ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ የኢራቅ ወጣቶች በጦርነት በቆሰለው ዓለም የክርስቶስ ብርሃን እና ተስፋ እንዲሆኑ አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከኢራቅ ልዩ ልዩ አካባቢዎች ተሰባስበው በኤርቢል ሀገረ ስብከት አንካዋ ከሐምሌ 1-4/2018 ዓ. ም. ድረስ ዓመታዊ ስብሰባ በማድረግ ላይ ለሚገኙት ወጣቶች የማበረታቻ መልዕክት ልከዋል። ወጣቶቹ የተስፋ መልዕክተኛነት ጥሪያቸውን ተቀብለው ጦርነት እና አለመረጋጋት ባለበት አገራቸው ውስጥ “የክርስቶስ ብርሃን” እንዲሆኑ አሳስበዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ዘንድሮ “ተልዕኮ” በሚል መሪ ቃል በአንካዋ በተዘጋጀው ስብሰባ ላይ ለተገኙት ወጣቶች በላኩት የቪዲዮ መልዕክት፥ ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ሕይወት ውስጥ ወጣቶች የማይተካ ሚና እንዳላቸው አስታውሰዋል።
“ቤተ ክርስቲያን የኢየሱስ ክርስቶስን ብርሃን ወደ ዓለም ሁሉ ለማድረስ የተቀበለችው ወሳኝ ተልዕኮ አላት” ሲሉ ተናግረው፥ ወጣቶቹ በሚመጡት ዓመታት ውስጥ ቤተ ክርስቲያንን እና ዓለምን በወንጌል ተልዕኮ እንዲቀርጹ አበረታተዋል።
ቅዱስነታቸው ቀደም ሲል የገለጹትን እምነት በማስታወስ፥ “ወጣቶች የቤተ ክርስቲያኗ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ብቻ ሳይሆኑ የዛሬውም ጭምር ናቸው” ብለው፥ በርካታ የኢራቅ ክርስቲያኖች አሁንም እያጋጠማቸው ያለ አስቸጋሪ እውነታንም በመገንዘብ፥ የወንጌል ምስክርነት ከፍተኛ ጥረትን የሚጠይቅ መሆኑን አስረድተዋል።
“በዓለም ውስጥ ብርሃን መሆን ቀላል አይደለም” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ “ሆኖም ይህንን ብርሃን ብዙውን ጊዜ ጦርነት እና አለመረጋጋት በተስፋፋበት ሁኔታ ውስጥ ለማብራት ተጠርታችኋል” ሲሉ ወጣቶችን አበረታተዋል።
“ፍራሃት አይዛችህ!”
ወጣቶቹ ተስፋ እንዳይቆርጡ በጥብቅ ያሳሰቡት ቅዱስነታቸው፥ በዚህ ተግባራቸው ብቸኝነት እንዳይሰማቸው በማሳሰብ፣ እኔ እና ቤተ ክርስቲያን ከእናንተ ጋር ስለሆንን አትፍሩ! በኢየሱስ እመኑ” ሲሉ አሳስበዋል።
“ተልዕኮ” በሚለው የስባሰባው መሪ ቃል ላይ ለማሰላሰል ብርሃንን እንደ ምሳሌ ያቀረቡት ቅዱስነታቸው፥ እያንዳንዱ ክርስቲያን ደቀ መዝሙር ሊቀረጽበት የሚገባቸው ሦስት ባህሪያትን እነርሱም እምነት፣ ፍቅር እና ተስፋ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ብርሃን አንድን ነገር ለማየት እንደሚያስችል፥ እምነትም ለሕይወት ችግሮች ምላሽ ብቻ ሳይሆን እውነታን ለማወቅ እና በእውነት ለመኖር፣ ይህም አማኞች ዓለምን፣ ሌሎችን እና ራሳቸውን በእግዚአብሔር ዓይን እንዲመለከቱ፣ ወጣቶችም ወንጌልን በሚኖሩት የሕይወት መንገድ እንዲመሰክሩ፣ ሌሎችም የሚፈልጉትን እውነት እና ትርጉም እንዲያገኙ ያስችላቸዋል” ብለዋል።
ብርሃን ሙቀትንም ጭምር የሚሰጥ በመሆኑ የእግዚአብሔር የፍቅር ምልክት በማድረግ፥ “እውነተኛ ተልዕኮ የሚጀምረው በምንፈጽማቸው ሥራዎች ሳይሆን በየቀኑ በምናቀርበው ጸሎት እና በቅዱሳት ምስጢራት በተለይም በንስሐ እና በቅዱስ ቁርባን አማካኝነት በሚደረግ የግል ግንኙነት ነው” ሲሉ አስረድተዋል።
የእግዚአብሔርን ፍቅር መሠረት ማድረግ
“ልባችሁን እግዚአብሔር ለእናንተ ባለው ጠንካራ የፍቅር መሠረት ላይ አድርጉት” ሲሉ አጥብቀው ያሳሰቡት ቅዱስነታቸው፥ “የክርስቶስን ልብ ፈልጉ፣ ሕይወታችሁንም በእርሱ ላይ መገንባትን አትፍሩ” ሲሉ መክረው፥ መሠረታቸውን በእግዚአብሔር ፍቅር ላይ የገነቡት ብቻ በዙሪያቸው ካሉ ሰዎች ጋር የእግዚአብሔርን ፍቅር እና የጸጋውን የማስታረቅ ኃይል ለሌሎች ማካፈል ይችላሉ” ብለዋል።
በመጨረሻም ብርሃንን የዕድገት እና የተስፋ ምልክት አድርገው ባቀረቡት መልዕክታቸው፥ እርቅን በሚናፍቅ ክልል ውስጥ ክርስቲያን ወጣቶች የሰላም ፈጣሪዎች ለመሆን የተጠሩ እንደሆኑ አስረድተው፥ “በተለይ በዙሪያችሁ ያሉትን አንድ ለማድረግ እና ዘላቂ ሰላም የሰፈነበት የወደፊት ተስፋን ወደ ሌሎች ዘንድ ለማምጣት ተጠርታችኋል” ሲሉ አሳስበዋል።
ወጣቶቹ የሚገኙበትን ሁኔታ ሁልጊዜ መቆጣጠር ባይችሉም ነገር ግን የክርስቶስ ሰላም ልባቸውን እንዲገዛ መፍቀድ እንደሚችሉ አሳስበው፥ “ይህም ከሞት ከተነሳው ኢየሱስ ክርስቶስ የሚመጣ የተስፋ ምልክት ይሆናል” ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በመልዕክታቸው ማጠቃለያ፥ ወጣቶቹን የቤተ ክርስቲያን እናት ለሆነች እመቤታችን ማርያም እናታዊ እንክብካቤ አደራ ሰጥተው፥ ወጣቶቹ ለእግዚአብሔር ፍቅር እንዲታመኑ በማበረታታት፥ ቸርነቱን ፈጽሞ እንዳይጠራጠሩ እና ለሕይወታችው ያለውን እቅድ እንዳይፈሩ በማሳሰብ፥ ነቢዩ ኤርምያስ በትንቢቱ፥ “እግዚአብሔር ተስፋ ያለውን ሕይወት ሊሰጣችሁ ይፈልጋል” ሲል የተናገረውን አስታውሰዋል።
