ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በካስቴል ጋንዶልፎ የነበራቸውን የእረፍት ጊዜያቸውን አጠናቀዋል።
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሰኞ ምሽት፣ ሐምሌ 21/2018 በኢትዮጲያ የሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 1፡30 በኋላ ከካስትል ጋንዶልፎ የወጡ ሲሆን፣ ሰኔ 28/2018 ዓ.ም ከጀመረው የእረፍት ጊዜ በኋላ ወደ ቫቲካን ተመልሰዋል።
መኪናቸው ከጳጳሳት የመኖሪያ ቤት ሲወጣ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በሥፍራው ለተገኙ ሰዎች ሰላምታ ማቅረባቸው የተገለጸ ሲሆን በሥፍራ ከወላጆቻቸው ጋር የነበሩትን በርካታ ሕጻናት ልጆችን ባርከዋል።
ረቡዕ፣ ሐምሌ 22/2018 ዓ.ም “የሰላም መዝሙር" የተባለውን የጸሎትና የወንድማማችነት ስብሰባ ላይ ለመገኘት ወደ ካስቴል ጋንዶልፎ ይመለሳሉ።
በላውዳቶ ሲ የከፍተኛ ትምህርት ማዕከል እና በአቶ አንድሪያ ቦቼሊ ፋውንዴሽን የተደገፈው ይህ ዝግጅት የአዚዚ የቅዱስ ፍራንችስኮስ ሞት 800ኛ ዓመት ክብረ በዓልን የሚያከብር የበዓላት አካል ነው። በጳጳሳዊ ቪላዎች የአትክልት ስፍራዎች ከምሽቱ 2፡00 ሰዓት ላይ ይጀምራል።
በካስትል ጋንዶልፎ የነበራቸው ቆይታ
በካስትል ጋንዶልፎ በ23 ቀናት ቆይታቸው፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ለጸሎት፣ ለንባብ እና ለስፖርት ጊዜ ሰጥተዋል። ከሮም ከተማ ውጭ በአልቦኖ ኮረብቶች ውስጥ አልባኖ ሐይቅ የሚገኝበት ትንሽ ከተማ ሲሆን፣ ከጣሊያን እጅግ ውብ መንደሮች መካከል አንዱ ነው።
ከምዕመናን ጋር አራት ዕለተ ሰንበቶችን ከማሳለፋቸው በተጨማሪ - ሰኔ 28፣ ሐምሌ 5፣ ሐምሌ 12፣ ሐምሌ 19/2018 ዓ.ም የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት ከሐዋርያዊ የመኖሪያ ሥፍራቸው መግቢያ ላይ ሆነው መርተው የነበሩት፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በሁለት ሌሎች የሕዝብ ዝግጅቶች ላይ ተሳትፈዋል።
ሐምሌ 4/2018 ዓ.ም፣ ከሮም ሀገረ ስብከት ከመጡ 200 ሰዎች ጋር በጳጳሳዊ የአትክልት ስፍራዎች ምሳ ተጋብዘዋል፣ ከእነዚህም ውስጥ 35 ልጆች ይገኙበታል።
ከሳምንት በኋላ፣ ሐምሌ 11/2018 ዓ.ም፣ በሐዋርያዊ የመኖሪያ ቤታቸው ግቢ ውስጥ በአልባኖ ሀገረ ስብከት በተዘጋጀ ኮንሰርት ላይ ተገኝተዋል።
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በቆይታቸው የመጨረሻ ሳምንት ለሦስት የግል ጉብኝቶች ሁለት ጊዜ ጉዞ አድርገዋል። ሐምሌ 13/2018 ዓ.ም የሞንቴካሲኖ የቅዱስ ቤነዲክቶስ ገዳምን ጎብኝተዋል። ሐምሌ 16/2018 ዓ.ም በሱቢያኮ የሚገኙትን የቅዱስ ቤኔዲክት እና የቅዱስ ስኮላስቲካ ገዳማትን ከመጎብኘታቸው በፊት በቫሌፒትራ ወደሚገኘው የቅድስት ሥላሴ መቅደስ ተጉዘው ነበር።
