ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በምሳ ግብዣ ላይ ለችግረኞች ሰላምታቸውን ባቀረቡበት ወቅት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በምሳ ግብዣ ላይ ለችግረኞች ሰላምታቸውን ባቀረቡበት ወቅት   (@VATICAN MEDIA)

አቅመ ደካማነት እና ተጋላጭነት ለማኅበረሰቦች የጥንካሬ ምንጭ ሆነው ሊቀርቡ እንደሚችሉ ተነገረ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በካስቴል ጋንዶልፎ ከ200 አቅመ ደካማ እና ተጋላጭ ከሆኑ ሰዎች ጋር የምሳ ማዕድ እንደሚጋሩ ተነግሯል። ከግብዣው ቀደም ብሎ የ “ውዳሴ ላንተ ይሁን!” የከፍተኛ ትምህርት ማዕከል የመገናኛ ክፍል አስተባባሪ ዶናቴላ ፓሪሲ ከቫቲካን የዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፥ “ይህም ቤተ ክርስቲያን ለሁሉም ክፍት በመሆን በተለይም ለተቸገሩ አስተማማኝ መጠጊያ መሆኗን ለማስታወስ የሚደረግ ነው” በማለት አስረድተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

አዘጋጆቹ ተስፋ፣ መልካም አቀባበል እና አካታችነት በተሰኙ እሴቶች በመነሳሳት ያስተባበሩት፥ “ከርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ጋር የምሳ ግብዣ” የተሰኘው መርሃ ግብሩ ቅዳሜ ሐምሌ 4/2018 ዓ. ም. በካስቴል ጋንዶልፎ ጳጳሳዊ የአትክልት ሥፍራ ውስጥ እንደሚካሄድ ታውቋል።

ተጋላጭ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥ የሚገኙት እና በሮም ሀገረ ስብከት እና ተባባሪ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች የሚታገዙት 35 ሕጻናትን ጨምሮ ሁለት መቶ ሰዎች በውበት እና በመንፈሳዊነት በተሞላ የአትክልት ሥፍራ ቀኑን ሙሉ እንደሚያሳልፉ ታውቋል።

“የተጠበቀ ሥፍራ በመሆኑ ለ400 ዓመታት ለዓለም ተዘግቶ ቢቆይም በቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ የተከፈተ እና ዛሬ በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በስፋት ተከፍቶ የክብር እንግዶችን በደስታ እየተቀበለ ይገኛል” ሲሉ የ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” የከፍተኛ ትምህርት ማዕከል የመገናኛ ክፍል አስተባባሪ ዶናቴላ ፓሪሲ ተናግረዋል።

የዕለቱ መርሃ ግብር የሚጀምረው  የ“ውዳሴ ላንተ ይሁን” የከፍተኛ ትምህርት ማዕከል ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ብጹዕ ካርዲናል ፋቢዮ ባጆ እና በቅድስት መንበር የበጎ አድራጎት አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሉዊስ ማሪን ደ ሳን ማርቲን በሚያቀርቡት የመስዋዕተ ቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ሲሆን፥ ቀጥሎም እንግዶቹ በ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” መንደር ሠራተኞች በመመራት ሥፍራውን እንደሚጎበኙት ታውቋል።

ቤተ ክርስቲያን ለሁሉም ክፍት የሆነች ናት

የ “‘ውዳሴ ላንተ ይሁን’ መንደር የሮምን ረጅም ታሪክ፣ የንጉሠ ነገሥት ዶሚቲያን ቪላ ቅሪቶች እና ከ17ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ለዕረፍት የሚመጡበት ሥፍራ ነው” ሲሉ ዶናቴላ ፓሪሲ ገልጸው፥ ቀጥለውም፥ ከ300 በላይ ልዩ ልዩ ዝርያዎች የተገኙ ከ4,000 በላይ ተክሎች ያሉበት ውብ የተፈጥሮ ፓርክ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

“የውበት እና የወዳጅነት ሃብት የሆነው ይህ ሥፍራ ዛሬ ቤተ ክርስቲያን ያለ ልዩነት በሮቿን ለሁሉም በተለይም ከማኅበረሰቡ ተለይተው ለሚኖሩት ክፍት ማድረጓን የሚገልጽ እና ‘ቤተ ክርስቲያን ዘወትር ለሁሉም ሰው ክፍት መሆን አለባት’ የሚለውን መልዕክት የሚያስተላልፍ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

“ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ይህንን መልዕክት በተደጋጋሚ አስተላልፈዋል” ያሉት ዶናቴላ ፓሪሲ፥የዛሬው ዝግጅት ቅዱስነታቸው የዓለምን ትኩረት ለመሳብ በሜዲትራኒያን መሃል ላይ በምትገኘው ትንሽ ደሴት ላምፔዱሳ ያደረጉት ሐዋርያዊ ጉብኝት ብዙውን ጊዜ ጦርነትን፣ ድህነትን እና ማኅበራዊ ኢ-ፍትሃዊነትን በማምለጥ የተሻለ ሕይወት ፍለጋ ሳይወዱ ስደት በመምረጥ በባሕር ላይ የሚሞቱ በሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ምስክር ሆኗል” ሲሉ አስረድተዋል።

