የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በካስቴል ጋንዶልፎ የሚገኘውን የ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” መንደር ሲባርኩ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በካስቴል ጋንዶልፎ የሚገኘውን የ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” መንደር ሲባርኩ   (@Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ በስማቸው የተዘጋጀውን የዘላቂ አስተዳደር የሜዳሊያ ሽልማት እንደሚሰጡ ተገለጸ

በሰሜን አሜሪካ የሚገነኘው የቪላኖቫ ዩኒቨርሲቲ በዘላቂ አስተዳደር እና ሁለገብ የሰው ልጅ ልማት የላቀ አመራር ላሳዩት ግለሰቦች እውቅናን ለመስጠት ያዘጋጀውን የክብር ሜዳሊያ ማዘጋጀቱን አስታውቋል። ዩኒቨርሲቲው በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ስም የተዘጋጀውን ሜዳሊያ ለተሸላሚዎቹ የሚሰጠው በያዝነው የጎርጎሮሳውያኑ 2026 ዓ. ም. ለመጀመሪያ ጊዜ በሮም እና በካስቴላ ጋንዶልፎ በሚካሄደው የቪላኖቫ ዓለም አቀፍ የዘላቂ አመራር ጉባኤ ላይ እንደሚሆን ታውቋል። ለተሸላሚዎቹ የተዘጋጀውን ሜዳሊያ የሚያበረክቱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እንደሚሆኑ ታውቋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በሰሜን አሜሪካ የሚገኘው የቪላኖቫ ዩኒቨርሲቲ በሥሩ ከሚገኘው የዘላቂ አስተዳደር ቢሮ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የዘላቂ አመራር ሜዳሊያው፥ በመሪነታቸው የላቀ ዘላቂነትን፣ ሥነ ምህዳራዊ ኃላፊነትን እና የተቀናጀ የሰው ልጅ ልማትን ላሳዩት ግለሰቦች የሚሰጥ አዲስ ዓለም አቀፍ የክብር ሽልማት እንደሆነ ታውቋል።

የቪላኖቫ ዩኒቨርሲቲ በመግለጫው ላይ እንዳስረዳው፥ “ሜዳሊያው ዘላቂነት ባለው ጠቅላላ ራዕይ ለአካባቢ እንክብካቤ፣ ለማኅበራዊ ፍትህ፣ ተጋላጭ ለሆኑ ሕዝቦች ባለው አሳቢነት እና ለኢኮኖሚያዊ እና የተፈጥሮ ሃብቶች ኃላፊነት ያለውን አመራር ለሚያሳዩ ሰዎች ክብር ለመስጠት ባለው ፍላጎት ነው” ሲል ገልጿል

በአሜሪካ ውስጥ የሚገኘው ይህ የቅዱስ አጎስጢኖስ ማኅበር ዩኒቨርሲቲ ከቴክኒካዊ መለኪያዎች ይልቅ የተቀናጀ ሥነ-ምህዳርን እንደሚገመግም አክሎ፥ የሜዳሊያው ተሸላሚዎች ከማንኛውም የሥራ ወይም የምርምር መስኮች ሊመጡ እንደሚችሉ እና የበለጠ ዘላቂ እና ፍትሃዊ ዓለምን ለማራመድ ባላቸው ተጽእኖ መሠረት እንደሚመረጡ አስረድቷል።

በዘላቂ አስተዳደር ላይ የሚካሄድ ጉባኤ

በጣሊያን ካስቴል ጋንዶልፎ ከተማ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ስም እና ለምድራችን እና ለድሆች ጩኸት ምላሽ ለመስጠት በሚል ዓላማ ከሰኞ ጥቅምት 2-5/2019 ዓ. ም. ድረስ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄደውን የቪላኖቫ ዓለም አቀፍ የዘላቂ አስተዳደር ሜዳሊያ ጉባኤን የሚከፍቱት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እንደሚሆኑ ታውቋል።

ጉባኤው ምሁራንን፣ ተመራማሪዎችን፣ የቤተ ክርስቲያን ተወካዮችን፣ ፋውንዴሽኖችን እና የመንግሥት እና የግል ዘርፍ መሪዎችን ጨምሮ በግምት 300 ተሳታፊዎችን የሚሰበስብ ሲሆን፥ እንዲሁም ከውይይት ወደ ተጨባጭ የትብብር እርምጃ ለመሸጋገር የተዘጋጀ የሁለትዮሽ የምርምር መድረክ እንዳለው ታውቋል።

