ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በካስቴል ጋንዶልፎ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በካስቴል ጋንዶልፎ   (@Vatican Media)

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ወደ ካስቴል ጋንዶልፎ ሲደርሱ ደማቅ አቀባበል ተደረገላቸው

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በሮም አቅራቢያ ወደምትገኝ ካስቴል ጋንዶልፎ ከተማ እሑድ ሰኔ 28/2018 ዓ. ም. ሲደርሱ የከተማው ምዕመናን ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል። ቅዱስነታቸው ደማቅ አቀባበል ያደረጉላቸውን የካስቴል ጋንዶልፎ ከተማ ምዕመናን ካመሰገኑ በኋላ እንደ ወንድም እና እንደ እህት የመሰብሰብን አስፈላጊነት አስገንዝበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በካስቴል ጋንዶልፎ አደባባይ ለተሰበሰቡት ምዕመናን ሰላምታ ካቀረቡላቸው በኋላ በደቡብ ጣሊያን በምትገኝ የላምፔዱሳ ከተማ ካደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት እና እሑድ ዕለት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ካደረሱ በኋላ በሮም አቅራቢያ ወደሚገኝ ካስተል ጋንዶልፎ ከተማ ከሰዓት በኋላ ተጉዘዋል።

ቅዱስነታቸው በከተማው በሚገኝ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ማረፊያ እስከ ሰኞ ሐምሌ 20/2018 ዓ. ም. ድረስ በመቆየት የዕረፍት ጊዜያቸውን እንደሚያሳልፉ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት መኖሪያ ቤት አስተዳደር መግለጫ አስታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከሐዋርያዊ ሕንጻቸው ለምዕመናን ሰላምታ ሲያቀርቡ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከሐዋርያዊ ሕንጻቸው ለምዕመናን ሰላምታ ሲያቀርቡ   (@VATICAN MEDIA)

አስፈላጊ የመሰብሰቢያ ጊዜ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የዕረፍት ጊዜያቸውን በካስቴል ጋንዶልፎ ለማሳለፍ በመምጣታቸው ደስታውን ለገለጸው የአካባቢው ማኅበረሰብ አጭር ንግግር አድርገዋል። ቅዱስነታቸው በንግግራቸው ለከተማው ነዋሪዎች በሙሉ ሰላምታቸውን እና ምስጋናቸውን አቅርበዋል።   

ቅዱስነታቸው ለምዕመናኑ ባሰሙት ንግግር፥ “እዚህ በመካከላችሁ የሚቀጥሉ ጥቂት ሳምንታትን ለማረፍ፣ ለመጸለይ፣ ለማንበብ እና ስፖርት ለመሥራት በመምጣቴ እጅግ ደስተኛ ነኝ! አንድ ላይ መሰባሰብ ዘወትር አስፈላጊ ነው፤ እዚህ በመገኘታችሁ ደስተኛ ነኝ፤ እንዲሁም በወንድምነት እና በእህትነት ላደረጋችሁልኝ አቀባበል አመሰግናችኋለሁ” ብለዋል።

የቅዱስነታቸው ጸሎት

ቅዱስነታቸው ለካስቴል ጋንዶልፎ ምዕመናን ባሰሙት ንግግር፥  በሚቀጥሉት እሑዶች በኅብረት በሚያቀርቡት የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት እና ሌሎች አጋጣሚዎችም እንደሚያገኙቸው ገልጸው፥ ምዕመናኑን ዘወትር በጸሎት እንደሚያስታውሷቸው ካረጋገጡላቸው በኋላ ‘እግዚአብሔር ዘወትር ከእናንተ ጋር ይሁን!’ በማለት ቡራኬያቸውን ሰጥተዋል።

ቅዱስነታቸው አጭር የዕረፍት ጊዜ በሚያሳልፉበት የካስቴል ጋንዶልፎ ማረፊያቸው
ቅዱስነታቸው አጭር የዕረፍት ጊዜ በሚያሳልፉበት የካስቴል ጋንዶልፎ ማረፊያቸው   (@Vatican Media)

በካስቴል ጋንዶልፎ የሚቆዩት የዕረፍት ጊዜ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሐምሌ 6/2017 ዓ. ም. በቪላኖቫው ቅዱስ ቶማስ ቁምስና መስዋዕተ ቅዳሴን ባቀረቡበት ወቅት ከቁምስናው መሪ ካኅን እና ምዕመናን ጋር ሰላምታ መለዋወጣቸው ይታወሳል።

በቅዱስነታቸው የዕረፍት ጊዜያት ማለትም እስከ ሐምሌ 29/2018 ዓ. ም. ድረስ ባሉት ቀናት ውስጥ  ሳምንታዊው ጠቅላላ የትምህርተ ክርስቶስ አስተምህሮ፣ እሑድ ዕለት በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከሚሰበሰቡት ምዕመናን ጋር የሚያቀርቡት የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት እና በቫቲካን ከልዩ ልዩ እንግዶች ጋር በግል የሚያደርጓቸው ስብሰባዎች እንደማይኖሩ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት መኖሪያ ቤት አስተዳደር መግለጫ አስታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በሐምሌ ወር ውስጥ የሚመሩት የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት በካስቴል ጋንዶልፎ ከተማ በሚገኘው ፒያሳ ዴላ ሊበርታ ላይ ከሚሰበሰቡት ምዕመናን ጋር የሚቀርብ መሆኑን መግለጫ አክሎ አስታውቋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ደማቅ አቀባበል ያደረጉት የካስቴል ጋንዶልፎ ከተማ ምዕመናን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ደማቅ አቀባበል ያደረጉት የካስቴል ጋንዶልፎ ከተማ ምዕመናን   (@VATICAN MEDIA)
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለካስቴል ጋንዶልፎ ከተማ ምዕመናን ንግግር ሲያደርጉ

 

07 Jul 2026, 11:50