“በመሆኑም ዛሬ በዚህ ዝግጅት አማካይነት ቤተ ክርስቲያን ለሁሉም ሰው ክፍት እንደሆነች እና ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ቤተሰቦች፣ ማኅበረሰቦች እና ሰዎች አስተማማኝ ሥፍራ መሆኗን እናረጋግጣለን” ሲሉ አስረድተዋል።

የተቸገሩ ሰዎች አመለካከታችንን ይለውጣሉ

“ይህ ተነሳሽነት በየዓመቱ ከሌሎች ሀገረ ስብከቶች የሚመጡ ሰዎችን መቀበል እንደሚችል ተስፋ እናደርጋለን” ያሉት አዘጋጆቹ፥ ባለፈው ዓመት ተሳታፊዎቹ የካስቴል ጋንዶልፎ ከተማ ከሚገኝበት ከአልባኖ ሀገረ ስብከት እና ዘንድሮ ከሮም ሀገረ ስብከት የሚመጡትን እንግዶች እንደሚያስተናግድ  ገልጸዋል።

“ከተሳታፊዎቹ መካከል ስደተኞች፣ ልጆች ያላቸው ባል አልባ እናቶች፣ በ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” መንደር የሥልጠና ኮርሶችን ጨርሰው ወደ ማኅበረሰብ እና ወደ ሥራ ገበታ የሚመለሱ ሰዎች፣ የአካል ጉዳተኞች፣ ችግር እንዳለባቸው የሚታሰቡ የኅብረተሰብ እና የቤተ ክርስቲያን ክፍሎች አሉ” ሲሉ ዶናቴላ ፓሪሲ ገልጸዋል።

“እንደ እውነቱ ከሆነ እዚህ በ ‘ውዳሴ ላንተ ይሁን’ መንደር በየቀኑ የምናገኘው ሰዎች ለማኅበረሰቡ ማበርከት የሚችሉ፥ መንደሩንም ማበለጸግ የሚችሉ እና የእነርሱ መገኘት ቤተ ክርስቲያን እና መላው ኅብረተሰብ አዲስ የጥንካሬ ምንጭ እንዲሆን የሚያደርግ ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

የምሳ ግብዣው በሮም ከተማ “ላ ኢሶላ ዴላ ፒሳ” ከተሰኘ ምግብ ቤት ልግስና የተዘጋጀው ሲሆን፥ የጠዋት ቁርስ ደግሞ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” ፕሮጄክትን በቅርበት ከተሳተፈ “ባር ዱኦሞ በአልባኖ” መዘጋጀቱ ታውቋል። ይህም “ለእንደዚህ ዓይነት ተነሳሽነት ልግስና እና ድጋፍ የሚሰጥ ውብ ምስክርነት ነው” ያሉት ዶናቴላ ፓሪሲ፥ የምግብ ምርጫው ከተለያዩ የሃገሪቱ ባሕላዊ ዳራዎች የሚመጡ እንግዶችን ያገናዘበ እንደሆነ አስረድተዋል።

በፍጥረታት መካከል ያሉ ፍጥረታት

“የምሳ ግብዣ ተነሳሽነቱ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለካስቴል ጋንዶልፎ ከተማ እና ለ ‘ውዳሴ ላንተ ይሁን’ መንደር ያላቸውን ጥልቅ አድናቆት ያንፀባርቃል” ያሉት ዶናቴላ ፓሪሲ፥ ቅዱስነታቸው ሥፍራውን እንደሚወዱት እና ፕሮጄክቱንም በቅርበት እንደሚከታተሉ ገልጸው፥ በሰኔ ወር ውስጥ በቫቲካን ለመጀመሪያው ጊዜ የተካሄደውን የ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” መንደር ስብሰባ መሳተፋቸውን አስታውሰዋል።

ስብሰባው ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ንግዶች እና ኢንዱስትሪዎች የተውጣጡ ተወካዮችን ያሳተፈ ሲሆን፥ የምርት ሂደቶች እና የሥራ ቦታዎች የበለጠ ዘላቂ ሊሆኑ እንደሚችሉ፣ ሰዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ የበለጠ ኃላፊነት እንዲሰማቸው የሚያስችል እንደሆነ ታውቋል።

“ተነሳሽነቱ ቀድሞውኑ በነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ ሐዋርያዊ መልዕክት ውስጥ እና ‘በማግኒፊካ ሂውማኒታስ’ በተሰኘ የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሐዋርያዊ መልዕክት ውስጥ የሚገኝ፥ እራሳችንን “በፍጥረታት መካከል የምንገኝ ፍጥረታት” ብለን እንድንገነዘብ የሚያደርግ ነው ሲሉ” የ “ውዳሴ ላንተ ይሁን!” የከፍተኛ ትምህርት ማዕከል የመገናኛ ክፍል አስተባባሪ ዶናቴላ ፓሪሲ ለቫቲካን የዜና አገልግሎት አስረድተዋል

 

11 Jul 2026, 12:46