዲናል ፋቢዮ ባጂዮ ሲሆን የላውዳቶ ሲ የከፍተኛ ትምህርት ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ሆነው እያገለገሉ ናቸው።
ሙዚቃው ከመጀመሩ በፊት ካርዲናሉ "ማቱሳላ" በመባል የሚታወቀውን ጸጥ ያለ ግን ኃይለኛ ምስክርነት ላይ አስተንትኖ አድርገዋል። በጳጳሳዊ የአትክልት ስፍራዎች ታሪክ ውስጥ የተመሰረተው ይህ ዛፍ ለእያንዳንዱ ወንድና ሴት የተሰጠውን ኃላፊነት ያመለክታል፡- "ለወደፊቱ ትውልዶች ሕይወትንና ተስፋን እንዲያመነጭ እንደ ስጦታ አድርገን ለመንከባከብ ይረዳናል" ብለዋል።
ካርዲናል ባጂዮ የቅዱስ አውጉስጢኖስን የማይረሱ ቃላት አስታውሰዋል፡- "የጥንቱንም፣ የአሁኑንም ውበት ዘግይቼ ቢሆን ወድጃለሁ" በማለት የተናግረውን ቃል አስታውሰዋል።
እንዲሁም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በሥፍራ በመገኘታቸው አመስግነዋል፣ ሰላም "ለእያንዳንዳችን የተሰጠ ተልእኮ" እንደሆነ ለተሰበሰቡት ሰዎች አስታውሰዋል።
ፍጥረት፣ ሰላም፣ ሰብዓዊ ክብር እና እምነት
የፕሮግራሙ የመጀመሪያ ክፍል በፍጥረት ላይ ያተኮረ ሲሆን በአቶ አንድሪያ ቦቼሊ እና በመዘምራኖቹ የተከናወኑ የፓኒስ አንጀሊኩስ እና የዶልቼ ሴንቲሬ ትርኢቶችን አሳይቷል። እህት አሌሳንድራ ስመሪሊ ከዚያም ከቅዱስ ፍራንችስኮስ የፍጥረታት መዝሙር ክፍል የተወሰደውን ክፍል አነበቡ፣ ከዚያም የካርዲናል ባጂዮ ከኦሪት ዘፍጥረት መጽሐፍ የመጀመሪያ ምዕራፍ ጥቅሶችን ወስደው በእንግሊዝኛ ቋንቋ ዝማሬ አሰምተዋል።
ሁለተኛው ክፍል በሕዝቦች መካከል ስምምነትን ለመፍጠር የተመደበ ሲሆን የጂያኒ ሮዳሪ ግጥም "ዘ ሙን ኦፍ ኪየቭ" የመዘምራን ቡድን የሙዚቃ ዝግጅትን ያካተተ ሲሆን በመቀጠልም ለአዚዚው ምስኪን ሰው ተብሎ የተነገረው ጸሎት፣ የቅድስት ምድር የበላይ ጠባቂ በአባ ፍራንችስኮስ ኢልፖ የተነበበው ነው።
ሦስተኛው ክፍል በሰው ልጅ ክብር ላይ ያተኮረ ነበር። ይህም መዝሙር በእንግሊዜኛው ቋንቋ "Singing All Togethe" (ሁሉም በአንድ ላይ መዘመር) የተሰኘው የመዝሙር ትሪት ሲሆን የቀድሞ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራችስኮስ በጣሊያነኛ ቋንቋ "Fratelli tutti" (ሁላችንም ወንድማማቾች ነን)፣ የቅዱስ ጳውሎስ ስድስተኛ እ.አ.አ. በጥቅምት 4/1965 ዓ.ም ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያደረጉትን ንግግር እና የቅዱስ ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ እ.አ.አ በግንቦት 13፣ 1985 በሄግ በሚገኘው የሰላም ቤተ መንግሥት ለዓለም አቀፍ የፍትህ ፍርድ ቤት ያደረጉትን ንግግር ያካትታል።
አራተኛው እና የመጨረሻው ክፍል፣ ለእምነት እና ለአንድነት የተሰጠ፣ የጋኤሊክ ቡራኬ ( ይህ ግጥም የተፈጥሮ አካላት በሆኑት (ውሃ፣ አየር፣ ምድር፣ ሰማይ፣ በእነዚህ በአራቱ አካላት አማካኝነት ሰላምን በማነሳሳት ፍጹም ስምምነት እንዲሰፍን ይጥራል) በዚህ የሰላም መዝሙር ትርኢት እና የዮሐንስ ወንጌል ምዕራፍ 20 ንባብን ያካተተ ነበር።
የሕጻናት ልጆቹ ጸሎት
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በወቅቱ ያደረጉትን አስተንትኖ ካበቁ በኋላ ልጆቹ በተለያዩ ቋንቋዎች የሚከተሉትን ጸሎቶች በንባብ አቅርበው ነበር . . .
“አባት ሆይ፣ እኛ ልጆች ነን። የምንጠይቀው መጫወት እንድንችል ብቻ ነው። ለዚህም ነው በፍቅርህ ተከበን እና ቅዱስ ፍራንችስኮስ ወንድም እና እህት ብለን እንድንጠራቸው ካስተማረን እያንዳንዱ ፍጡር ጋር በመስማማት በደስታ የምንኖርበትን ውብ የአትክልት ስፍራ የፈጠርክልን። የአትክልት ስፍራውን መንከባከብ አልቻልንም፣ እናም በውስጡ የመኖር ደስታ ወደ አንተ ፍርሃት ተለውጧል፣ ስለዚህ ራሳችንን ሸሸግን። ነገር ግን ፍቅርህ ልክ እንደ መደበቅ እና መፈለግ ጨዋታ አገኘን። ኢየሱስ በመስቀል ላይ በከፈለው መስዋዕትነት፣ ከአንተ ጋር አስታረቀን፣ እርስ በርሳችን እና ከሁሉም ፍጥረት ጋር ያለንን ግንኙነት መልሰሃል። በእውነተኛ ደስታ እንድንኖር የአትክልት ስፍራውን እንድንከባከብ እንድትረዳን እንለምንሃለን”።
ስብሰባው የተጠናቀቀው በጌታ ጸሎት፣ የሰላም ምልክት እና የሐዋርያዊ ቡራኬ ልውውጥ ነበር። አቶ አንድሪያ ቦቼሊ እና የመዘምራን ቡድኑ ከዚያም አስደናቂ ጸጋን አቅርበዋል፣ ከየትውልድ አገራቸው ልጆች ያዘጋጇቸውን ስጦታዎች ለርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ካቀረቡ በኋላ ዝግጅቱ ተጠናቋል።
