ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ "የማኅበር ሕይወት የሚቀደሱበት ቦታ ነው" ሲሉ አስገነዘቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለልዩ ልዩ ገዳማዊ ማኅበራት የበላይ አለቆች ጉባኤ በላኩት መልዕክት፥ “ሕይወታቸውን ለወንጌል አገልግሎት የሰጡ ሰዎች ምስክርነታቸውን እንዲያጠናክሩ ድጋፍ አድርጋችኋል” በማለት ምስጋናቸውን ያቀረቡት በሰሜን አሜሪካ የቅድስት መንበር ሐዋርያዊ እንደራሴ ለሆኑት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል ካቻ በጻፉት መልዕክት ሲሆን፥ አቡነ ገብርኤል በስብሰባው ላይ ለተገኙት የማኅበራት የበላይ አለቆች የቅዱስነታቸውን መልዕክት በንባብ አቅርበዋል።
“በክርስቶስ አንድ በመሆን የምንኖረው የማኅበር ሕይወት” በሚል መሪ ቃል በአሪዞና ግዛት የሚከበረው የማኅበራት የበላይ አለቆች ጉባኤ 70ኛ መታሰቢያ የሚያከብረው ከሐምሌ 13-16/2018 ዓ. ም. ድረስ እንደ ሆነ ታውቋል።
የወንዶች ገዳማውያን ማኅበራት የበላይ አለቆች ብሔራዊ ጉባኤ (CMSM) በሰሜን አሜሪካ ውስጥ የሚገኙ ልዩ ልዩ ገዳማት እና ሐዋርያዊ ሕይወት ተቋማት መሪዎችን የሚወክል ብሔራዊ ጉባኤ እንደሆነ ይታወቃል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለጉባኤው ሥራ አስፈፃሚ ዳይሬክተር ለአባ ፍራንክ ዶኒዮ ሐምሌ 9/2018 ዓ. ም. በጻፉት መልዕክት፥ “በሰሜን አሜሪካ ውስጥ በሚገኙ ገዳማውያን መካከል ትብብርን በማበረታታት በሰባ ዓመታት ለተቀበሏቸው ጸጋዎች እግዚአብሔርን ለማመስገን ተገቢ ጊዜ ነው” ብለዋል።
ርዕሥ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ብሔራዊ ጉባኤው ለውይይት ቦታን በመስጠት እና የማኅበራት የአመራር አባላትን ለመደገፍ ላደረገው ጥረት አመስግነው፥ ይህም “ሕይወታቸውን ለወንጌል አገልግሎት የሰጡ ሰዎች ኢየሱስ ክርስቶስን እና ምሳሌውን እንዲከተሉ እና ምስክርነታቸውንም ለማጠናከር አስተዋጽኦ እንዳደረገላቸው ተናግረዋል።
በዘንድሮው የስብሰባ ጭብጥ ላይ በማሰላሰል በጻፉት መልዕክታቸው፥ “የማኅበር ሕይወትን የሚቀደሱበት፥ በሐዋርያዊ አገልግሎት ውስጥ የመነሳሳት፣ የምስክርነት እና የጥንካሬ ምንጭ አድርገው እንዲቆጥሩት ለማድረግ እፈልጋለሁ” ብለዋል።
ቀጥለውም “ከሞት የተነሣው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመካከላችሁ የሚገለጠው ቁሳዊ ነገሮችን ጨምሮ መንፈሳዊ ልምዶችን፣ ሐዋርያዊ አስተሳሰቦችን እና በጎነትን በጋራ በመካፈል ነው” ሲሉ አስረድተው፥ በዚህ ሃሳባቸውም “እነዚህ የአስተንትኖ፣ የውይይት እና የጸሎት ቀናት በተቋማቶቻችሁ መካከል ያለውን የወንድማማችነት ኅብረትን በማጠናከር በምታገለግሉባቸው ልዩ ልዩ ማኅበራት እና ሐዋርያነት ውስጥ አንድ ላይ ሆናችሁ ለኢየሱስ ክርስቶስ አስደሳች እና እውነተኛ ምስክርነት ማቅረብን እንድትቀጥሉ ያስችላችኋል” ብለዋል።
ቅዱስነታቸው በመጨረሻም ለጉባኤው አባላት ያላቸውን ቅርበት በማረጋገጥ፥ ብሔራዊ ጉባኤውን የቤተ ክርስቲያን እናት ለሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ፍቅራዊ አማላጅነት አደራ በመስጠት፥ ጉባኤውን ለሚሳተፉት ሁሉ እንዲሁም ለሚወክሏቸው ማኅበራት ሐዋርያዊ ቡራኬያቸው በመስጠት መልዕክታቸው ደምድመዋል።
