ፈልግ

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ በሮም የተባበሩት መንግሥታት የዓለም የምግብ ፕሮግራም ዋና ጽ/ቤት ንግግር ሲደርጉ ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ በሮም የተባበሩት መንግሥታት የዓለም የምግብ ፕሮግራም ዋና ጽ/ቤት ንግግር ሲደርጉ  (@Vatican Media)

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ከሰዎች ይልቅ ግጭቶች እየዳበሩ እንደሚገኙ ተናገሩ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በሮም በሚገኘው የተባበሩት መንግሠታት ድርጅት ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት የዓለም የምግብ ፕሮግራም ዋና መሥሪያ ቤትን (WFP) ጎብኝተዋል። ቅዱስነታቸው በጉብኝታቸው ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፥ ምግብ፣ ውሃ እና የጤና አጠባበቅ ለፖሊቲካ ፍላጎቶች ተገዢ መሆን እንደማይችሉ ገልጸው፥ አገራት ከአዲሱ የባለብዙ ወገናዊነት ጋር ተባብረው እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ረሃብንና የተመጣጠነ ምግብ እጥረትን የመጋፈጥ አጣዳፊ ተግባርን በጋራ እናከናውናለን፤ እንዲሁም እነሱን የሚደግፉትን መሠረታዊ መዋቅራዊ ምክንያቶች እንፈታለን። ይህንን ተግባር በብቃት ለመወጣት ከፊታችን ያሉትን ተግዳሮቶች፣ መሠረታዊ መንስኤዎቻቸውን እና ወደ ዘላቂ መፍትሄዎች የሚወስዱትን መንገዶች መመርመር አለብን” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ይህን የተናገሩት ሰኞ ሰኔ 15/2018 ዓ. ም. በሮም ለሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት የዓለም የምግብ ፕሮግራም ሥራ አስፈፃሚ ቦርድ ባደረጉት ንግግር ሲሆን፥ በሰጡት አስተያየትም፥ እንደ ውሃ፣ ምግብ እና የጤና አጠባበቅ ያሉ መሠረታዊ ፍላጎቶች ለጂኦፖሊቲካዊ ፍላጎቶች ተገዢ መሆን እንደማይችሉ አፅንዖት ሰጥተዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ በግጭቶች እና በተፈጥሮ አደጋዎች መካከል የምግብ ዕርዳታ ለተጎዱት በማቅረብ ሕይወትን ለማዳን ላሳየው ቁርጠኝነት መሥሪያ ቤቱን አመስግነው፥ የወንጌል ጥሪን መሠረት በማድረግ የወንድማማችነት መንፈስ ለማጎልበት ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ካላት ተልዕኮ ጋር በእጅጉ የሚስማማ መሆኑን አስታውሰዋል።

“ዛሬ ቀውሶች ከተለዩ ክስተቶች ወደ ዘላቂ እውነታዎች በመሸጋገር፥ በረጅም ጊዜ ግጭቶች፣ ሥር በሰደደ የምግብ ዋስትና ማጣት፣ በኢኮኖሚ ተለዋዋጭነት እና እየጨመረ በሚሄደው የአየር ንብረት ተጋላጭነት ተለይተው ይታወቃሉ” ብለዋል።

ይህ እውነታ “ምን ዓይነት ስሌት የዓለም አቀፍ ሥርዓትን እንደገና ማባዛት እና አንዳንድ ጊዜም እነዚህን ሁኔታዎች መደበኛ ማድረግ ይችላል?” የሚለውን መሠረታዊ ጥያቄ እንደሚያስነሳ ገልጸው፥ “ጉዳዩ ከአሁን በኋላ ጣልቃ መግባት በሚቻልበት መንገድ ላይ ብቻ የተወሰነ ሳይሆን ሥርዓቱ ሳያቋርጥ መስተካከል የሚገባውን ችግር ለምን መልሶ እንደሚያመጣ ለመረዳት የሚያግዝ ነው” ብለዋል።

