ር. ሊ. ጳ ሊዮ 14ኛ፥ “የአካባቢ ቀውስ የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ገጽታ ነው” ሲሉ ገለጹ
የዚህ ዝግጅት አቅራቢ ዮሐንስ መኰንን - ቫቲካን
“ለአየር ንብረት ቀውስ ውጤታማ ምላሽ ለመስጠት በኅብረተሰባችን መሠረት ላይ የተገነቡ እና የሁሉ ሰው እኩል ክብር እና መብት የተመለከቱ ማኅበራዊ እና ሥነ-ምግባራዊ ጉዳዮችን መፍታት አለብን” ሲሉ ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ ማክሰኞ ሰኔ 9/2018 ዓ. ም. ይፋ ባደረጉት የቪዲዮ መልዕክት ተናግረዋል።
“የአካባቢ ቀውስ የተናጠል ጉዳይ ሳይሆን ይልቁንም የዘመናዊው ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ሥነ-ምህዳራዊ ገጽታ ነው” በማለት በሰው ሠራሽ አስተውሎት ዘመን የሰውን ልጅ ከጉዳት ለመጠበቅ በማሰብ በቅርቡ ይፋ ባደረጉት “Magnifica humanitas” (የሰው ልጅ ታላቅነት) የሚለውን ሐዋርያዊ መልዕክት ጠቅሰዋል።
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ለአካባቢ ቀውስ ምላሽ ለመስጠት የሚረዱ ሦስት ጭብጦች እነርሱም እምነት፣ ተስፋ እና ፍቅር መሆናቸውን በቪየና በተካሄደው አሥረኛው የኦስትሪያ ዓለም አቀፍ ጉባኤ በላኩት መልዕክት የገለጹ ሲሆን፥ መልዕክታቸውም የአየር ንብረት ቀውስን በማስመልከት ለሚደረግ ውይይት መፍትሄዎችን እና ሃሳቦችን ለማቅረብ ያለመ እንደሆነ ታውቋል።
የአየር ንብረት ቀውስ የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ማሳያ ነው
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ “የሰው ልጅ ታላቅነት” በሚለው ሐዋርያዊ መልዕክታቸው፥ የሁሉም ሰው እኩል ክብር እና መሠረታዊ መብቶች አስፈላጊነትን በማስታወስ፥ የጋራ ጥቅም መርሆዎችን፣ የሸቀጦች ዓለም አቀፍ መዳረሻን፣ የድጎማ ድጋፍን፣ የአንድነት እና የማኅበራዊ ፍትህ መርሆዎችን በአግባቡ በመተግበር በበቂ ሁኔታ ማረጋገጥ ይቻላል” ብለዋል።
“እነዚህ አስፈላጊ የሆኑ የግል እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ከአየር ንብረት ቀውስ ጋር በቅርበት የተቆራኙ ናቸው” ብለው፥ “የአየር ንብረት ቀውስ ሰፋ ያለ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ አንዱ መገለጫ ነው” ሲሉ ተናግረው፥ እነዚህ ችግሮች ካልተፈቱ አካባቢን ከጉዳት ለመጠበቅ የሚቀርቡ ምንም ዓይነት የቴክኒክ መፍትሄዎች የሚፈለገውን ግብ ማሳካት እንደማይችሉ ገልጸው፥ በዚህ ረገድ መፍትሄዎች በሚዘጋጁበት ወቅት ለድሆች እና ለአካባቢ ቀውስ ተጋላጭ ለሆኑ ሰዎች ልዩ ትኩረት መስጠት አስፈላጊ መሆኑን አጥብቀው ተናግረዋል።
እምነት ሕይወትን እና ተፈጥሮን ለመጠበቅ ያግዛል
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ ማኅብረሰባችንን የሚነኩ የተለያዩ ጉዳዮች እርስ በርስ መያያዛቸውን የሚገልጽ ባለብዙ ገጽታ አቀራረብ በእምነት ዕይታ ላይ የተመሠረተ መሆኑን ጠቁመው፥ “ዓለማችን በእግዚአብሔር የተፈጠረች እና በአፈጣጥሯም መልካም እንደሆነች የሚያምኑ ሰዎች ይህ የእምነታቸው መስፈርት ስለሆነ፥ ፍጥረትን ለመንከባከብ የበለጠ ኃላፊነት እንዲወስዱ ይገደዳሉ” ሲሉ ተናግረዋል።
