ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ ሁሉም ሰው በውይይት የጋራ ጥቅምን ማበረታታት እንደሚያስፈልግ አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “Magnifica humanitas” (የሰው ልጅ ታላቅነት) የተሰኘ ሐዋርያዊ መልዕክታቸው ከሰው ሠራሽ አስተውሎት (IA) ጋር ግንኙነት ያላቸውን እና በዘርፉ የሚሠሩን ልዩ ልዩ ሰዎች በማዳመጥ የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸው፥ “አልጎሪዝምን” ያለ አግባብ መጠቀም፥ የሰው ልጅ ወሳኝ በሆኑ ዘርፎች ውክልናውን በማጣቱ በሚወጡ አሳሳቢ ዘገባዎች የተገፋፋ ነው” ሲሉ ረቡዕ ሐምሌ 1/2018 ዓ. ም. ለጉባኤው በላኩት መልዕክት ተናግረዋል።
ቅዱስነታቸው መልዕክታቸውን የላኩት፥ “የሰው ሠራሽ አስተውሎት ለመልካም ዓላማ” በሚል ርዕሥ በጄኔቫ ከሰኔ 30 እስከ ሐምሌ 3/2018 ዓ. ም. ድረስ በመካሄድ ላይ ለሚገኝ ዓለም አቀፍ ጉባኤ እንደሆነ ታውቋል። ጉባኤው የተዘጋጀው በተባበሩት መንግሥታት ዓለም አቀፍ የቴሌኮሙኒኬሽን ኅብረት (ITU) ከሌሎች የተባበሩት መንግሥታት ኤጀንሲዎች እና ከስዊዘርላንድ መንግሥት ጋር በመተባበር ሲሆን፥ ዓላማውም የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ዓለምን እንዴት እየቀረጸው እንደሚገኝ ለመዳሰስ እና ለዓለም አቀፍ ተግዳሮቶች መፍትሄን ለመስጠት ያለመ እንደሆነ ታውቋል።
“ስለ ሰው ልጅ የወደፊት ዕጣ ፈንታ በተመለከተ በዘመናችን ውስጥ አንዳንድ ዋና ዋና ጥያቄዎችን በሚያስነሳው የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ላይ ለማሰላሰል በሚሰበሰቡበት ወቅት፥ በተለይም በዛሬው እና በሚመጣው የለውጥ ዘመን ቅድስት መንበር ለውይይት ዝግጁ እንደ ሆነች ቅዱስነታቸው ማረጋገጥ ይፈልጋሉ” ሲል መልዕክቱ ገልጿል።
በዚህ ረገድ መልዕክቱ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በሰው ሠራሽ አስተውሎት ዘመን የሰውን ልጅ ለመጠበቅ የጻፉት “Magnifica humanitas” (የሰው ልጅ ታላቅነት) የተሰኘ ሐዋርያዊ መልዕክታቸው፥የጋራ ጥቅምን ለማስተዋወቅ የሚያግዙ አዳዲስ መንገዶችን ለመለየት፣ ሁሉም ሰው የተከበረ ሕይወት እንዲኖር እና ከሁሉም ዓይነት ሰዎች ጋር ውይይት ለማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው ይገልጻል።
“Magnifica humanitas” (የሰው ልጅ ታላቅነት) በሚል ርዕሥ የተጻፈው የቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ መልዕክት፥ ከፍተኛ መከራን ለማስታገስ በሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎች ላይ በቅን ልቦና የሚሠሩ የሳይንስ ጠበብቶችን እና መሐንዲሶችን፤ ፍትሃዊ ሕጎችን በጽናት የሚፈልጉ የፖለቲካ መሪዎችን እና የሕዝብ ባለሥልጣናትን፤ ለወጣት ትውልዶች የወደፊት ዕጣ ፈንታ በጥልቅ የሚያስቡ ወላጆችን እና መምህራን በማዳመጥ እንደሆነ ታውቋል።
ሐዋርያዊ መልዕክታቸው በተጨማሪም፥ ሰው ሠራሽ አስተውሎት በሰዎች እና በኅብረተሰቡ ላይ ያሳደረውን አሉታዊ ተጽዕኖ ተመልክቶ የተጻፈ እንደሆነ ታውቋል።
መልዕቱ በመጨረሻም፥ “የጉባኤው ተካፋዮች ገንቢ እና አበራታች በሆኑ ውይይቶች ላይ በመሳተፍ የሰውን ልጅ ለማገልገል የሚያደርጉትን ጥረት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በጸሎት ለማገዝ ያላቸውን ፈቃደኝነት ያረጋግጣሉ” ሲል ደመድሟል።
