ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በጦርነት መቅሰፍት መካከል፣ ክርስቶስ ተስፋ ነው ማለታቸው ተገለጸ

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ መልአኩ ገብርኤል ማርያምን ያበሰረበት የመልአከ እግዚአብሔር ጸሎት በሰኔ 28/2018 ዓ.ም በቫቲካን ከተከናወነ በኋላ በእለቱ ቅዱስ ወንጌል ላይ ተንተርሰው የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ ማድረጋቸው የተገለጸ ሲሆን ክርስቶስ ትግላችንን እንዴት እንደሚጋራው እና በዓለም ላይ ላለው ክፉ ነገር መልስ እንደሆነ ተናግረው፣ እንዲሁም የእግዚአብሔር ጥበብ “በሥጋዌ ትሕትና” እንደሚገለጥ አጉልተው ተናግረዋል። የችግሮቻችንን እና የመከራችንን ሸክም ሊያቃልልልን የሚችለው ክርስቶስ ብቻ ነው፣ ነገር ግን ፍቅሩ የሚገኘው በትሕትና ብቻ ነው ሲሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ እሁድ ሰኔ 28/2018 ዓ.ም በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡ ምዕመናን ተናግረዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን  

"ከባርነት ውስጥ፣ ክርስቶስ ነፃ ያወጣናል። በጦርነት መቅሰፍት መካከል፣ ክርስቶስ ተስፋ ነው። በኃጢአት ሰዓት፣ ክርስቶስ ይቅርታ ነው" ሲሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ አፅንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።

"ይህ እውነተኛ ጥበብ እና በስሙ ደቀ መዛሙርት አንድ ሆነን አብረን ለመጓዝ የምንፈልገው መንገድ ነው። ኢየሱስ ይህንን እንደ ወንድማችን በመሆን ያስተምረናል። በመንፈስ ቅዱስ ኃይል፣ ስለ እግዚአብሔር እና ስለ ሰው ልጅ እውነቱን ለቤተክርስቲያን ይገልጣል" ሲሉ ቅዱስነታቸው ተናግረዋል።

ኢየሱስ በክፉ መንፈስ የተጎዳውን የሰው ልጅ ወደ ራሱ ይወስዳል

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ የምንሸከመው የመስቀል ክብደት “ቀላል” እና “ልዝብ” ሊሆን የሚችለው “እግዚአብሔር ራሱ ከእኛ ጋር ስለሚሸከመው፣ ሸክማችንን ለብቻችን ስለማይተው” ብቻ መሆኑን አጉልተው ገልጸዋል።

“እንደ እውነተኛ አስተማሪ፣ ኢየሱስ ለመፈወስና ለመንከባከብ በክፉ ነገር የተጎዳውን የሰው ልጅ ወደ ራሱ ይወስዳል” ሲሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ አጥብቀው ተናግረዋል።

እንዲሁም የመስቀሉን ትርጉም በመረዳት ተስፋና መጽናኛ እንዴት ማግኘት እንደምንችል አብራርተዋል።

ከክርስቶስ የምናገኘው ጥበብ “የመዳን አዋጅ” እና “ቀንበሩ ከእያንዳንዱ ውድቀት ያነሳናል” ሲሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ አስተያየታቸውን የሰጡ ሲሆን ከማቴዎስ 11፡25-30 የተወሰደውን የእለቱን ቅዱስ ወንጌል ቅዱስነታቸው በዋቢነት ጠቅሰዋል።

ክርስቶስ የሚሰጠው ዕረፍት

በዚያ ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “የሰማይና የምድር ጌታ አባት ሆይ፤ ይህን ከጥበበኞችና ከዐዋቂዎች ሰውረህ ለሕፃናት ስለ ገለጥህላቸው አመሰግንሃለሁ፤ አዎን አባት ሆይ፤ ይህ የአንተ በጎ ፈቃድ ሆኗልና።