የሜዳሊያው አሸናፊዎች ስም ዝርዝር ይፋ የሚደረገው ከጉባኤው በፊት በመስከረም ወር ውስጥ ሲሆን፥ 

የሽልማት አሰጣጡ ሥነ-ሥርዓት በካስቴል ጋንዶልፎ የ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” መንደር ውስጥ እንደሚካሄድ ታውቋል።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የዘላቂ አመራር ሜዳሊያ ሽልማት የሚያተኩረው፥ “በማይነጣጠሉ የጋራ መኖሪያ ምድራችን እንክብካቤ እና የእርስ በርስ መተሳሰብ ጥልቅ እምነት ላይ ነው” ሲሉ የቪላኖቫ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አባ ፒተር ኤም ዶኖሁ ተናግረዋል።

አባ ፒተር በማከልም “ሥራቸው የአካባቢ ጥበቃን እና የጋራ ጥቅምን የሚያበረታታ መሆኑን በመገንዘብ በዓለም ዙሪያ ባሉ ማኅበረሰቦች ውስጥ ትርጉም ያለውን እና ዘላቂ ተጽእኖን እንደምናነሳሳ ተስፋ እናደርጋለን” ብለዋል።

የቪላኖቫ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች

በወቅቱ ሮበርት ኤፍ ፕሬቮስት በመባል የሚታወቁት የዛሬው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እንደ ጎርጎሮሳውያን በ1977 ዓ. ም. ከቪላኖቫ የሳይንስ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪ ማግኘታቸው ሲታወስ፥ ዩኒቨርሲቲው በኋላም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2014 ዓ. ም. በሰብዓዊነት የክብር ዶክተርነት ማዕረግ   መስጠቱ ይታወሳል።

የቪላኖቫ ዩኒቨርሲቲ በየሁለት ዓመቱ የሚሰጠው የሜዳልያ ሽልማት፥ ተቋሙ ዓለም አቀፍ የዘላቂነት አመራር ተነሳሽነት ለማራመድ እና የተዋሃደ ሥነ-ምኅዳር ለማጎልበት ያለው ቁርጠኝነት አካል ሲሆን፥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የ 2026 ዓ. ም. ሽልማት የሚቀበሉት እጩዎች የተመረጡት በዩኒቨርሲቲው የዘላቂነት አመራር ምክር ቤት ባካሄደው የግምገማ ሂደት እንደሆነ ታውቋል።

በፍጥረት እንክብካቤ እና በሰው ልጅ ክብር ማሳደግ መካከል ያለው ትስስር

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ የ2026 ዓ. ም. ዓለም አቀፍ የዘላቂነት አመራር ጉባኤ የሚካሄደው በሮም በሚገኘው “ፓትሪስቲኩም” እና በካስቴል ጋንዶልፎ በሚገኘው “ውዳሴ ላንተ ይሁን” ከፍተኛ የትምህርት ማዕከል መካከል እንደሆነ ታውቋል።

ጉባኤው የሚዘጋጀው የሰው ልጅ ልማትን ከሚያበረታታ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤት፣ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” ከፍተኛ የትምህርት ማዕከልን ጨምሮ በርካታ ተቋማዊ አጋሮች ጋር በመነጋገር ሲሆን፥ በተጨማሪም ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ባቋቋሙት ወሳኝ ሥነ-ምህዳራዊ ምሥረታ እና ዘላቂ ትምህርት ተነሳሽነት እንደሆነ ታውቋል።

የ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” ከፍተኛ የትምህርት ማዕከል ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ፋቢዮ ባጆ ተነሳሽነቱን በደስታ ተቀብለውት፥ “የዘላቂነት አመራር ሜዳልያ ሽልማት ለግለሰቦች የሚሰጠው፥ በእምነት ብርሃን ላይ የተመሠረተ ፍጥረትን በመንከባከብ እና ሰብዓዊ ክብርን በማስተዋወቅ መካከል ያለውን የማይነጣጠል ትስስር በሕይወታቸው ስለሚመሰክሩ ነው” ብለዋል።

ብጹዕ ካርዲናል ፋቢዮ ባጆ በማከልም፥ “ይህን ልዩ ቁርጠኝነት በመገንዘብ ሜዳሊያው መጪው ትውልድ ለምድሪቱ እና ለድሆች ጩኸት ምላሽ ለመስጠት ወሳኝ ሥነ-ምኅዳርን እንዲቀበል መሪዎችን የሚያበረታታ ነው” ብለዋል።

 

21 Jul 2026, 16:58