ር. ሊ. ጳ. ሊዮ 14ኛ፥ "የወንጌልን ደስታ በአንድነት እና በብዝሃነት መመስከር ይገባል" ሲሉ አሳሰቡ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊይ 14ኛ በማድሪድ በሚገኘው ታዋቂው የሳንቲያጎ በርናቡ ስታዲየም ውስጥ ሰኞ ሰኔ 1/2018 ዓ. ም. አመሻሽ ላይ በመገናኘት፥ የሀገረ ስብከቱ ምዕመናን በፍጥነት እየተለወጠች ባለችው ከተማ ውስጥ መናገር የሚችሉ የተስፋ ምሳሌዎች እንዲሆኑ ግብዣቸውን አቅርበዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በበዓሉ ላይ ንግግር ከማድረጋቸው በፊት፥ በማድሪድ ሀገረ ስብከት ሕይወት የተሳተፉ ምእመናን፣ የሐዋርያዊ ምክር ቤት አባል፣ የሀገረ ስብከት ካኅን፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ አቀባበል እና ድጋፍ ያገኘ ስደተኛ ቤተሰብ እና በቅርቡ ምስጢረ ጥምቀትን የተቀበለ አንድ ጎልማሳ የማድሪድ ቤተ ክርስቲያን ልዩ ልዩ እውነታዎችን የሚያንፀባርቁ የግል ምስክርነቶችን አቅርበዋል።
የምስክርነቶቹ የእምነት፣ የአገልግሎት፣ የማሰላሰል እና የመለወጥ ታሪኮቻቸው ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በምዕምናን ኅብረት፣ በስብከተ ወንጌል እና በዘመናዊው የከተማ ማኅበረሰብ ውስጥ የቤተ ክርስቲያን የሚስዮናዊነት ጥሪን በማስመልከት ላቀረቧቸው አስተያየቶች ሕያው አውድ እንደ ነበሩ ታውቋል።
የእምነት መዝሙር
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በስታዲየሙ ለተሰበሰቡ 80,000 ለሚሆኑ ምእመናን ባደረጉት ንግግር፥ ምሽቱን “ታላቅ የእምነት መዝሙር” ሲሉ ገልጸውት፥ የማድሪድ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ ካርዲናል ሆሴ ኮቦ ካኖ፥ መንፈሳዊ ዜማ እና አንድነት የቤተ ክርስቲያንን ሕይወት የሚረዱበት መንገድ አድርገው በማቅረባቸው አመስግነዋቸዋል።
“አሃዞች፣ መረጃዎች እና እውነታዎች ብቻቸውን ማኅበረሰብን ለመገንባት በቂ አይደሉም” ያሉት ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “ልባችን መዘመር አለበት” ሲሉ አሳስበው፥ ከመንፈሳዊ ዜማ ተምሳሌትነት በመነሳት ቤተ ክርስቲያን ማለት በዜማ ውስጥ የብዙ ቃላት አንድነት የሚገለጽበት የምዕመናን ኅብረት መሆኑን በማሰብ፥አንድነት ልዩነቶችን ሳያስወግድ ነገር ግን ወደ ስምምነት የሚያመጣ መንገድ እንደሆነ አስረድተዋል።
የምስጢረ ጥምቀት የመለወጥ ኃይል
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በተለይም ምስጢረ ጥምቀት የመለወጥ ኃይል እንደሆነ በቀረበው ምስክርነት ላይ በማሰላሰል፥ እምነት የሚለወጠው የግለሰብን ሕይወት ብቻ ሳይሆን ስጦታዎችን እና ተሰጥኦዎችን የመረዳት መንገድም ጭምር እንደ ሆነ አስረድተው፥ “እንደ ግል ስጦታነት የሚታሰበው ምስጢረ ጥምቀት በጋራ ጥቅም አገልግሎት ላይ ያተኮረ ነው” ብለዋል።
