ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ በበጋ ዝግጅት ላይ የተሳተፉ ልጆችን ሲጎበኙ ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ በበጋ ዝግጅት ላይ የተሳተፉ ልጆችን ሲጎበኙ   (@Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ “ቴክኖሎጂ ጓደኝነትን የሚያገለግል እንጂ የሚተካ መሆን የለበትም” ሲሊ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በበጋ ዝግጅት ላይ የተሳተፉ የቫቲካን ሠራተኞች ልጆችን ጎብኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል። ቅዱስነታቸው በመልዕክታቸው ልጆች ቴክኖሎጂን በኃላፊነት እንዲጠቀሙ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የቫቲካንን የበጋ ወቅት ካምፕ ሰኞ ሰኔ 15/2018 ዓ. ም. ጎብኝተው በዚህ ዓመት ፕሮግራም ላይ ከሚሳተፉ ልጆችና ወጣቶች ጋር ተገናኝተው በርካታ ጥያቄዎችን መልሰዋል።

ሰብዓዊ ግንኙነቶች ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል

ቅዱስነታቸው በትምህርት ዘመን ከተንቀሳቃሽ ስልኮች ጋር ያለውን ግንኙነት የማቆም ፈተናን አስመልክቶ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፥ የቴክኖሎጂን ጥቅሞች ቢቀበሉም እውነተኛ የሰው ልጅ መስተጋብርን መተካት እንደሌለበት አፅንዖት ሰጥተዋል።

“ቴክኖሎጂ እጅግ ጥሩ እና ለብዙ ነገሮች ጠቃሚ ሊሆን ይችላል” ብለው፥ ሆኖም ግን አብረው በሚሆኑበት እያንዳንዱ ጊዜ ሞባይል ስልክን፣ ስማርት ስልክን ወይም ታብሌትን መያዝ አስፈላጊ አይደለም” ብለዋል።

ልጆች ግንኙነታቸው ከመሣሪያዎች ጋር ከመሆን ይልቅ እንደ ሰው ከጓደኞቻቸው ጋር አብረው ጊዜን እንዲያሳልፉ አደራ ብለዋል።

“ጓደኝነትን በመገንባት አብሮ ጊዜ ማሳለፍ፣ አብሮ መጫወት እና ምናልባትም አብሮ ማጥናት በጣም አስፈላጊ ነው” ብለው፥ እኛ ሰዎች በመሆናችን ከሌሎች ሰዎች ጋር መገናኘት እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው” ብለዋል።

“ቤተሰብ አንድ ላይ በሚሆንበት ጊዜ ሁሉም ሰው በየራሱ ስልክ ላይ ከመሆን ይልቅ የቤተሰብ ሕይወትን በማስፋት እንዴት መነጋገር፣ ማውራት እና እርስ በርስ መደሰት እንደሚቻል መማር በጣም አስፈላጊ ነው” ብለዋል።

ቅዱስነታቸው የጸሎትን አስፈላጊነት ሲያስረዱ፥ “ልጆች መጽሐፍ ቅዱስን እና ጸሎቶችን ከስልኮቻቸው ማግኘት ቢችሉም ነገር ግን እግዚአብሔር ስልኮቻቸውን ከማየት ይልቅ ልባቸውን እና ሕይወታቸውን መመልከት ይፈልጋል” ሲሉ አስረድተዋል።

የዲጂታል መሣሪያዎች ጥገኝነት መኖራቸውንም ማወቅ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በተለይ ለትልልቅ ልጆች ሲናገሩ፥ ተጠቃሚዎች በርካታ መተግበሪያዎች ለረጅም ጊዜ እንዲመለከቷቸው ለማድረግ ሆን ተብሎ የተነደፉ መሆናቸውን በማስጠንቀቅ፥ የመተግበሪያው ባለቤቶች በቴክኖሎጂ ላይ ጥገኞች እንድንሆን ለማድረግ እንደሚሞክሩ አስረድተዋል።

በተንቀሳቃሽ ስልክ አጠቃቀም ላይ ተግባራዊ ገደቦችን ማስቀመጥ፣ ስልኮችን በቀን ውስጥ ለተወሰኑ ጊዜያት ማስቀመጥ እና ለውይይት እና ለቤተሰብ ግንኙነቶች ዕድል ማዘጋጀት የመሳሰሉ ተግባራዊ ገደቦችን ማስቀመጥ እንደሚገባ ሃሳባቸውን አቅርበዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ቀጥለውም ልጆች ግንኙነቶችን በማዳበር፣ እግዚአብሔርን በጸሎት በመፈለግ እና ነፃነታቸውን ሊገድቡ የሚችሉ ጥገኝነቶችን በማስወገድ ሰብዓዊ እና መንፈሳዊ ሕይወታቸውን እንዲያዳብሩ አበረታተዋቸዋል።

በግል ማሰብን መማር

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ሐዋርያዊ ጉብኝት ለማድረግ የሚያደርጓቸውን ጉዞዎች መሠረት በማድረግ፥ የጂፒኤስ አሰሳ ሥርዓቶች ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ ሲመሩ የተመለከቷቸውን በርካታ አጋጣሚዎች አስታውሰው፥ በጣሊያን፣ በሌሎች የአውሮፓ አገሮች፣ በፔሩ እና በዩናይትድ ስቴትስ ጂፒኤስ ወደ ተሳሳተ መንገድ እንደወሰዳቸው ተናግረዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ “በራስ ማሰብን መማር እና በሕይወታችን ውስጥ ወዴት እንደምንሄድ የማወቅ ወሳኝ ችሎታን ማዳበር የተሻለ ነው” ሲሉ አስረድተው፥ ልጆች ሙሉ በሙሉ በቴክኖሎጂ ላይ ከመመካት ይልቅ እግዚአብሔር የሰጣቸውን ችሎታዎች በሚገባ በሙላት እንዲጠቀሙ አበረታቷቸዋል።

“አእምሮዬ የሚሠራ ከሆነ ስልክ አያስፈልገኝም” ብለው፥ ዝግጅት እና ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ ሰዎች ችግሮችን እንዲያልፉ እና ያልተጠበቁ ችግሮች ሲከሰቱ መፍትሄን ለማግኘት እንደሚረዳቸው አክለዋል።

ከቅዱስነታቸው ጋር የተደረገ ጸሎት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በውይይቱ መጨረሻ፥ “የበጋ ጊዜ ዝግጅት ዋና አሳሽ” ተብለው በመሰየም ለአሰሳ የሚያግዙ መሣሪያዎች እና የመታሰቢያ ሰሌዳም የቀረበላቸው ሲሆን፥ ልጆቹ አብሮአቸው እንዲጸልዩ ጋብዘው፥ ይህንንም ለወላጆቻቸው እንዲነግሩ በማበረታታት፥ “ኢየሱስ አብሮን እንዲሆን ስለምንፈልግ ጸሎት ለእኛ በጣም አስፈላጊ ነው” ሲሉ መልዕክታቸውን ደምድመዋል።

 

23 Jun 2026, 16:29