ነፍስሔር ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” በሚል ርዕሥ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ 2015 ዓ. ም. ይፋ ባደረጉት ሐዋርያዊ መልዕክታቸው፥ “የእግዚአብሔርን የእጅ ሥራ ጠባቂዎች የመሆን ጥሪያችንን መኖር ለበጎ ሕይወት አስፈላጊ ነው” ያሉትን በመጥቀስ፥ የተለያዩ በርካታ ሃይማኖቶች ፍጥረትን እንደ መለኮታዊ ስጦታ እንደሚረዱት እና የሕይወት ቅድስናን እንደሚደግፉ ተናግረው፥ “ሃይማኖታዊ እምነት ሕይወትን ለመጠበቅ እና ተፈጥሮን ለመንከባከብ ያለውን ጠቅላላ ፍላጎት ያጠናክራል” ብለዋል።
ተስፋ ከፍተኛ አንቀሳቃሽ ኃይል ነው
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ፥ “ዛሬ በዓለም ላይ ባሉ ተግዳሮቶች እና ውጥረቶች ምክንያት ለፍጥረት አክብሮት ማጣት፣ የተፈጥሮ ሃብቶችን በመበዝበዝ እና በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የኑሮ ጥራት ቀስ በቀስ በመቀነሱ ሰላም አደጋ ላይ እንደሚወድቅ ያለው ግንዛቤ እየጨመረ መጥቷል” ብለዋል።
በተጨማሪም በአየር ንብረት ጉዳዮች ላይ በሚደረጉ ድርድሮች ውስጥ ብዙውን ጊዜ የአቅጣጫ ለውጥ እና ስልጣን የማጣት ፍርሃት እንዲሁም እርግጠኛ ያልሆኑ ውጤቶችን መፍራት እንደሚኖር ጠቅሰው፥ በዚህ ረገድ ዓለም አቀፍ ትብብር ተያያዥ እና ወደፊት የሚመራ ባለብዙ ወገንተኝነት በመሆኑ እነዚህን ፍርሃቶች ማሸነፍ እንደሚቻል አስረድተዋል።
የሃይማኖት መሪዎች እና ማኅበረሰቦች በዚህ ላይ ትልቅ ሚና ሊጫወቱ እንደሚችሉ አፅንዖት ሰጥተው፥ ምክንያቱም “መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎች ፍርሃት በተስፋ እንዴት ሊወገድ እንደሚችል በሚገልጹ ምሳሌዎች የተሞላ ነው” ብለው፥ “ተቃዋሚዎች ወይም ተጠራጣሪዎች ቢኖሩም ተስፋ ኃይለኛ አንቀሳቃሽ ኃይል ሊሆን ይችላል” ሲሉ በድጋሚ ተናግረዋል።
በተባበሩት መንግሥታት የዓየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ (COP30) የታየው ዕድገት፥ የጋራ ጥቅም ከትርፍ ይልቅ ቅድሚያ ወደሚሰጥባቸው ኢኮኖሚያዊ ሞዴሎች፥ በፍትሃዊ ሽግግር በሰብዓዊ ክብር ላይ ብቻ የተመሠረቱ ሳይሆን በአብሮነት እና በእውነት ላይ መሆኑን አስረድተው፥ ሆኖም ሃብታም አገሮች ድሃ አገሮችን በገንዘብ እንዲደግፉ እና ሰውን ማዕከል ያደረገ አዲስ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ማዕቀፍ በመፍጠር እነዚህን መንግሥታት መርዳት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።
ፍቅርን ማሳደግ
ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ 14ኛ በመልዕክታቸው ማጠቃለያ፥ በፍቅር እና ለአካባቢ እውነተኛ እንክብካቤ በማድረግ አስፈላጊነት ላይ በማትኮር፥ ይህም ርዕሠ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንችስኮስ “ሲቪክ እና ፖለቲካዊ ፍቅር” ብለው የጠሩትን እንደሚያካትት ተናግረዋል።
በማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ ማኅበረሰቡን የበለጠ ሰብዓዊ እና የበለጠ ብቁ ለማድረግ፥ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ባህላዊ አዲስ የፍቅር እሴት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበው፥ የ “ውዳሴ ላንተ ይሁን” ሐዋርያዊ መልዕክት በድጋሚ በመጥቀስ፥ ይህም “የአየር ንብረት ቀውስን ለመቋቋም ትላልቅ ስልቶችን ለመንደፍ ይረዳል” ሲሉ አስረድተዋል።
ቅዱስነታቸው በመጨረሻም፥ የስብሰባው ተሳታፊዎች የእንክብካቤ ባህልን ሊያበረታቱ እና ፍቅርን ለመገንባት አስተዋጽኦ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
