ፈልግ

ር.ሊ.ጳ ሊዮ የቅዱስ ቁርባን ጸጋ እንዴት እንደሚለውጥ እና የተስፋ ዋና ገፀ-ባህሪያት እንደሚያደርገን

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከግንቦት 29 እስከ ሰኔ 5/2018 ዓ.ም አራተኛውን ሐዋርያዊ ጉብኝት በስፔን እያደረጉ መሆናቸው ይታወቃል። በማድሪድ ከተማ ልብ ውስጥ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከ1.2 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የተሳተፉበትን የጎርጎሮሳዊያኑን የቀን አቆጣጠር በሚከተሉ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ምዕመናን ዘንድ በግንቦት 30/2018 ዓ.ም የክርስቶስ ቅዱስ ሥጋው እና ክቡር ደም የሚታወስበት አመታዊ በዓል ተክብሮ ማለፉ የሚታወስ ሲሆን በወቅቱ ቅዱስነታቸው ባሳረጉት መስዋዕተ ቅዳሴ ላይ ባሰሙት ስብከት፣ ስፔናውያንን "ይህችን ሀገር ለዘመናት የቀረፀው እና የገለጸው ሃይማኖታዊነት ሊጎበኝ የሚገባው የቀድሞ ሙዚየም ሳይሆን ዛሬም ቢሆን የምንጎበኘው የእምነት ትምህርት ቤት መሆኑን እንዲያረጋግጡ" አበረታተዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ መብራቱ ኃ/ጊዮርጊስ-ቫቲካን

በስፔን በምያደርጉት ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው ሁለተኛ ቀን መጀመሪያ ላይ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የክርስቶስን ቅዱስ ሥጋ እና ክቡር ደም ክብረ በዓል በመስዋዕተ ቅዳሴ መርተዋል። በማድሪድ እና በዙሪያው ባሉት መንገዶች ከ1.2 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ፕላዛ ደ ሲቤሌስ በተሰኘው ሥፍራ ተጨናንቀው የተገኙ ሲሆን፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ከእነሱ ጋር በመሆናቸው ደስታቸውን ገልጸዋል፣ "በመካከላችን የክርስቶስ ሕያው መገኘት ስጦታ የሆነውን በቅዱስ ቁርባን ዙሪያ ተሰብስበው መገኘታቸው እንዳስደሰታቸው" ቅዱስነታቸው ተናግረዋል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በዚህ ቀን ጌታ ሕይወቱን በፈቃደኝነት እንዴት እንዳቀረበልን "ከአብ ጋር ኅብረት እንድንፈጥርና ልጆቹ እንድንሆን" እና "ከሞት ይልቅ በሚጠነክር ፍቅር ከእግዚአብሔር ሕይወት ጋር ሊመግባን ከሰማይ እንደወረደ እዚህ እንዳለ" በልዩ መንገድ እናስታውሳለን ብለዋል።

የክርስቶስ ቅዱስ ሥጋ እና ክቡር ደም ወጎች ሕያው እምነት

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ስፔን የጌታን መገኘት በቅዱስ ቁርባን እንጀራ ውስጥ ስላከበረችው የበለፀገ ታሪክ ክብር ሰጥተዋል፤ በማድሪድ እና በብዙ የስፔን ክፍሎች የክርስቶስ ቅዱስ ሥጋ እና ክቡር ደም በዓል "ወደ እምነት ልብ" ለመመለስ "ለእግዚአብሔር ያለንን ፍቅር እና ታማኝነት ለማደስ" በልዩ መንገድ ይከበራል ብለዋል።

በታላላቅ መንፈሳዊ ሁደቶች በተለያዩ ዘመናት ውስጥ እነዚህ ወጎች የስፔን ሕዝብ ልዩ እና የአምልኮ፣ የኪነጥበብ፣ የሙዚቃ፣ የሕንፃ እና የህይወት መግለጫዎችን እንዴት እንደሰጡ አስተውለዋል። እነዚህም የሚወክሉት ከባህላዊና ከሥነ ጥበብ በላይ ብቻ ሳይሆን "በእኛ መካከል ሕያው ሆኖ የሚመላለሰውን ከሙታን የተነሣውን ጌታ ፊት የእምነት መግለጫ፣ እሱም ሕያው የሆነውና በመካከላችን መሄዱን የሚቀጥል፣ የሕይወትን ረሃብ ለማርካት እንጀራ የሚሆነውን፣ የልባችንንና የታሪካችንን ጓዳዎች፣ በጨለማ የተሸፈኑትን እንኳን የሚጎበኝ ነው" አምላክ ነው ብለዋል።

የሚመግበንና የሚከተለን

የቅዱስ ቁርባን ሁደቶች ኢየሱስ ክርስቶስ እንዴት እንደሚንከባከበን ያስታውሳሉ፣ ነገር ግን እንዴት "ሊገናኘን እንደሚወጣ" እና በዕለት ተዕለት ሕይወታችንና እንቅስቃሴዎቻችን ውስጥ እንደሚከተለንም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ገልጸዋል።

