ፈልግ

ዛሬ የማድሪድ ቤተ ክርስቲያን በርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሐዋርያዊ ጉብኝት የማይረሳ ታሪክ አስመዝግባለች ተባለ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በስፔይን ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ከአገሪቱ የፓርላማ አባላት እና ከጥቃት ሰለባዎች ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል። እንዲሁም በአልሙዴና ካቴድራል ውስጥ ጸሎት በማድረስ ወደ 80,000 ከሚጠጉ ምዕመናን ጋር ማምሻውን አሳልፈዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሰኞ ሰኔ 1/2018 ዓ. ም. በማድሪድ ባሳለፉት ሙሉ ቀን በስፔን ፓርላማ ታሪካዊ ጉብኝት በማድረግ ዛሬ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚነሱ አንዳንድ ጉዳዮች፥ ሰባዓዊ ክብርን፣ ስደትን፣ የሕይወት ጥበቃን፣ የጦር መሣሪያ ትጥቅ ማደራጀትን፣ የቤተሰብ ሕይወትን፣ ሰው ሠራሽ አስተውሎትን እና ሰላምን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ፍትሃዊ ማኅበረሰብ የሚመሠረተው ለእያንዳንዱ ሰው የማይደፈር ክብር እውቅናን በመስጠት ነው” ብለው፥ በዚህ መልኩ የአገራትን ኅሊና እና የዓለምን ሥነ-ምግባራዊ መሠረት የሚፈታተን አሳዛኝ የስደት ቀውስን አስታውሰዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለስፔይን ፓርላማ አባላት ንግግር ሲያደርጉ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለስፔይን ፓርላማ አባላት ንግግር ሲያደርጉ   (@Vatican Media)

“የስደተኞች እና የጥገኝነት ጠያቂዎች ሁኔታ በሰዎች ላይ የሚያተኩር፥ ለስደት ዋና ምክንያቶች የሆኑ ችግሮችን የሚፈታ እና ስደትን ከመቆጣጠር በላይ የሆነ ምላሽን ይጠይቃል” ሲሉ አፅንዖት ሰጥተዋል።

ቀጥለውም እያንዳንዱ ጦርነት በመደራደር ችሎታ ላይ የሚደርስ ከባድ ሽንፈት መሆኑንም ገልጸው፥ “የጦር መሣሪያዎች ጊዜያዊ ጸጥታ ሊያስገኙ ቢችሉም ነገር ግን እውነተኛ እና ዘላቂ ሰላም መገንባት አይችሉም” በማለት ባስገነዘቡ ጊዜ ከሰባት ደቂቃ በላይ ተጨብጭቦላቸዋል።

እንደ ቤተ ክርስቲያን በሰላም መኖር

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከስፔይን ፓርላማ ቆይታ በኋላ ከአገሪቱ ብጹዓን ጳጳሳት ጋር ተገናኝተው  ግልጽ እና ቀጥተኛ ተመሳሳይ መልዕክታቸውን አስተላልፈው፥ ብጹዓን ጳጳሳቱን አንድነትን እንዲጠብቁ፣ የእርስ በርስ ውይይት እንዲያሳድጉ፣ ከመለያየት ይልቅ በአንድነት ሆነው በአደራ የተሰጣቸውን ምዕመናን እንዲመሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በስፔይን ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ጽሕፈት ቤት ተገኝተው
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በስፔይን ብጹዓን ጳጳሳት ጉባኤ ጽሕፈት ቤት ተገኝተው   (@Vatican Media)

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በሥፍራው ለነበሩ ሰዎች ባደረጉት ንግግር፥ “የቤተ ክርስቲያኒቱ ጥንካሬ የሚለካው በሃብቷ ብዛት ሳይሆን በልጆቿ ቅድስና፣ በሐዋርያዊ እረኞቿ ኅብረት እና በመንፈስ ቅዱስ ለመመራት ፈቃደኛ በሆኑ ሰዎች ትሑትና ጽኑ ታማኝነት ነው” ሲሉ አስገንዝበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከክርስትና እምነቶች እና ሌሎች ሃይማኖቶች ጋር፣ ከማያምን ማኅበረሰብ፣ ከሲቪል ባለስልጣናት እና ለጋራ ጥቅም በበጎ ፈቃድ ለሚሠሩ ሰዎች የበለጠ በነፃነት ለመናገር ውስጣዊ ሰላም እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አብራርተዋል።