በመጨመር ላይ የሚገኝ የተወሳሰበ ዓለም አቀፍ ሥርዓት

ዓለም አቀፉ ሥርዓት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተወሳሰበ መምጣቱ በከፊል ከባለብዙ ወገን ሥርዓት ቀውስ የመነጨ መሆኑን በሐዘን ገልጸው፥ በእነዚህ ጉዳዮች እና በብዙ ወገን ትብብር መካከል ያለውን የጠበቀ ግንኙነት ችላ በማለት መንግሥታት ሃብታቸውን ለብሔራዊ ደህንነት፣ ለኢኮኖሚ እድገት እና ለአገር ውስጥ መረጋጋት እያከፋፈሉ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በአንድ በኩል የሰብዓዊነት እርምጃ ለተቸገሩ ሰዎች ዕርዳታን ሊያዘገዩ በሚችሉ የቢሮክራሲ ሂደቶች ውስጥ የሚገኝ መሆኑን በሌላ በኩል ደግሞ ምግብን ጨምሮ አስፈላጊ የሆኑ መሠረታዊ ቁሳቁሶች ተደራሽነት ብዙውን ጊዜ በኢኮኖሚያዊ ወይም በስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ተጽዕኖ የሚደረግበት መሆኑን ተናግረዋል።

ከሰዎች ይልቅ የግጭቶች በቀላሉ ማደግ

በአደጋው ምክንያት ሊለካ የማይችል እሴት ያላቸው ሰዎች እየተረሱ መምጣታቸውን በምሬት ገልጸው፥ ይህም ከባድ የሥነ-ምግባር ፈተናን እንደሚፈጥር እና የሰው ልጅ ከአሁን በኋላ በዓለም አቀፍ እርምጃ ላይ በቋሚነት እንደማይቀመጥ አስረድተዋል።

በዚህ አውድ ውስጥ ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ፥ “የዕርዳታ እና የልማት ፕሮጀክቶች ለመረዳት በማይችሉ የፖለቲካ ውሳኔዎች፣ በተዛቡ ርዕዮተ ዓለማዊ ራዕዮች ሲደናቀፉ ነገር ግን የጦር መሣሪያ ምርት እና ጥቅም የማይደናቀፍ መሆኑን መገንዘብ አስፈላጊ ነው” ሲሉ መናገራቸውን ቅዱስነታቸው አስታውሰዋል።

“ግጭቶች ሰዎች ከሚመገቡት በላይ ይመገባሉ” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ “ይህ እውነታ የአሠራር ጉድለቶችን ብቻ ሳይሆን በፖለቲካዊ እና በሥነ ምግባራዊ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች ላይ መሠረታዊ አለመመጣጠን መኖሩን ያንፀባርቃል” ብለዋል።

የ “WFP” መኖር ቀውሶች እንዳይባባሱ ያግዛል

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ የውጤቱ አስከፊነት ጉዳቱ ከደረሰባቸው በላይ እንደሚዘልቅ ገልጸው፥ ረሃብ ከሰብዓዊ ጉዳይ በላይ ማኅበራዊ ትስስርን እንደሚያበላሽ፣ የግጭት አደጋን እንደሚጨምር እና አስገዳጅ ስደትን እንደሚያስፋፋ አስረድተዋል።

ከዚህ አንፃር የሰብዓዊነት እርምጃ ከዓለም አቀፍ ሥርዓት ውጭ እንዳልሆነ አፅንዖት ሰጥተው፥ አንድነትን ለማጠናከር፣ መገለልን ለመቋቋም እና ለእያንዳንዱ ሰው እግዚአብሔር የሰጠውን ውስጣዊ ክብር ለመገንዘብ ያለውን የዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ኃላፊነት አጉልተው ገልጸዋል።