"እሱ ከሕዝቡ ጋር የሚሄድ፣ የታሪክ ጌታ የሆነ፣ ለእኛ ቅርብ የሆነ አምላክ ነው። ለደካሞች መጽናኛ፣ ለቤተሰቦች ብርሃን፣ ለታመሙ ተስፋ እና ለሚሰቃዩ ሰዎች ሰላም ነው። በትህትና ጎዳናዎች ላይ የሚሄደው ክርስቶስ ከድሆች፣ ከተበደሉ፣ ብቻቸውን ከሆኑ እና ከተተውት ጋር የሚገናኝ ነው" ብለዋል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የክርስቶስ ቅዱስ ሥጋ እና ክቡር ደሙ "ከራስ ወዳድነትና ከግዴለሽነት፣ ከምቾት፣ ከግል እምነት እንድንወጣ፣ ለለውጥ ላቀረበልን ግብዣ ምላሽ እንድንሰጥ፣ አመለካከታችንን እንድንቀይር፣ እና የሚቀይረንን እና የአዲስ ዓለም ገንቢዎች የሚያደርገንን የእርሱን መገኘት እንድንቀበል" እንዴት እንደሚጠይቀን አብራርተዋል።

እናም ዛሬ በልዩ መንፈሳዊ ሁደቶች የክርስቶስን ቅዱስ ሥጋ እና ክቡር ደም በዓል "በዕለት ተዕለት ሕይወታችን፣ በግንኙነቶቻችን፣ በኅብረተሰቡ እና የወደፊቱን እንድንገነባ፣ እግዚአብሔር እንዴት እንደሚወደን፣ እንደሚንከባከበን፣ እንደሚከተለን እና እንደሚያድነን" በእለቱ ምንባባት እንደ ሰማነው "ማስታወስ ይኖርብናል" የሚል ወቅታዊ ግብዣ ነው ብለዋል።

ሃይማኖታዊነትን መኖር

ከዚያም ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ "የዛሬው እና የወደፊቱ የስፔን ተግባር" "ይህችን አገር ለዘመናት የቀረፀው እና የገለጸው ሃይማኖታዊነት የሚጎበኝ ያለፈው ዘመን ሙዚየም ሳይሆን ዛሬም ቢሆን የምንጎበኘው የእምነት ትምህርት ቤት መሆኑን ማረጋገጥ" አለብን ብለዋል።

ይህ ትምህርት ቤት "በእግዚአብሔር እና በባልንጀራችን ፊት እንድንበረከክ" ጥሪ ያቀርብልናል፤ ስለዚህም "ስጦታ የሚሆን የፍቅር ነፃነት... በመካከላችን እንዲፈስ እና የራስ ወዳድነት ሰንሰለቶችን እንዲሰበር ማድረግ ያስፈላጋል ያሉ ሲሆን ልክ እግዚአብሔር "እውነተኛ መገኘት" እንደሆነ ሁሉ እኛም "በኅብረተሰቡ እውነታዎች እና ተግዳሮቶች ውስጥ እንድንገኝ ተጠርተናል... በግል ለጋራ ጥቅም ግንባታ እራሳችንን አሳልፈን እንድንሰጥ ተጋብዘናል" ብለዋል።

ከቅዱስ ቁርባን ምንጭ በመነሳት

በማጠቃለያው፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ሁሉም ሰው ወደ ጌታ "በቅን ፍቅር" እንዲመለስ፣ ከእርሱ ጋር ለመገናኘት ክፍት እንዲሆኑ እና "የልባችንን ጥማት እንዲያረካ እንድንፈቅድለት፣ ከዚያም ወደ ሕይወት እና ታሪክ ጎዳናዎች እንድንወጣ፣ ይህንን የንፁህ ውሃ ጅረት፣ የፍቅር፣ የሰላም፣ የፍትህ እና የደስታ ጅረት ለሰዎች እንድናመጣ" መጸለይ ይኖርብናል ብለዋል።

ሁላችንም "ከዚህ የቅዱስ ቁርባን ምንጭ እንደገና እንድንጠጣ" የጸለዩት ቅዱስነታቸው ይህም ወንድሞቻችንን፣ እህቶቻችንን፣ ቤተሰቦቻችንን፣ ድሆችን፣ መከራ የደረሰባቸውን እና ተስፋ የቆረጡትን ለማደስ" ጠቃሚ ነው ብለዋል።

“የቅዱስ ቁርባን ጸጋ ይለውጠናል እና የታሪክ ለውጥ ዋና ገፀ-ባህሪያት ያደርገናል፣ ለምናገኛቸው ሰዎች የተስፋ ምልክት ነው። በቅዱስ ቁርባን ውስጥ የሚገኘው ጌታ ኢየሱስ፣ የተቆረሰ፣ የተሰጠ እና የሚቀርብ እንጀራ ይለውጣችሁ፣ ይህም ለእናንተ፣ ለቤተሰባችሁ እና ለአገራችሁ የሙላት ሕይወት እንዲበቅልላችሁ ያደርጋል" ሲሉ ቅዱስነታቸው ተመኝተዋል።

በዓሉ የተጠናቀቀው በርዕሰ ሊቃነ ጳጳስ ሊዮ የሚመራው የቅዱስ ቁርባን ሥነ ሥርዓት በመንፈሳዊ ሁደት እና ቡራኬ ከተጠናቀቀ በኋላ ሲሆን ከ30,000 በላይ አበቦችን ባጌጡ አስራ ስድስት የተለያዩ የአበባ ማስቀመጫዎች መካከል መንፈሳዊ ሁደት ከተደረገ በኋላ እንደ ነበረ ተገልጿል።

 

08 Jun 2026, 10:58