በብዝሃነት ውስጥ ያለ አንድነት
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “የሰው ልጅ ታላቅነት” በሚል በቅርቡ ይፋ ያደረጉትን ሐዋርያዊ መልዕክታቸውን በመጥቀስ፥ በብዝሃነት እና በኅብረት መካከል ባለው ግንኙነት ላይ በማሰላሰል ሲናገሩ፥ የኢየሩሳሌምን ቅጥር እንደገና በመገንባት አንድ ሙሉ ማኅበረሰብን ያስተባበረውን መጽሐፍ ነህምያን አስታውሰዋል።
እንደዚሁም ዛሬ ክርስቲያኖች እርስ በርስ በመደማመጥ፣ በጋራ ውይይት እና በሲኖዳዊነት መንገድ ልዩነቶችን ወደ ሃብት ለመቀየር መጠራታቸውን በማስታወስ፥ በተለይም እንደ ማድሪድ ባሉ ትላልቅ ከተሞች ውስጥ ብዙ ባሕሎች፣ ወጎች እና ልምዶች እንደሚገናኙ ተናግረው፥ ማድሪድ ለቤተ ክርስቲያን አዳዲስ ጥያቄዎችን እያቀረበች ለወንጌል አገልግሎት ልዩ ዕድሎችን የምትሰጥ ከተማ እንደሆነች ጠቅሰዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ለምዕመናኑ ባስተላለፉት መልዕክት፥ የሚታወቁ ፈተናዎችን እየተቋቋሙ አዳዲስ የባህል ትረካዎችን እና ማኅበራዊ እውነታዎች እየተቀረጹ ወዳሉበት የከተማዋ ልብ እንዲጓዙ አበረታተው፥ ወደ ከተማዋ ልብ መድረስ የሚቻለው ከእውነት ጋር በመተባበር እና እውነት ዘወትር ከእኛ እንደሚበልጥ ያለንን ግንዛቤ በማዳበር ነው” ሲሉ አስረድተዋል።
ደግነትን ማሳደግ
ደግነት እንደ ክርስቲያን ምስክርነት ያለውን አስፈላጊ ገጽታ አጉልተው የገለጹት ቅዱስነታቸው፥ ብዙውን ጊዜ መከፋፈል፣ እርግጠኛ አለመሆን እና ብቸኝነት በሚታይበት ማኅበረሰቦች ውስጥ የወንጌል ምስክርነት ከእውነተኛ የሰው ልጅ ግንኙነት ተለይቶ ውጤታማ ሊሆን እንደማይችል ተናግረው፥ የማድሪድ ከተማ የበለፀገ ልዩነት በማስታወስ፥ የእግዚአብሔር ምሕረት ያለ ልዩነት እያንዳንዱን ሰው የሚያቅፍ መሆኑን አስታውሰዋል። የቤተ ክርስቲያኒቱ ተልዕኮም በኢየሱስ ክርስቶስ የተገለጸውን ዓለም አቀፍ የሕይወት ሙላት ጥሪ በግልጽ ማሳየት ነው” ሲሉም አክለዋል።
በተለይ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ተቀባይነት ያገኘ ስደተኛ ቤተሰብ ምስክርነት በመጥቀስ፥ ብዙ ሰዎች በጭፍን ጥላቻ ወይም በብስጭት የተሞሉ የፍርሃት ልብ ይዘው የክርስቲያን ማኅበረሰቦችን እንደሚቀርቡ ጠቅሰው፥ “ደግነት ከጥቂት ሰዎች የሚመጣ ቢሆንም የብዙዎችን ፍርሃት ማሸነፍ ይችላል” ብለዋል።
የምዕምናን ሐዋርያዊ ምክር ቤቶች
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ የቁምስናዎች እና የሀገረ ስብከት ሐዋርያዊ ምክር ቤቶች ሚናን አጉልተው በማሳየት ወደ አስተዳደራዊ መዋቅርነት እንዳይቀየሩ አስጠንቅቀው፥ ይልቁንም ምእመናን መንፈስ ቅዱስን አብረው ለማዳመጥ እና እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንን ለዘመናዊ ፈተናዎች ምላሽ እንድትሰጥ እየጠራት መሆኑን የሚያወቁበት እና ለጋራ ግንዛቤ ልዩ ቦታዎች መሆናቸውን አስረድተዋል።
