ር. ሊ. ጳ. ሊዮ፥ ካህናት የመልካሙ እረኛ ምስክሮች ሆነው ራሳቸውን ለእርሱ እንዲሰጡ አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “በየቀኑ በምናደርገው እና በሚደርስብን ነገር በሙሉ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር እንሁን” በማለት ቤተ ክርስቲያን የካህናት ቅድስና ቀንን በምታከብርበት ዓርብ ሰኔ 5/2018 ዓ. ም. ለካህናት በላኩት መልዕክት አሳስበዋል።
ቅዱስነታቸው በመልእክታቸው፥ ቅድስና በብዙዎች ዘንድ ምርጫ ወይም ረቂቅ ሃሳብ እንዳልሆነ ተናግረው፥ “ከሞት የተነሳው የኢየሱስ ክርስቶስን ሕይወት ለመካፈል የሚፈልግ የእያንዳንዱን ሰው ማንነት ያካትታል” ብለዋል።
በእግዚአብሔር ላይ በሙላት መታመን
እግዚአብሔር በራሱ ቅድስና እንድንካፈል የሚጋብዘን መሆኑን በአጽንኦት ሲናገሩ፥ ከእኛ የሚጠይቀው ይህ ቅድስና በመንፈስ ቅዱስ እንድንለወጥ የሚያስችል እምነት የሚጣልበት ነው” ብለዋል።
ምድራዊ ብንሆንም ብዙውን ጊዜ ውስኖች እና ፍጽምና የጎደለን፣ ደካማ እና አንዳንድ ጊዜም ብንቆስልም በእግዚአብሔር ቅድስና እንድንካፈል የተጠራን ነን” ሲሉ አስረድተዋል።
ስለዚህ እንዲህ ያለ ደካማ የሰው ልብ ለዚህ ዓይነት ከፍተኛ ጥሪ ምላሽ እንዴት ሊሰጥ ይችላል?” ሲሉ ጠይቀው፥ ከክርስቶስ ልብ ጋር አንድነትን መፍጠር ለጥቂቶች ብቻ የተወሰነ ሳይሆን ነገር ግን በሕይወታችን ውስጥ በየቀኑ የሚገለጥ የቅዱስ ቁርባን ጉዞ እንደሆነ ተናግረዋል።
በንቃት መታደስ አለብን
“በክኅነታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ብንዋቀርም በዕለታዊ መስዋዕተ ቅዳሴያችን፣ በጸሎት፣ በእግዚአብሔር ቃል ላይ በማሰላሰል ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን በትህት በማገልገል የጸጋ ስጦታን በውስጣችን ዘወትር ማደስ አለብን” ብለዋል።
“ሰብዓዊነታችን የተከፋፈለ አይደለም” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ አክለውም፥ ጊዜ ወይም ፍቅር በከንቱ የሚባክን ቢመስለንም ጸሎት፣ አገልግሎት፣ የእርስ በርስ ግንኙነቶች፣ ድካም፣ ደስታ እና ውድቀቶች ሁሉም እግዚአብሔር ራሱን እና ወሰን የሌለውን ፍቅሩን የሚገልጥባቸው ልዩ ቦታዎች ይሆናሉ” ሲሉ አስረድተዋል።
ዝግጁ፣ ትሑት እና ንጹህ ልብ ያለው ካኅን በአገልግሎት መካከል ማሰላሰል፣ በፈተና ጊዜ መሐሪ እና ታማኝ መሆን እንዲሁም በስጦታው ደስተኛ መሆን እንደሚችል ተናግረዋል።
“ዓለም ከቃላት ወይም ከዕቅዶች በላይ የሚያቀርቡ ሐዋርያዊ እረኞች በእጅጉ ያስፈልጉታል” ሲሉ አፅንዖት ሰጥተው የተናገሩት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ የኢየሱስ ክርስቶስን የቅድስና ጣፋጭ መዓዛን የሚያወጣ የታረቀ ልብ ሕያው ምስክርነት ያስፈልገዋል” ብለው፥ “ከኢየሱስ ልብ ጋር የተዋቀረ የክኅነት ሕይወት የአንድነት፣ የሰላም እና የምሕረት ታማኝ ምልክት ነው” ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በመልዕክታቸው፥ “መለያየት እና ፍርሃት ባለበት በዚህ ዘመን የሰላም ግንበኞች እና የተበተኑትን መሰብሰብ እና የቆሰሉትን መፈወስ የሚያውቅ የመልካሙ እረኛ ርኅራኄ ምስክሮች መሆን አለብን” ብለዋል።
ጉድዩ ስለ ፍጹምነት አይደለም
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ለቅድስና ጥሪ የሚሰጥ ምላሽ በአብዛኛው በብቸኝነት ሥራ ወይም ፍጹምነትን በመፈለግ ላይ እንደማይመካ ገልጸው፥ ምንም እንኳን እነዚህ ነገሮች አስፈላጊ ቢሆኑም ነገር ግን በኢየሱስ ክርስቶስ የተወጋ ልብ በተገለጠው ፍቅር በመታመን ላይ ነው” ብለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ፥ “እኛነታችን የሚገለጠው በእኛ ሳይሆን በእኛ ውስጥ በሚኖረው በኢየሱስ ክርስቶስ ነው” ብለው፥ ካኅናት ምዕመናንን እርሱ በሚወዳቸው ፍቅር እንዲወዱ እና ራሳቸውን ሙሉ በሙሉ ለእርሱ እንዲሰጡ አሳስበዋል።
ይህ ፍቅር እኛ እጅ ሰጥተን ራሳችንን ሙሉ በሙሉ ለእርሱ ብንሰጥ ምንም እንደማናጣ የተገባልን ቃል ኪዳን እና ዋስትና ነው” ሲሉ አክለዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ መጨረሻም፥ “ካህናትን እናታቸው ለሆነች ለእመቤታችን ድንግል ማርያም በአደራ በመስጠት፥ የልጇን የኢየሱስ ክርስቶስ ምስጢር በልቧ ውስጥ የጠበቀችው ማርያም፥ በሕይወት እንድንኖር እና የዓለም አዳኝ የሆነው የኢየሱስ ክርስቶስ ልብ በውስጣችን እንዲሠራ ታድርግ” በማለት መልዕክታቸውን ደምድመዋል።
