ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በሞንቴካሲኖ ገዳም ጎብኝታቸው ላይ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በሞንቴካሲኖ ገዳም ጎብኝታቸው ላይ  (@Vatican Media)

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በጣሊያን በሚገኘው የሞንቴካሲኖ ገዳም ውስጥ ስለ ሰላም ጸለዩ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በመካከለኛው ደቡብ ጣሊያን የሚገኝ የሞንቴካሲኖ ገዳም ጎብኝተው ከገዳሙ ማኅበረሰብ ጋር ተገናኝተዋል። ገዳሙን ሰኞ ሐምሌ 13/2018 ዓ. ም. በጎበኙበት ወቅት በገዳሙ መሥራች በቅዱስ ብሩክ መካነ መቃብር ፊት ቀርበው ጸሎት ያደረሱ ሲሆን በጸሎታቸውም፥ “በደም መፋሰስ እና በግጭት በተሞሉ የዓለም ክፍሎች ሰላም እንዲወርድ” የቅዱሱን አማላጅነት ጠይቀዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

በቅድስት መንበር መግለጫ መሠረት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሰኞ ሐምሌ 13/2018 ዓ. ም. ጠዋት ሞንቴካሲኖን ጎብኝተው በገዳሙ በሚገኘው የቅዱስ ብሩክ መካነ መቃብር ፊት በመቅረብ፥ “በደም መፋሰስ እና በግጭት ለተሞሉ የዓለማችን ክልሎች ሰላምን እንዲያማልድ” በማለት ጸሎታቸውን አቅርበው፥ ከገዳማውያኑ ጋር ከተገናኙ በኋላ በምሳ ግብዣ ላይም ተገኝተዋል። በመጨረሻም እስከ ሰኞ ሐምሌ 20/2018 ዓ. ም. ድረስ የበጋ ዕረፍት ወደሚያደርጉበት ካስቴል ጋንዶልፎ ተመልሰዋል።

በሞንቴካሲኖ የሚገኘው የቅዱስ ብሩክ ገዳም ከሮም በመኪና የሁለት ሰዓት መንገድ ሲሆን፥ ገዳሙም በቅዱስ ብሩክ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ529 ዓ. ም. የተመሠረተው የመጀመሪያ ገዳም እንደሆነ ይታወቃል።

የገዳሙ አመሠራረት

በሞንቴካሲኖ ጦርነት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በየካቲት 15/1944 ዓ. ም. የአካባቢው ኃይሎች ቦታው በጀርመን ወታደሮች የተያዘ መስሏቸው በስህተት ባካሄዱት ጦርነት ሙሉ በሙሉ መውደሙ ይታወሳል። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ከጣሊያን መንግሥት በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ እንደገና የተገነባ ሲሆን፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ጳውሎስ ስድስተኛ በ1964 ዓ. ም. በገዳምነት እንዲያገለግል መወሰናቸው ይታወሳል። ሞንቴካሲኖ ዛሬ ከዓለም ዙሪያ የሚመጡ መንፈሳዊ ነጋዲያንን እና ጎብኚዎችን የሚቀበሉ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው የቅዱስ ብሩክ ማኅበር ገዳማውያን የሚገኙበት ቦታ እንደሆነ ይታወቃል።

በአቅራቢያው በሞንቴካሲኖ ጦርነት የተሰው ወታደሮች መታሰቢያ ሲከበር መቃብራቸው የቱ እንደሆነ የማይታወቁ ከ4,000 በላይ የኮመንዌልዝ ወታደሮች እንደሚገኙበት እና እዚያው የተቀበሩት የሌሎች 289 ሰዎች ማንነትም እንደማይታወቅ ታውቋል።

ከገዳሙ አቅራቢያ የፖላንድ ወታደሮች መካነ መቃብርም የሚገኝ ሲሆን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በግንቦት ወር 1944 ዓ. ም. ሞንቴካሲኖ በተያዘበት ወቅት የተገደሉ 1,072 የፖላንድ ወታደሮች መሆናቸው ሲታወቅ፥ በመቃብራቸው ላይ የተተከሉት መስቀሎች እና የዳዊት ኮከቦች በዘመቻው ወቅት የተሰጡ ሰዎች ሃይማኖት የሚገልጹ መሆናቸው ታውቋል።

የ “ፓቺስ ኑንቲየስ” ሽልማት

የሞንቴካሲኖ ጦርነት በተካሄደበት በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ወደ ፍርስራሽነት የተቀየረው እና የጦርነት ውድመት ዘላቂ ምልክት የሆነው የ 2026 ዓ. ም. የ “ፓቺስ ኑቲየስ” ሽልማት ከአሥር ቀናት በፊት ለኢየሩሳሌም የላቲን ፓትርያርክ ብጹዕ ካርዲናል ፒርባቲስታ ፒዛባላ እንደተሰጣቸው ይታወሳል።

 

21 Jul 2026, 16:53