ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ ክርስቲያኖች ከራስ ወዳድነት የጸዳ ማንነታቸውን ወደ ዓለም እንዲያመጡ አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የስፔይን ሐዋርያዊ ጉብኝታቸው የመጀመሪያ ምዕራፍ ማክሰኞ ሰኔ 2/2018 ዓ. ም. ባገባደዱበት ወቅት ሌሎች ሰዎች በሐዋርያዊ ጉብኝታቸው እንዲደሰቱ ለማድረግ ከተባበሩት በጎ ፈቃደኞች ጋር ተገናኝተው መልዕክት አስተላልፈዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በጎ ፈቃደኞችን ለአገልግሎታቸው አመስግነው፥ አገልግሎታቸውም ለእግዚአብሔር፣ ለቤተ ክርስቲያን እና ለርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ባላቸው ፍቅር የተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
በጎ ፈቃደኞችን ለልግስናቸው ያመሰገኑት ቅዱስነታቸው፥ ለቀረበላቸው ጥሪ ፈጣን ምላሽ መስጠታቸውን ጠቅሰው፥ ብዙዎቹ ከሚፈለገው በላይ ጊዜያቸውን የሰጡ መሆኑን ተናግረዋል።
በቅዱስነታቸው የስፔይን ሐዋርያዊ ጉብኝት ወቅት ብዙ ሰዎች ከሥራ ገበታ የዕረፍት ፍቃድ መውሰዳቸው እና ሌሎች ደግሞ ለወራት ያህል ሙሉ ጊዜያቸውን መስጠታቸው ታውቋል።
“እያንዳንዳችሁ በምትችሉት ሁሉ ልባችሁን፣ እጃችሁን፣ ሃሳባችሁን፣ ተሰጥኦአችሁን እና ደስተኛነታችሁን አቅርባችኋል” ብለው፥ ለዚህም እግዚአብሔር ራሱ በሚያውቀው መንገድ ይክሳችሁ!” ብለዋል።
ቅዱስነታቸው በመቀጠልም፥ በየቦታው ያሉ ክርስቲያኖች ከራስ ወዳድነት የጸዳ ማንነትን ለዓለም እንዲያቀርቡ አበረታትተው፥ የእርሾን ምሳሌ በማስታወስ፥ የበጎ ፈቃደኞች ልግስና ክርስቲያኖች ለሌሎች በሚያደርጉት እንክብካቤ ኅብረተሰቡን እንዴት ማርካት እንዳለባቸው ማወቃቸውን ያሳያል” ብለዋል።
“ከራስ ወዳድነት ነጻ የሆነ ማንነት እንደ እርሾ የኅብረተሰቡ ሰብዓዊ፣ ሥነ-ምግባራዊ እና መንፈሳዊ ገጽታዎች እንዲያድጉ የሚያደርግ ልዩ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው” ብለዋል።
ምንም እንኳን ብድር መመለስ ለማይችሉት የተደረገ መልካምነት ቢሆንም፥ በራስ ጥቅም እና በትርፍ ፍለጋ በተሞላው ዓለማችን ውስጥ ክርስቲያኖች ወደ አንድነት እና የሰው ልጅ ዕድገት በሚያመራ መንገድ መጓዝ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
“ኢየሱስ ክርስቶስ እርሾን ወደሚመስል ዓለማችን ውስጥ የሰማይ መንግሥቱን በማምጣት የታመመውን ሰብዓዊነታችንን በመሥዋዕቱ እና በመንፈስ ቅዱስ እሳት ይፈውሳል” ብለዋል።
“ኢየሱስ ከርስቶስ ከሞቱና ከትንሣኤው በኋላ ደቀ መዛሙርቱን በዚያው የመንፈስ ቅዱስ ኃይል በመሙላት በዓለም ላይ የፍቅር፣ የፍትህ እና የሰላም መንግሥት ምልክቶች እና መሣሪያዎች እንዲሆኑ ልኳቸዋል” ብለዋል።
“ክርስቲያኖች የእግዚአብሔርን መንግሥት በስብከታቸው፣ በተለይም ከወንጌል ጋር በሚስማማው የአኗኗር መንገዳቸው ያሰራጩታል” ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በጎ ፈቃደኞቹ ላሳዩት ልግስና በድጋሚ አመስግነው፥ በእግዚአብሔር ፍቅር የተመሰለው ሥራ ማድሪድን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እንድትቀርብ እንደረዳት ተናግረዋል።
“ይህ ሁሉ የእግዚአብሔር ጸጋ ነው!” ያሉት ቅዱስነታቸው፥ ምስጢሩም ፀሐይን እና ከዋክብትን የሚያንቀሳቅሰውን የእግዚአብሔር ፍቅር ኢየሱስ ክርስቶስን ያገኙትን ሰዎች ልብ እንደሚያበረታታ እና ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ በረከት እንዳለው አስረድተዋል።
በመልዕክታቸው ማጠቃለያ፥ ጉብኝታቸውን ያመቻቹላቸው በጎ ፈቃደኞች በእነዚህ ቀናት ውስጥ ልምዳቸውን በትህትና፣ በእምነት ጽናት እና በልግስና እንዲያሰራጩ ብርታትን ተመኝተውላቸዋል።
