ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት በመካከለኛው ምስራቅ ፍትሃዊ ሰላም እንዲሰፍን አዲስ የድርድር ጥሪ አቅርበዋል
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እሁድ ዕለት በካስቴል ጋንዶልፎ ከተካሄደው የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት በመቀጠል ባስተላለፉት መልእክት በቅድስት ምድር እና በመካከለኛው ምስራቅ የሰላም ጥሪያቸውን አድሰዋል፣ እየጨመረ በመጣው ዓመፅ ላይ ጥልቅ ስጋት እንዳላቸው እና ወዲያውኑ ወደ ውይይት እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበዋል።
በዌስት ባንክ እና በጋዛ ለሚኖሩ ሲቪሎች ስጋት
"በቅድስት ምድር ውስጥ እየተካሄደ ያለውን እና እየተባባሰ የመጣውን ዓመፅ በጥልቅ መከታተሌን እቀጥላለሁ" ሲሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የተናገሩ ሲሆን "በቅርቡ በዌስት ባንክ እና በጋዛ ብዙ ሲቪሎች ሰለባ ሆነዋል" ብለዋል።
"በእያንዳንዱ ሰብዓዊ ሰው ክብር እና እኩል መብቶች ላይ የተመሰረተ ፍትሃዊ የፖለቲካ መፍትሄ ለማግኘት የታለመ ድርድር እንዲጀመር እና ተጨማሪ ወታደራዊ እርምጃዎችን እና የአንድ ወገን ውሳኔዎችን ውድቅ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፣ በተለይም ለእያንዳንዱ እምነት እና ቅዱስ ሥፍራዎች ክብር እና ሁኔታ የሚጥሱ ጉዳዮች እንዲቆሙ እጠይቃለሁ" ብለዋል።
ለዲፕሎማሲ የቀረበ ጥሪ
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በመካከለኛው ምስራቅ ስላለው ሁኔታ ያቀረቡትን ጥሪ አድሰዋል፣ “የወታደራዊ እንቅስቃሴዎች መጠናከር እንደገና ዓመፅንና ውድመትን አምጥቷል፣ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን የሲቪል ዜጎች ሕይወት ወደ ከፍተኛ አደጋ ውስጥ አስገብቷል እንዲሁም የመጠጥ ውሃና የኤሌክትሪክ እጥረትን አባብሷል” ብለዋል።
“በመላው ክልል በጣም የሚፈለገው ሰላም ሳይዘገይ እንዲገኝ ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ጥቃታቸውን እንዲያቆሙ እና የውይይትና የዲፕሎማሲ መንገዶችን በአስቸኳይ እንዲከፍቱ አሳስባለሁ” ሲሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ተናግረዋል።
በዓለም ዙሪያ በጦርነት ለተጎዱ ሕዝቦች የሚቀርቡ ጸሎቶች
ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በጦርነት ምክንያት ለሚሰቃዩ በዓለም ዙሪያ ላሉ ሕዝቦች ሁሉ መጸለያቸውን እንዲቀጥሉ አበረታተዋል።
“እግዚአብሔር ልብን ይንካ እና ኃላፊነት በተሰጣቸው ቦታዎች ላይ ያሉትን ሰዎች አእምሮ ያብራል፣ ስለዚህም እርቅና ሰላም በቅርቡ እንዲሰፍን መጸለያችንን እንቀጥላለን” ብለዋል።
