ፈልግ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከድሆች ጋር ማዕድ የተጋሩበት ዝግጅት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከድሆች ጋር ማዕድ የተጋሩበት ዝግጅት   (@Vatican Media)

ር. ሊ. ጳ. ሊዮ በዓለም የድሆች ቀን መልዕክት “እግዚአብሔር የድሆች መጠጊያ ነው” ሲሉ አስገነዘቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለ10ኛው ዓለም አቀፍ የድሆች ቀን ባስተላለፉት መልዕክት፥ እግዚአብሔር የድሆች መጠጊያ መሆኑን በመናገር፥ ክርስቲያኖች የድሆችን ማዕከላዊነት በሚገባ በማወቅ ለፍትህ፣ ለአብሮነት እና ለሰው ልጅ ክብር ያላቸውን ቁርጠኝነት እንዲፈትሹ አሳስበዋል።

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በመጭው ዓመት ኅዳር 6/2019 ዓ. ም. ለሚከበረው 10ኛው የዓለም የድሆች ቀን መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመዝ. 14:6, “የምስኪኖችን ዕቅድ ታዛባላችሁ፥ እግዚአብሔር ግን መጠጊያቸው ነው” በሚለው ላይ በማሰላሰል፥ በኢየሩሳሌም የሚገኘው ቤተ መቅደስ በወደመበት አስጨናቂ ወቅት ሕዝቡ የእግዚአብሔርን መኖር እንዳያውቅ ተነፍጎ ታይቶ የማይታወቅ ቁሳዊና ሥነ ምግባራዊ ችግር ባጋጠመው ጊዜ የተጻፈ መሆኑን ተናግረዋል።

የርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ የድሆች ቀን መልዕክት ይፋ የሆነው፥ የፓዶቫው ቅዱስ አንጦንዮስ ዓመታዊ ክብረ በዓል በተከበረበት በሰኔ 6/2018 ዓ. ም. መልዕክት ሲሆን፥ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሱ ለትውልድ ሁሉ መናገር መቀጠሉንም አስረድተዋል።

የመክፈቻ ጥቅሶቹ በጥበብ በሚኖሩ እና “ከእኛ የሚበልጥ የለም” ብለው በሚያስቡ ሰዎች መካከል ያለውን ልዩነት እንደሚያመላክቱ ተናግረው፥ “ዛሬም ቢሆን ከትምክህተኝነት እና ከሙስና የሚመነጩ ኢ-ፍትሐዊ የሆኑ ማኅበራዊ ድርጊቶች ሲፈጸሙ እና ይህም አድሎአዊ የመሆኑን ያህል አሳዛኝ ነው” ሲሉ ጽፈዋል።

የድሆች ድምጽ እንዲታፈን አትፍቀዱ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በመቀጠልም፥ መዘዙ ብዙውን ጊዜ በድሆች ላይ እንደሚወድቅ ገልጸው፥ ቁጥራቸውም በብዙ ማኅበረሰቦች ዘንድ እያደገ መሆኑን ተናግረዋል።

“የእግዚአብሔር አለመኖር ሰዎች እርስ በርስ ተከባብረው አንድ ላይ እንዳይኖሩ ያደርጋቸዋል፤ አንዱን ከሌላው በማበላለጥ ጭቆና እንዲበረታ ያደርጋል” ብለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ የድሆች ጩኸት ብዙውን ጊዜ እጅግ እየጨመረ በሚሄድ ስውር ዘዴ እንደሚደፈን እና የዲጂታሉ ዓለምም ጭፍን ጥላቻን በማባባስ ግዴለሽነትን ሊያጠናክር እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

“ድሆች ወደ እግዚአብሔር ዘንድ ከመጮህ ሌላ ምንም አማራጭ የላቸውም” ብለው፥ ራሳቸውን ለእርሱ እንዲያቀርቡ፥ እግዚአብሔር ታማኝ እና በምሕረቱ ባለ ጠጋ በመሆኑ እንደሚሰማቸው እርግጠኛ ይሁኑ” ሲሉ ጽፈዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ በመልዕክታቸው፥ ከሌሎች ይልቅ ድሆች የሚያስፈልጋቸውን ነገር የመለየት ችሎታ እንዳላቸው እና በአስፈላጊ ነገር ላይ ብቻ እንደሚያተኩሩ አስረድተዋል።

በዚህም ምክንያት በተለይም እግዚአብሔር መጠጊያቸው መሆኑን በመገንዘብ በፍትሕ ላይ ተስፋ ማድረግ እንደሚችሉ ተናግረዋል።

በዚህ ወቅት በሚታይ ድህነት ላይ ያሰላሰሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “በዘመናችን ያሉ ድሆች የተረሱ እና የተገለሉ፥ ዳቦን ብቻ ሳይሆን ድምጽን እና ፊትንም የተዘረፉ ናቸው” ብለዋል።

ይህን በማሰብ በተለይም በክርስቲያኖች እና በቤተ ክርስቲያን በኩል ክርስቶስን እንዲያኙት ጸሎታቸውን አቅርበው፥ “የዕለት እንጀራን እና ወዳጅነትን የሚያቀርብ፣ ብርሃንን የሚያመጣ፣ የተስፋ አድማስን የሚከፍት፣ እያንዳንዱን ሰው በስም ጠርቶ ለሁሉም ክብርን የሚሰጥ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው” ብለዋል።

በመቀጠልም ክርስቲያኖች የተጠሩት በእግዚአብሔር ዘንድ መሸሸጊያን ለመፈለግ ብቻ ሳይሆን የድሆች መሸሸጊያ እንዲሆኑ ጭምር መሆኑን አስገንዝበዋል።

“ክርስቲያኖች ዛሬ በራቸው ላይ የሚቆሙትን እና ራሳቸውን ዘግተው ለሚቆዩት የማይታዩ በርካታ ሰዎችን ችላ ማለት አይችሉም” ብለዋል

ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ነገሮች መለየት

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ ቅዱስ አጎስጢኖስ ስለ ሃብታሙ እና ስለ ደሃው አልዓዛር ምሳሌ የሰጠውን አስተያየት በማስታወስ፥ ምእመናን የራሳቸውን ሕይወት እና ቅድሚያ የሚሰጥባቸውን ነገሮች እንዲመረምሩ ጋብዘዋል።

“ወድጄሃለሁ!” የሚለውን ሐዋርያዊ ምክራቸውን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፥ እግዚአብሔር ድሆችን እንደሚወድ ሁሉ ቤተ ክርስቲያንም ለተናቁት ቦታን የምትሰጥ እና ከድሆች ጋር የምትጓዝ የብፁዓን ቤተ ክርስቲያን መሆን አለባት” ብለዋል።

በመልዕክታቸው ማጠቃለያ፥ “እራሳችንን በድሆች ጫማ ውስጥ በማስገባት እና ስለ እነርሱ ከመናገር ይልቅ በማዳመጥ ተመሳሳይ ደስታ ማግኘት የሚቻል መሆኑን ዛሬም ቢሆን መመስከር እንወዳለን” ሲሉ ጽፈዋል።

በመጨረሻም፥ አሥረኛው የዓለም የድሆች ቀን፥ ክርስቲያኖች በእግዚአብሔር ዘንድ መሸሸጊያን የሚሹትን እና በማኅበረሰባችን ውስጥ እንደ ቤተኛ ለመኖር የሚናፍቁ የበርካታ ወንድሞች እና እህቶች ፊት እንደገና ለማግኘት እንደሚረዳቸው ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

16 Jun 2026, 16:26