“ሁሉም ነገር ከአባቴ ተሰጥቶኛል፤ ከአብ ሌላ ወልድን የሚያውቅ የለም፤ ከወልድና ወልድ ራሱ ፈቅዶ ከሚገልጥላቸው ሌላ አብን የሚያውቅ የለም።

“እናንተ ሸክም የከበዳችሁና የደከማችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም ዕረፍት እሰጣችኋለሁ። ቀንበሬን ተሸከሙ፤ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ በልቤ የዋህና ትሑት ነኝና፤ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ፤ ቀንበሬ ልዝብ፣ ሸክሜም ቀላል ነውና” (ማቴ. 11:25-30)።

“በዚህም ምክንያት፣ ክርስቶስን የመከተል ጉዟችን የሚያሰቃይ መናፍቅነት አይደለም። ይልቁንም የታሪክን ድራማ በቁም ነገር የሚመለከት እና በተለይም በጣም ጨለማ በሆኑ ጊዜያት ትርጉሙን ያለማቋረጥ የሚያበራ የነፃነት ትምህርት ቤት ነው” ብለዋል።

ስለዚህ “ክፉ የሚሸነፈው በኢየሱስ መስቀል ብቻ ነው፤ በፍቅሩ ብቻ ነው የሟች ድካም መጽናኛና ቤዛ የሚያገኘው በክርስቶስ መስቀል ብቻ ነው” ሲሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ አፅንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።

የእግዚአብሔር ትምህርት ለሚታገሉ ሁሉ የተነገረ ነው።

ሆኖም፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ትሕትና የክርስቶስን ፍቅር ለመረዳት አስፈላጊ አካል መሆኑንም ጠቅሰዋል። የእለቱ ቅዱስ ወንጌል በመጥቀስ “ኢየሱስ አብን በማመስገን ከእርሱ ጋር እንድንተባበር ይጋብዘናል” ሲሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ የተናገሩ ሲሆን “የእንደዚህ ዓይነት ድንገተኛ እና የደስታ ምልክት ቀላልነት እግዚአብሔር ራሱን ‘ለሕፃናት’ በመግለጥ እንዴት እንደሚደሰት ገልጸዋል።  

“ጥበበኞችና አስተዋዮች’ በራሳቸው ሀሳቦች የተሞሉ በመሆናቸው ሕዝቡን ሊጎበኝ የሚመጣውን የክርስቶስን መገኘት እንዳያውቁት አድርጓቸዋል” ሲሉ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ አመልክተዋል። “ስለዚህ የሰው ጥበብ ትዕቢት ይሆናል፣ ትምህርትም ወደ ኩራት ይሸጋገራል” ሲሉ ከእንደዚህ ዓይነት ተግባራት እንድንቆጠበ ቅዱስነታቸው አሳስበዋል።

“በአንጻሩ የእግዚአብሔር እውነተኛ ጥበብ በሥጋዌ ትሕትና ይገለጣል፣ ትምህርቱም ከሁሉም በላይ ለሚታገሉ ሰዎች የተነገረ ነው፡- ‘እናንተ ደካሞችና ከባድ ሸክም የተሸከማችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ ያለውን የኢየሱስን ቃል በማስታወስ’” ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በዚህ ረገድ ድካም እና መከራ በሚበዛብን ወቅት ወደ እርሱ መሄድ ይኖርብናል ብለዋል።

“ወደ ኢየሱስ መሄድ ማለት እስከ መስቀል ድረስ ለፍቅሩ ምላሽ መስጠት እና በሕይወቱ ውስጥ መካፈል ማለት እንደሆነ” አጉልተው ገልጸዋል።

“የኢየሱስን ‘ቀንበር’ የሚያዋቅረው ይህ በፍቅር የተሰጠ ራስን መስጠት ነው፣ ይህም የትምህርቱ ፍሬ ነገር እና የጥበቡ ልብ የሆነው፣ ለሁሉም ፍቅር የተሞላ ነው” ካሉ በኋላ ቅዱስነታቸው ለእለቱ ያሰናድቱን የቅዱስ ወንጌል አስተንትኖ አጠናቀዋል።  

05 Jul 2026, 12:50