ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የሰው ሕይወት አክብሮት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለሐምሌ ወር ያዘጋጁትን ወርሃዊ የጸሎት ሃሳብ ይፋ አድርገዋል። ቅዱስነታቸው ለወሩ ባዘጋጁት የጸሎት ሃሳብ፥ ካቶሊካዊ ምዕመናን ለሰው ሕይወት ክብር እንዲጸልዩ አሳስበው፥ ሁሉም ሰው የእያንዳንዱን ሰብዓዊ ሕይወት ልዩ እና የማይተካ እሴት እንዲገነዘብ እና እንዲጠብቅ አደራ ብለዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በዓለም አቀፍ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት የጸሎት አውታረ መረብ አማካይነት ይፋ ባደረጉት የሐምሌ ወር የቪዲዮ መልዕክት፥ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ካቶሊካውያን በሐምሌ ወር ለሰው ሕይወት ክብር እንዲጸልዩ አሳስበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በጸሎታቸው፥ እግዚአብሔር እያንዳንዱን ሰው በፍቅር ፈጥሮ በሙላት እንዲኖር የጠራው መሆኑን በማስገንዘብ፥ “እያንዳንዱ ሰው ከመጀመሪያው የሕይወት ቅጽበት ጀምሮ እስከ መጨረሻዋ እስትንፋስ ድረስ አንተን የሚመስል ቅዱስ ስጦታ ነው” ብለው፥ “ዛሬ ሁላችንም የእያንዳንዱን ሰው ልዩ እና የማይተካ እሴት ማወቅ እና መጠበቅ የምንችልበትን ጸጋን እንለምናለን” ብለዋል።

ሕይወትን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ መቀበል

ቅዱስነታቸው በጸሎት ሃሳብ መልዕክታቸው ሕይወትን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ መቀበልን፣ ደካሞችን በርኅራኄ መንከባከብን፣ እያንዳንዱን እርምጃ በክብር መጓዝን እና ድምፅ የሌላቸውን በድፍረት መከላከልን ለመማር ያላቸውን ምኞት ገልጸዋል።

“በግድየለሽነት እና በንቀት ባሕል ውስጥ ስንወድቅ፣ በሌሎች ውስጥ ያለውን ፍቅር ማየት ሲሳነን እግዚአብሔር ይቅር ይበለን! ሕይወትን ለመምረጥ ዝግጁ የሆነ አዲስ ልብ ይስጠን! በተጨባጭ ድርጊቶች ሕይወትን የሚንከባከቡ ለጋስ እጆችን ይስጠን” በማለት ጸሎታቸውን አቅርበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያኑ ሕያው የወንጌል ምስክር የምትሆንበት፣ እያንዳንዱ ሕይወት የሚከበርባት፣ ማንም እንደተገለለ የማይሰማባት እና ሰብዓዊነት ሁልጊዜ የሚከበርባት እና የሚጠበቅባት ቤት እንዲያደርጋት” በማለት ጸሎታቸውን አቅርበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በመጨረሻም፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ሕይወትን እንደወደደ ሁሉ እኛም በርኅራኄ፣ በታማኝነት እና ራስን በመስጠት ሕይወትን እንድንወድ ይረዳን ዘንድ በመማጸን፥ “እያንዳንዱ የሰው ልጅ ሕይወት የራሳችን ስጦታ መሆኑን በቃልም ሆነ በድርጊት እንመስክር” በማለት ጸሎታቸውን ደምድመዋል።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዓለም አቀፍ የጸሎት መረብ

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ1844 ዓ. ም. የተመሠረተው የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዓለም አቀፍ የጸሎት አውታረ መረብ ሐዋርያነት ለኢየሱሳውያን ማኅበር በአደራ የተሰጠ ጳጳሳዊ አገልግሎት እንደሆነ ይታወቃል።

ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ይህን አገልግሎት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በታህሳስ ወር 2020 ዓ. ም. የቫቲካን ፋውንዴሽን አድርገው በማቋቋም የመጨረሻ ደንቦቹንም በሐምሌ ወር 2024 ዓ. ም. ማጽደቃቸው ይታወሳል።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ዓለም አቀፍ የጸሎት አውታረ መረብ ባሁኑ ጊዜ በ92 አገሮች ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፥ በየቀኑ ለእግዚአብሔር ተልዕኮ ዝግጁ ሆነው ለመኖር የሚጥሩ ከ22 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ያሉበት መንፈሳዊ ማኅበር እንደሆነ ይታወቃል።

ከተልዕኮቹ መካከል ዋናዎቹ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ወርሃዊ የጸሎት ሃሳቦች ሲሆኑ፥ የሰውን ልጅ ፊት ለፊት የሚገጥሙ አጣዳፊ ችግሮችን በማቃለል፥ በቤተ ክርስቲያኗ ተልዕኮ ላይ እንዲያተኩሩ አባላቱን ይጋብዛል።

 

07 Jul 2026, 14:18