ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ "ፍቅርን በማሳደግ ጥላቻን በሰላም መተካት ይገባል" ሲሉ አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ረቡዕ ሰኔ 3/2018 ዓ. ም. በስፔይን ሞንትሴራት የሚገኘውን የእመቤታችን ማርያም ገዳም በመጎብኘት ቅድስት ድንግል ማርያም በፍቅሩ ዓመፅን ማስወገድ ወደሚችል ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ እንደምትመራን አስረድተው፥ “የሰላም ንግሥት ቅድስት ድንግል ማርያም የጥላቻ ቃላትን፣ የተሳሳተ ፍርድን፣ ሐሜትን እና ስም ማጥፋትን እንድንተው ታስተምረን” ሲሉ ተናግረዋል።
“ጥላቻ ለተስፋ እና ለሰላም ቦታን እንዲለቅ ለማድረግ ፍቅርን በቤተሰቦቻችን፣ በጓደኞቻችን፣ በሥራ ቦታ፣ በማኅበራዊ ሚዲያ፣ በፖለቲካ ክርክሮች እና በክርስቲያን ማኅበረሰቦች መካከል ማሳደግን እንማር” ሲሉ አሳስበዋል።
የአንድ ሽህ ዓመት ዕድሜ ገዳም
በካታሎኒያ ክልል የሚገኘው የሞንትሴራት ገዳም ከ12ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በአካባቢው የተከበረ መንፈሳዊ ሥፍራ እና የክልሉ ባልደረባ የሆነች የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ መቅደስ የሚገኝበት ቦታ እንደሆነ ይታወቃል። በቅዱስ ብሩክ ገዳም መነኮሳት የሚተዳደረው ገዳሙ የምሥረታውን አንድ ሺህኛ ዓመት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ በ 2025 ዓ. ም. አክብሯል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ወደ ገዳሙ ሲደርሱ በባዚሊካው ዙሪያ ለተሰበሰቡት ወደ 7000 ለሚጠጉ ምዕመናን ሰላምታቸውን ያቀረቡ ሲሆን፥ የሳንት ፌሊዩ ደ ሎብሬጋት ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ዛቢየር ጎሜዝ ጋርሲያ እና የሞንሴራት ገዳም አበምኔት አባ ማኔል ጋሽ ኢ ሁሪዮስ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
ቅዱስነታቸው በባዚሊካው ጸሎት ቤት አጭር ጸሎት ካቀረቡ በኋላ ከበርካታ ምዕመናን ጋር የመቁጠሪያ ጸሎት ከማድረሳቸው በፊት የሀገረ ስብከቱ ጳጳስ እና የገዳሙ አለቃ የአቀባበል ንግግር ያደረጉ ሲሆን ዕድሜያቸው ከ9 እስከ 14 ዓመት የሚሆናቸው በአውሮፓ ጥንታዊ የኤስኮላኒያ መዘምራን ትምህርት ቤት አዳጊ ተማሪዎች ዝማሬያቸውን አሰምተዋል።
“እመቤታችን ማርያም ወደ ጥልቅ ለውጥ ትመራናለች”
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ከመቁጠሪያ ጸሎት በኋላ ምዕመናኑን አመስግነው፥ ፍትህ እና ሰላም በጠማው ዓለም ውስጥ ሐዋርያዊ ተልዕኮአቸውን ወደ ሞንሴራት እመቤታችን ማርያም ዘንድ በማቅረብ የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።
“የቤተ መቅደሱ ግድግዳዎች ወደ ሞንሴራት ማርያም ለዘመናት የቀረቡ ሥፍር ቁጥር የሌላቸውን የአምልኮ፣ የምስጋና እና የተስፋ ታሪኮችን ይነግሩናል” ብለው፥ ቅድስት ድንግል ማርያም የሰዎችን ስሜት ወደ ጥልቅ መለወጥ እንደምታነሳሳ አፅንዖት ሰጥተው ተናግረዋል። በማከልም ምዕመናን የኢየሱስ ክርስቶስን ፍቅር እንዲከተሉ የሚያሳስበውን የቅድስት ድንግል ማርያምን ግብዣ እንዲቀበሉ አሳስበዋል።
“እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በቃና ዘገሊላ የተናገራቸው ቃላት ለክርስትና ሕይወት የሚሆን እውነተኛ መመሪያ ነው” ብለው፥ እመቤታችን ማርያም እኛን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘንድ በመምራት ድምፁን እንድንሰማ፣ ለቃሉ እንድንታዘዝ እና እንድንለወጥ ታስተምረናለች” ሲሉ ተናግረው፥ “‘እርሱ የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ’ ስትለን የዕርቅ ልባችንን ለወንጌል እንድንከፍት ትጋብዘናለች” ብለዋል።
ልባችንን የሚያደነድነውን የመሣሪያ ትጥቅ በማርያም እግር ሥር እናኑር
“ኢየሱስ ክርስቶስ የምሕረት፣ የእርቅ፣ የእውነት እና የገርነት መንገድ ያሳየናል” ሲሉ አጥብቀው የተናገሩት ቅዱስነታቸው፥ “ኢየሱስ ክርስቶስ በቃላችን እና በአመለካከታችን ውስጥ ሊደበቅ የሚችለውን ዓመፅ፥ የሚያዋርድ ትችትን፣ የሚያጠፋ ኩነኔን እና የሚከፋፍል ጠበኝነትን ገሃድ ያደርገዋል” ብለው፥ “ያ የተደበቀ ዓመፅ ብዙውን ጊዜ ቁስላችንን፣ ፍርሃታችንን እና በፍትሕ መጓደል ምክንያት የሚመጣውን ስቃይ ለመጠበቅ የሚያግዝ መስሎ ሊቀርብ ይችላል” ብለዋል።
“ልባችንን የሚያደነድነውን የመሣሪያ ትጥቅ ኢየሱስን በጭኗ የተሸከመች እና እርስ በርሳችን እንድንዋደድ በምትጋብዘን በእመቤታችን ማርያም እግር ሥር እናስቀምጥ” ሲሉ አሳስበው፥ “ማርያም የታቀፈችው ሕፃን ኢየሱስ ያለ ምንም ትጥቅ በመስቀል ላይ ራቁቱን ሆኖ በፍቅሩ ኃይል ሊያድነን ራሱን ለአብ ስጥቷል” ብለዋል።
የሞንሴራት እመቤታችን ማርያም በቀኝ እጇ ሉል መያዟን ያስታወሱት ቅዱስነታቸው፥ ይህም ለመላው ዓለም የምታደርገው የእናትነት እንክብካቤ ምልክት እንደሆነ አብራርተው፥ “ማንም እንዳይገለል፣ ኅብረታችን የበለጠ ጠንካራ እንዲሆን፣ እርስ በርሳችን ወንድማማቾች እና እህትማቾች እንድንሆን ትጋብዘናለች” ብለዋል።
“ዓይኖቻችንን ወደ እመቤታችን ማርያም በማንሳት የእግዚአብሔርን የዕርቅ እና የሰላም መሣሪያን ብቻ ለመታጠቅ እንድትረዳን እንለምናት” በማለት በሞንሴራት እመቤታችን ማርያም ምስል ፊት ጸሎታቸውን አቅርበዋል።
ምዕመናኑን ለጠንካራ እምነታቸው አመስግነው፥ “አንድ ቤተሰብ ሆነን የሞንሴራት ማርያም እናታችንን ተቀብለናል” ብለው፥ በእነዚህ ቀናት ውስጥ በመጀመሪያ በማድሪድ፣ ቀጥሎ በባርሴሎና፣ አሁን ደግሞ በካታሎኒያ እና እንዲሁም በቅርቡ በካናሪ ደሴቶች እያጋጠመ ያለውን ደስታ፣ ጉጉት እና ጥልቅ የእምነት ስሜት በማስታወስ፥ መላው ስፔይን በእምነት እና በፍቅር በመሞላት እግዚአብሔርን ለማመስገን አንድ የመሆን ፍላጎት አለው” ሲሉ ተናግረዋል።
በመጨረሻም ከሌሎች አገራት የመጡ በርካታ እንግዶችን በእንግድነት የተቀበለውን የካታሎኒያን ማኅበረሰብ አመሰግነው፥ “ይህም ሁሉንም እንደ ቤተሰብ አንድ ላይ ማምጣት የሚቻል መሆኑን ያሳያል” ብለው፥ መነኮሳቱን እና ወደ ሞንሴራት የእመቤታችን ማርያም ገዳም ለጸሎት የሚመጡትን በሙሉ አመስግነዋል።
