ፈልግ

2026.06.14 Angelus 2026.06.14 Angelus  (@Vatican Media)

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ክርስቲያኖች ለጥላቻ በፍቅር ምላሽ እንዲሰጡ አሳሰቡ

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ እሑድ ሰኔ 14/2018 ዓ. ም. በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ከተሰበሰቡት ምዕመናን ጋር ሆነው የብስራተ ገብርኤል ጸሎት አድርሰዋል። በዕለቱ በተነበበው ቅዱስ ወንጌል ላይ በማስተንተን ባሰሙት ቃለ ምዕዳን፥ ክርስቲያኖች ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ካላቸው የጠበቀ ግንኙነት ጥንካሬን በማግኘት ተልዕኳቸውን በማሰላሰል እንዲተገብሩ አሳስበው፥ በሁሉም ሁኔታዎች ውስጥ ቢገኙም ወንጌልን በተስፋ፣ በፍቅር እና በጽናት እንዲመሰክሩ አበረታትተዋል።

ክቡራት እና ክቡራን፥ ከዚህ ቀጥሎ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለምዕመናን ያሰሙትን ቃለ-ምዕዳን ትርጉም ሙሉ ይዘቱን እንደሚከተለው እናቀርብላችኋለን፥

የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን

“ውድ ወንድሞቼ እህቶቼ፥ መልካም ዕለተ ሰንበት ይሁንላችሁ! ከማቴ 10:26-33 ተወስዶ በተነበበው በዛሬው ወንጌል ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱን ለአገልግሎት ሲልካቸው እንዲህ ሲል መከራቸው። ‘በጨለማ የነገርኳችሁን በብርሃን ተናገሩ፤ በጆሮአችሁ የሰማችሁትንም በሰገነት ላይ ስበኩ’ (ማቴ. 10:27)።

በግል የምንሰማውን ማለትም በልባችን ውስጥ ያለውን ምስጢር እና ለሰዎች እንድናውጅ በተጠራነው መካከል ያለውን ተመሳሳይነት ይገልጻል። ወንጌልን ማወጅ በመጀመሪያ ደረጃ ለእያንዳንዳችን ልዩ እና ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር የግል ግንኙነት ማድረግ ነው።

ከአቀራረብ እና ከምንጠቀምባቸው መንገዶች ባሻገር የማናችንም ሐዋርያዊ ጥንካሬ የሚመነጨው በውስጣችን ካለው የመንፈስ ቅዱስ ሥራ እና ከምላሻችን ትክክለኛነት ነው። ቅዱስ ቶማስ አኩዊናስ ‘ስብከት ማለት የምናስበውን ነገር ለሌሎች የምናስተላልፍበት መንገድ’ ሲል ይገልጻል። “contemplata aliis tradere” (cf. Summa Theologiae, III, q. 40, a. 1, ad 2)።

በጽሞና ማሰላሰል ለቅዱሳን፣ ለመነኮሳት ወይም ለባህታውያን ብቻ የተወሰነ ልዩ ተሞክሮ አድርገን ማሰብ የለብንም። ሁላችንም በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ውስጥ ወደ እግዚአብሔር ፊት በጸጥታ ቀርበን ድምፁን ለመስማት፣ ደስታችንን እና ጭንቀታችንን ለእርሱ ለመንገር እና ሕይወታችንን ከእርሱ ጋር ለመፈተሽ የሚያስችሉ የጽሞና ጊዜያት ሊኖሩን ይገባል። ይህም የበለጠ ጠንካራ እና ግልጽ እምነት እንዲኖረን ያግዘናል። የቅዱስ ወንጌልን እሴት፣ ብዙዎች ባይረዱት እና ባይቀበሉትም በእያንዳንዱ የሕይወት ሁኔታ ውስጥ በታማኝነት እና በነጻነት እንድንመሰክር ይረዳናል።

ሐዋርያው ቅዱስ ማቴዎስ የጻፈው የዛሬው የወንጌል ክፍል ሕይወታቸው ቀላል ላልነበራቸው ማኅበረሰቦች የጻፈው ነው። ዛሬም ድረስ በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የሚገኙ ብዙ ክርስቲያኖች ጥላቻን እና ስደትን ይጋፈጣሉ። ተስፋ የመቁረጥ እና ድካም እንዲሁም በፍርሃት የመሸነፍ ፈተናም እጅግ ትልቅ ነበር።

ልክ እንደ ድሮው ሁሉ ለኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርቶች ታማኝ ለመሆን እና ቃሉንም ለመመስከር ፈታኝ በሆነ ጊዜ ውስጥ እንገኛለን። ጥላቻን በፍቅር፣ ትዕቢትን በትሕትና እና ተስፋ መቁረጥን በጽናት ለማለፍ አስቸጋሪ በሆነ ጊዜ ውስጥ እንገኛለን። በዚህ ምክንያት ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ባለን የጠበቀ ግንኙነት እምነታችንን እና ተልዕኮአችንን ማጠናከር አለብን (የወንጌል ደስታ ቁ. 8)። ይህም ተስፋ ሳንቆርጥ በሁሉም ሁኔታ ውስጥ ለሁሉም ሰው የተስፋ፣ የፍቅር እና የሰላም መልዕክት ማካፈልን እንድንቀጥል ጥንካሬን ይሰጠናል። ለዛሬው ዓለማችን ይህ እጅግ ያስፈልገዋል!

እያንዳንዳችን እንደጥሪያችን የኢየሱስ ክርስቶስ ሚስዮናዊ ደቀ መዛሙርት እንድንሆን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ትረዳን” በማለት ቃለ-ምዕዳናቸውን አጠቃልለዋል።

ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከምዕመናን ጋር ሆነው የብስራተ ገብርኤል ጸሎት አድርሰዋል።

 

22 Jun 2026, 16:35