በዚህ መልኩ የዓለም የምግብ ፕሮግራም ከፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ቴክኒካዊ ተዋናይነት በላይ የሆነ የዓለም አቀፍ አንድነት ተጨባጭ መግለጫ እንደሆነ ገልጸው፥ “ፕሮግራሙ በእርግጥም ብሔራዊ ተቋማት ሲጠፉ፣ የማኅበረሰብ አውታረ መረቦች ሲበታተኑ እና ሰብዓዊ ቀውሶች ወደማይቀለበስ ውድቀት እንዳይሸጋገሩ ለመከላከል ይረዳል” ብለዋል።

ለባለብዙ ወገን ትብብር የሚሆን አዲስ ቁርጠኝነት

በዚህ ምክንያት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ለባለብዙ ወገን ትብብር አዲስ ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ አፅንዖት ሰጥተው፥ የዓለም መንግሥታትን እና ሕዝቦችን ቁርጠኝነታቸውን እንዲያድሱ እና እንዲያጠናክሩ፣ ረሃብን እና ዋና ዋና ምክንያቶቹን ለመዋጋት የሚረዱ ሃብቶችን እንዲጨምሩ እና ዕርዳታ ለተቸገሩ ሰዎች እንዳይደርስ የሚያግዱ እንቅፋቶችን እንዲያስወግዱ ጠይቀው፥ እንደዚሁም እንዲህ ዓይነቱ ድጋፍ ከቤተ ክርስቲያን እና ከሲቪል ማኅበረሰብ ጋር ያለውን ግንኙነት ማጠናከር እንዳለበት አሳስበው፥ “የእነዚህን ሁሉ ተዋናዮች አቅም ማስተባበር ረሃብን በመዋጋት ረገድ የጋራ ውጤታችንን ያሳድጋል” ብለዋል።

የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን የዕርዳታ ጥረቶችን መደገፍ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን በአብያተ ክርስቲያናት፣ በሀገር ስብከት፣ በ “ካሪታስ” የዕርዳታ ድርጅቶች እና በሌሎች የእምነት ተቋማት በተመሠረቱ ውጥኖች በኩል ብዙውን ጊዜ ዓለም አቀፍ ተዋናዮች በማይደርሱባቸው አካባቢዎች ተጋላጭ ለሆኑ ሰዎች እንደምትደርስ በመጥቀስ፥ የዓለም የምግብ ፕሮግራም እና አጋሮቹ ለእነዚህ ጥረቶች የሚያደርጉትን ድጋፍ እንዲቀጥሉ አበረታተዋል።

በዚህ ረገድ የዓለም የምግብ ፕሮግራም ከአደጋ ጊዜ ምላሽ ሥራዎች በዘለለ የረጅም ጊዜ ተነሳሽነቶችን ማለትም ለትምህርት ቤት ልጆች ምግብ በሚሰጡ ፕሮግራሞች ላይ እንዲሠራ መደረጉን አድንቀዋል።

በአደጋ መከላከል ዓለም አቀፍ ትብብር ያለው ተአማኒነት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ንግግራቸውን ከማጠቃለላቸው በፊት በሰጡት ጥብቅ ማስጠንቀቂያ፥ “በአደጋ መከላከል ላይ የኤጀንሲው ውጤታማነት ብቻ ሳይሆን የዓለም አቀፍ ትብብር ተዓማኒነትም ጭምር ነው” ብለው፥ ይህም ድርጅቱ አዲስ መንገድ ማመቻቸቱን ያሳያል ብለዋል።

ይሁን እንጂ ይህ ከመጠን በላይ ውስብስብ የሆነውን ነገር ለማቅለል፣ አስፈላጊ ለሆኑ ነገሮች ቅድሚያን ለመስጠት እና ማንም ሰው እንዳይረሳ ለማድረግ ቁርጥ ውሳኔ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፥ በመጨረሻም እግዚአብሔር ጥረታቸውን እንዲባርክላቸው በመጸለይ፥ “ሁሉም ሰው የዕለት እንጀራቸውን አግኝቶ በክብር እንዲኖሩ” በማለት ጸሎታቸውን አቅርበዋል።

23 Jun 2026, 16:35