የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ የላምፔዱሳ ጉብኝት በአውሮፓ ድንበር የአንድነት ምስክርነት መሆኑ ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ቅዳሜ ሰኔ 27/2018 ዓ. ም. ጠዋት በ6,000 የሚገመቱ የላምፔዱዛ ደሴት ነዋሪዎች ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛን ለመቀበል በየጎዳናዎች ላይ ተሰልፈው ወደ ስደተኞች የመቃብር ሥፍራ፣ ወደ አውሮፓ የመታሰቢያ ሐውልት እና ወደ ፋቫሎሮ ፒር በሚወስደው መንገድ ላይ ቅዱስነታቸውን በደስታ የተቀበሉ ሲሆን፥ በመጨረሻም ቅዱስነታቸው የስፖርት ሜዳውን ከሞሉት ምዕመምና ጋር መስዋዕተ ቅዳሴን ካቀረቡ በኋላ የአካባቢውን ማኅበረሰብ አመስግነዋል።
በባሕር ዳርቻ ላይ የተገኙት በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ምዕመናን ከስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ጋር ሆነው ላሳዩት አንድነት፥ ለባሕር ላይ አደጋ የተጋለጠ ስደተኛን እንደ ወንድም እና እህት በመቁጠር እርስ በርስ ለመዋደድ በመምረጣቸው አመስግነው፥ አጋርነታቸውን ማሳየት ብቻ ሳይሆን በጉዞአቸው ወቅት ይበልጥ የተቸገሩትን ያገዙ ስደተኞችንም አመስግነዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በመስዋዕተ ቅዳሴው ላይ ባሰሙት ቃለ-ምዕዳን፥ “ወንድሞች እና እህቶች ሆይ! ለሌሎች ለመድረስ ያላችሁ ፍላጎት እንደ ቀላል የሚወሰድ እና በድንገት የሚከሰት ባለመሆኑ አመሰግናችኋለሁ” ብለዋል።
ትንሿ የሲሲሊ ደሴት ከዋናው የጣሊያን ክልል ይልቅ ወደ ቱኒዚያ የባሕር ዳርቻ የምትቀርብ ስትሆን፥ለዘመናት እና በተለይም ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ከሰሜን አፍሪካ አደገኛውን የሜዲትራኒያን ባሕር ለመሻገር ለሚሞክሩ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች ተፈጥሯዊ የመድረሻ ቦታ ሆናለች።
ከጦርነት፣ ከስደት እና ከድህነት የሚሸሹ ሥፍር ቁጥር የሌላቸው ወንዶች፣ ሴቶች እና ልጆች በተለይም እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2011 ዓ. ም. የአረብ የጸደይ አብዮት ንቅናቄ ወቅት እና በ2015 ዓ. ም. የሶርያ ጦርነት ወቅት ወደ ላምፔዱሳ የባሕር ዳርቻ ደርሰዋል። በ2023 በአንድ ሳምንት ውስጥ ብቻ ወደ 10,000 የሚጠጉ ሰዎች ወደ ደሴቲቱ የደረሱ ሲሆን፥ ይህም የላምፔዱሳ ነዋሪ ሕዝብ ቁጥር እጥፍ እንደሚጠጋ ታውቋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ቅዳሜ ሰኔ 27/2018 ዓ. ም. ጠዋት በላምፔዱሳ ያደረጉትን ሐዋርያዊ ጉብኝት በፎቶዎች እና በቴሌቪዥን ምስሎች አማካኝነት የተከታተሉት ሰዎች ምንም ዓይነት ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂ የማይታይበት ሁኔታ መኖሩን ሲገነዘቡ ሳይገረሙ እንዳልቀሩ ተነግሯል። በደሴቲቱ ለመቆየት ከመረጡት እና ነፍስ በማዳን እና አቀባበል በማድረግ ወሳኝ ሚና ከሚጫወቱት በተጨማሪ ወደ ሌሎች የመቀበያ ማዕከላት ከመዛወራቸው በፊት በላምፔዱሳ ማዕከል ከ24 እስከ 48 ሰዓታት ብቻ እንደሚቆዩ ታውቋል።
አውሮፓ እስካሁን ድረስ እጅግ ገዳቢ የሆኑ የስደት ፖሊሲዎቿን እያጠናከረች ባለችበት ወቅት እና በፍጥነት “የመመለሻ ማዕከላት” በመመሥረት ላይ ባተኮረችበት ወቅት፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የላምፔዱሳ ነዋሪዎች በኅብረት ሊያሳኩ በሚችሉት ነገር ትንቢታዊ ምልክት ሆነው እንዲቀጥሉ አበረታተዋል።
መለያየትን እና ልዩነትን በማሸነፍ ኢኮኖሚው የፍጥረት እንክብካቤን እና ማኅበራዊ ወዳጅነትን ዛሬውኑ የሚፈልገው ዓለም በሰብዓዊነት ውህደት ውስጥ አንድ ላይ የሚሰበሰብበትን መሠረት ጥለዋል።
