ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ለቅድስት መንበር መገናኛዎች ጽ/ቤት አዲስ ተጠሪ መሰየማቸው ተገለጸ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ በአሁኑ ወቅት የ“Eternal Word Television Network” (EWTN) ፕሬዝዳንት እና ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑትን ማርያ ሞንሴራት አልቫራዶን ከጥቅምት 22/2019 ዓ. ም. ጀምሮ ለቅድስት መንበር መገናኛ ጽሕፈት ቤት ተጠሪ አድርገው ሾመዋል።
በሜክሲኮ ሲቲ የተወለዱት አልቫራዶ ከፍሎሪዳ ኢንተርናሽናል ዩኒቨርሲቲ እና ከጆርጅ ዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚ ዲግሪዎችን አግኝተዋል። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ2009 እስከ 2023 ድረስ በ “Becket Fund for Religious Liberty” በተሰኘ ድርጅት ውስጥ የአመራር ቦታዎችን በመያዝ የሃይማኖት ነፃነትን ለመከላከል እና ሰብዓዊ ክብርን ለማስጠበቅ በተደረጉ ተነሳሽነቶች ውስጥ አገልግለዋል።
እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ2023 ጀምሮ በ “Eternal Word Television Network” (EWTN) የመገናኛ ተቋም ውስጥ በቴሌቪዥን፣ በሬዲዮ፣ በህትመት፣ በዲጂታል እና በማኅበራዊ ሚዲያዎች በኩል በሰባት ቋንቋዎች የሚዘጋጁ ዓለም አቀፍ መድረኮችን በበላይነት እና በዋና ሥራ አስከያጅነት አገልግልለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ አልቫራዶን ለቅድስት መንበር መገናኛ ጽሕፈት ቤት በመሾም በቀድሞው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮ የተጀመረውን የቅድስት መንበር ከፍተኛ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች የተሃድሶ ሂደትን ቀጥለዋል። ይህም በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ውስጥ ለወንድ እና ሴት ምዕመናን የአመራር እና የኃላፊነት ቦታዎችን በአደራ መስጠትን የሚያሳይ ሲሆን፥ አልቫራዶ የቅድስት መንበር መገናኛ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሆነው የተሾሙ የመጀመሪያዋ ሴት ምዕመን እንደሆኑ ታውቋል።
ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ በቅድስት መንበር ሥር በሚገኙ ከፍተኛ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤቶች ውስጥ በጀመሩት የተሃድሶ መርሃ ግብር መሠረት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በሰኔ 27/2015 ዓ. ም. የቫቲካን ዜናን፣ የቫቲካን ሬዲዮን፣ የ“ሎሴርቫቶሬ ሮማኖ” ጋዜጣን፣ የቫቲካን ሚዲያዎችን ማለትም የፎቶ፣ የድምጽ እና የቪዲዮ አገልግሎቶችን፣ መግለጫ ክፍልን፣ የቫቲካን ማተሚያ ቤት እና የፊልም ማኅደር ክፍልን በቅድስት መንበር መገናኛ ጽሕፈት ቤት እንዲመሩ ማድረጋቸው ይታወሳል።
የቅድስት መንበር መገናኛ ጽሕፈት ቤት ከተጠቀሱት ቴክኖሎጂያዊ ተግባራት በተጨማሪ የቤተ ክርስቲያኒቱን እንቅስቃሴ በመገናኛ መስክ ውስጥ ሥነ-መለኮታዊ እና ሐዋርያዊ አገልግሎት ገጽታዎችን የሚያጎለብት እና የሚያዳብር እንደሆነ ታውቋል።
አልቫራዶ ከዚህ በፊት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ2018 ዓ. ም. ከፍተኛ ጳጳሳዊ ጽሕፈት ቤትን እንዲመሩት የሰየሟቸውን የመጀመሪያ ወንድ ምዕምን ዶ/ር ፓኦሎ ሩፊኒን እንደሚተኩ ታውቋል።
አልቫራዶ ሹመታቸው ከታወቀ በኋላ በሰጡት መግለጫ፥ “ይህ ሹመት ያልጠበቁት ቢሆንም፥ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከፍተኛ የሐዋርያዊ አገልግሎት ሥልጣን የተቀበሉበት ወቅት በመሆኑ ላገለግላቸው ልባዊ ፍላጎት አለኝ” ብለው፥ ዶ/ር ፓኦሎ ሩፊኒ ባለፉት ዓመታት ላሳዩት አመራር አመሰግናለሁ፤ በሮም እና በየትኛውም ቦታ ኢየሱስ ክርስቶስን ለዓለም ማቅረብን በወዳጅነት እና በተስፋ የጽሕፈት ቤቱን አገልግሎት ማጠናከር እንደሚቀጥሉ እጠብቃለሁ” ብለዋል።
ዶ/ር ፓኦሎ ሩፊኒ ለቅድስት መንበር መገናኛ ጽሕፈት ቤት ሠራተኞች በላኩት ደብዳቤ፥ ጽሕፈት ቤቱ በፍጥነት ከሚለዋወጠው የመገናኛ ዓለም ጋር ሳያቋርጥ የመጣጣም ግዴታ እንዳለው ገልጸው፥ እንደ ተቋም ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ የሚመራቸው ይህ እንደሆነ እና አሁንም እንደሚመራቸው ገልጸው፥ በዚህ ሰዓት እና በጊዜ ሂደት የሚያድግ የኅብረት እና የመገናኛ መሣሪያ ሆኖ መገኘት እንደሚገባ አሳስበዋል።
ከወ/ሮ ሞንሴራት አልቫራዶ ጋር በሚገባ እንደሚተዋወቁ የገለጹት ዶ/ር ፓኦሎ ሩፊኒ፥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አንድ በሚያደርጋቸው በኅብረት መንፈስ ተቀራርበው እንደሚሰሩ ተናግረው፥ በርካታ ቁጥር ላላቸው የጽሕፈት ቤቱ ሠራተኞችም ባስተላለፉት መልዕክት፥ ባለፉት ስምንት ዓመታት አብረው ላደረጉት ጉዞ አመስግነው፥ የቅድስት መንበር መገናኛ ጽሕፈት ቤት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳትን በአንድነት እና በግልጽነት መንፈስ የማገልገል ተልዕኮው እያደገ እንዲሄድ ለመርዳት በሚቀጥሉት ወራት ውስጥ ቀስ በቀስ ሽግግር ማድረግ መጀመራቸውን አስረድተዋል።
በ “Eternal Word Television Network” (EWTN) የመገናኛ ተቋም ውስጥ የቦርድ ሊቀ መንበር እና ዋና ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ሚካኤል ፒ. ዋርሶ በበኩላቸው፥ ወ/ሮ አልቫራዶ በኔትወርኩ ውስጥ ባሳለፏቸው ዓመታት አብሮአቸው ከሚሠሩት ሰዎች እምነት እና አክብሮት ማግኘታቸውን ተናግረው፥ አክለውም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛን ማገልገል በሚጀምሩበት በዚህ ከፍተኛ ተልዕኮ የ“Eternal Word Television Network” (EWTN) ሠራተኞች ሙሉ የጸሎት እና የማበረታቻ ድጋፍ እንደሚያቀርቡላቸው አረጋግጠዋል።