የቅዱስነታቸው የግል ስብሰባ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በስፔይን ውስጥ በካኅናት በደል ከደረሰባቸው ሰዎች ጋር አንድ ሰዓት የቆየ የግል ውይይት ማካሄዳቸውን የቅድስት መንበር መግለጫ ክፍል ዳይሬክተር ማቴዮ ብሩኒ የገለጹ ሲሆን፥ ተጎጂዎቹም በበኩላቸው፥ ቤተ ክርስቲያኒቱ ለእንዲህ ዓይነት አሳዛኝ ጉዳይ የምትሰጠውን ምላሽ የበለጠ ውጤታማ የሚያደርጉ ሃሳቦችን ሲያቀርቡ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የጥቃቱ ሰለባዎች ስቃይ በጥልቀት የተሰማቸው መሆኑን የመግለጫ ክፍሉ ዳይሬክተር ማቴዮ ብሩኒ አስረድተዋል።

ግድግዳዎችን አፍርሶ እንደገና መገንባት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከስፔይን ብጹዓን ጳጳሳት ጋር የማድሪድ ሀገረ ስብከት ጠባቂ የአልሙዴና እመቤታችን ቅድስት ማርያም ካቴድራል ውስጥ በጸሎት የተወሰነ ጊዜ ካሳለፉ በኋላ በፈረሰው ግድግዳ እና በእመቤታችን ቅድስት ማርያም ሐውልት በማሰላሰል ባደረጉት ንግግር፥ “አዲስ፣ የሚያምር እና ዘላቂ የሚሆን ሥራ ለመሥራት ግንቦችን ለማፍረስ ፈቃደኞች መሆን አለብን” ሲል አስረድተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በአልሙዴና እመቤታችን ቅድስት ማርያም ካቴድራል ውስጥ ጸሎት ሲደርሱ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በአልሙዴና እመቤታችን ቅድስት ማርያም ካቴድራል ውስጥ ጸሎት ሲደርሱ   (@Vatican Media)

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ሁሉም ሰው የእምነት ምሥክርነቱን እንዲሰጥ በማሳሰብ፥ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እገዛን እንዲለምን አደራ ብለዋል።

የተከፈተ መጽሐፍ ቅዱስ መሆን

“ለእግር ኳስ ተጫዋች በዚህ ስታዲየም ውስጥ ጎል ማስቆጠር በሕይወታቸው ላይ የማይረሳ ምልክት የሚተው እንደሆነ እገምታለሁ” ብለው፥ ነገር ግን ዛሬ በማድሪድ የምትገኝ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የማይረሳ ታሪክ አስመዝግባለች” ሲሉ ተናግረዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ትኩረታቸውን ከዓለማዊ ድል ጥልቀት ወዳለው መንፈሳዊ ድል በማዞር፥ ከማድሪድ ሀገረ ስብከት የመጡ ወደ 80,000 የሚሆኑ ምዕመናን ውብ ቤተሰባዊነት በመገንባታቸው አድናቆታቸውን ገልጸውላቸዋል።

ቅዱስነታቸው በንግግራቸው የዜማ እና የሙዚቃ ውበት አስፈላጊነት በመገንዘብ፥ ሁሉም ሰው የደግነት መንፈሳዊ ጥበብን እንዲማር አሳስበው፥ “ያለዚህም የወንጌል ምስክርነት መደጋገም ከመሆኑ በላይ ውጤታማነቱን ሊያጣ ይችላል” ሲሉ አስገንዝበዋል።

ቅዱስነታቸው ወደ ስታዲየሙ ሲደርሱ የተደረገላቸው አቀባበል
ቅዱስነታቸው ወደ ስታዲየሙ ሲደርሱ የተደረገላቸው አቀባበል   (@Vatican Media)

“የማድሪድ ሀገረ ስብከት እንደ ቤተ ክርስቲያን በአንድነት፥ በልዩ ልዩ አስደንጋጭ ምስሎች እና ቃላት ለተጎዳው፣ ፍትህን ለተራበው እና እውነትን ለተጠማው የሰው ልጅ ኃይል የሚሆን የወንጌል ምስክርነት ሊሰጥ የሚችል በመሆኑ ምዕመናን መፍራት የለባቸውም” ሲሉ አሳስበዋል።

“መንፈሳዊ ዝማሬ ወደ ሰዎች ልብ ውስጥ ሲደርስ መልካም አቀባበል እንዲሰማቸው ያደርጋል” ብለው፥ ፍቅር ቤተኛነት እንዲሰማ የሚያደርግ ቋንቋ በመሆኑ ሁሉም ሰው ለሌላው የተገለጠ መጽሐፍ ቅዱስ መሆን እንደሚገባ በማሳሰብ መል ዕክታቸውን ደምድመዋል።

 

 

 

 

09 Jun 2026, 16:48